Tuesday, May 17, 2016

ውሸት ማራባት ከጥቅም ውጪ የሚሆንበት ጊዜ አለው፡፡የማታ ማታም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ May 17, 2016 – ምኒሊክ ሳልሳዊ

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) ሰዎችም በአንድ ውሸት ሲሳቡና ያንን ውሸት የራሳቸው ሲያደርጉ ከዚያ የሚለያቸው ኃይል አይኖርም፡፡ ኦርጅናሌ ዋሾውን እንደተአምረኛ ያዩታል፡፡ በዙሪያው ይከባሉ፡፡ እንደመንጋም ይነዳሉ፡፡ በየፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳያችን አንፃር የሌለንን አለን፣ ያለንን የለንም ብለን ከዋሸንና ካሳመንን፤ ተከታያችን ሊደሰትበት፣ አልፎም ሊኮራበት ይችላል፡፡ ይሄ እርግማን ነው፡፡ እርግማኑ በመንግሥትም፣ በተቃዋሚም፣ በሰባክያንም፣ በምዕመናንም አንፃር ብናሰላው ያው ነው፡፡ ህዝብን ማታለል ክፉ እርግማን ነው፡፡ የማታ ማታም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ያም ሆኖ እንደማናቸውም ነገር ውሸትም ከጥቅም ውጪ የሚሆንበት ጊዜ አለው፡፡
ያለአቅማችን ጉልበተኛ ነን ማለትም ሆነ ጉልበተኛ ሆነን ምስኪን ኮሳሳ ነን ማለትም ያው መዋሸት ነው፡፡ እያየን አላየንም፣ እየሰማን አልሰማንም፣ እያጠፋን አላጠፋንም ማለትም ያው መቅጠፍ ነው! ስለግልፅነት እያወራን የበለጠ ሚስጥራዊ የምንሆን ከሆነ ያው መዋሸት ነው፡፡ ዛሬ ያልነውን ነገ ካልደገምነው ያው መዋሸታችን ነው፡፡ ሰውን በሸራ ኳስ እያጫወትን እኛ በካፖርተኒ የምንጫወት ከሆነ ያው ማጭበርበራችን ነው፡፡ያብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክም ያው መዋሸት ነው!ካፈርኩ አይመልሰኝ ማለትም ያው መዋሸት ነው!
አስገድደን የምንፈፅመውም ሆነ ዋሽተን የምናሳምነው፣ አሊያም በገንዘብ የምንደልልው፤ የዘወትሩን ሰው ቢያስጨበጭብልንም የክቱን ሰው ያሳዝናል፡፡ በመዋሸት የተገነባ አመኔታ ከጥርጣሬ የፀዳ አይሆንም፡፡የሌለ ጀግና መፍጠርም ሆነ፤ ያለን ጀግና መካድ ሁለቱም ማታለል ነው፡፡በከፋ መልኩ ሲታይ ራስንም ማታለል ነው፡፡ የሰው ዓላማ የኔ ነው ማለትና የሌላውን ስም የራስ ማድረግ፤ ከኢኮኖሚ ዘረፋም የከፋ ዘረፋ ነው፡:ውሸት እንደማግኔት መግነጢሳዊ ኃይል አለው፡፡ ማግኔት፤ በአንዳች የማይታይ ኃይል ባካባቢ ያሉ ነገሮችን ይስባል፡፡ እነዚያ ነገሮችም በፈንታቸው የመሳብ ኃይል ያበጃሉ::ባካባቢያቸው ያሉትን ነገሮች በተራቸው ይስባሉ፡፡ ያንን ኃይል ይዘው ይቆያሉ፡፡ ዋናው ነገር እውነቷን፣ እቅጯን አለመርሳት ነው፡፡ ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ

No comments:

Post a Comment