የሞቅታና የሆታ ፖለቲካ ያከስራል – ግርማ ካሳ
የኢትዮጵያ ፖለቲክ በጣም ፈታኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በጣም ከባድና አስቸጋሪ ባህል ነው ያለን። ትላንት የካብነዉን ሰው ዛሬ እንዘረጥጠዋለን። አንድ ሰው የተለየ ሐሳብ ካቀረበ ወይንም ከተቸኝ እንደ ጠላት እንቆጥረዋለን። ስንተች አንወድም።
ግፉ ጭክኔው ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተባብሷል አንጂ አልቀነሰም። የግፍ አገዛዙ ይኸው 25ኛ አመት የብር እዩቤልዩን አከብሯል። እልፍ ደርጅት ነው ያለው በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ፤ ግን ምንም የተለወጠ የተለየ ነገር የለም። አፍጥጦ የወጣው ሐቁ ይሄ ነው።
ለአገዛዙ አሁን በስልጣን ላይ መሆን ተጠያቂዎቹ በዋናነት ተቃዋሚዎች ናቸው ባይ ነኝ። በፓርቲዎች ዉስጥ ተቋማትን ከማጠናከር የተቃዋሚ መሪዎችን እላይ እንክባቸዋለን። ሲዋሹ፣ ሲያጭበረብሩ፣ ለስልጣናቸውና ለክብራቸው ሲሉ አብሮ ከመስራት ፣ ከመተባበር ሲቆጠቡ፣ ገንዘብ ሲመዘብሩ፣ የሰበሰቡትን ገንዘብ ምን ላይ እንዳዋሉት ሲጠየቁ መልስ አልሰጠም ሲሉ ፣ በሚወስኗቸው ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ስለመሆናቸው ቻሌንጅ ሲደረጉ ሲያኮርፉ፣ ዝም እንላቸዋለን። ጥያቄ የሚያቀርቡትን “ወያኔዎች ናቸው፣ እንዴት መሪያችንን ይናገራሉ ?” ብለን እንጨረጨራለን። ገንዘባችንን በልተው፣ ልባችንን ሰርቀው፣ “ሆ ሆ ሆ ” አሰኝተዉን ዘጭ ሲያደርጉን መልሰን ደግሞ እነርሱን መራገም እንጀምራለን። ተስፋ እንቆርጣለን።
አንድ አጉል የሆነ ንግግር ደግሞ አለ። “መጠላለፍ የለብንም። ወያኔ ላይ ብቻ ነው ማተኮር ያለብን” የሚል። ለምንድን ነው ወያኔ ላይ ብቻ የሚተኮረው ? ለወያኔ መኖር ምክንያቱ የተቃዋሚው መዳከም መሆኑ ተረስቶ ነው ? እንደዉም ማጭድና መዶሻ በመያዝ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከሥር አንስቶ ማሻሻል ያስፈልጋል።
ሰው ማንበብ የሚጽፈውን ብቻ እየጻፍን እንዲጨበጨብልን ማድረግ እንችላለን። በጣም ቀላል ነው። ግን ሰው መስማት የሚፈልገውን ብቻ የመናገር ፖለቲካ ውጤት አያመጣምም። አላመጣም። እዉነቱን መነጋገር አለብን። በተቃዋሚዎች ዘንድ መሰረታዊ የአካሄድ ለዉጥ መኖር አለበት።
1. የተናጥል ትግል መቆም አለበት። ቢያንስ አገር አቀፍ የሆኑ ድርጅቶች ሪሶርሳቸዉን፣ ሃይላቸውን ማሰባሰብ አለባቸው። በጎሳ የተደራጁ ደርጅቶች ጋር መሰባሰቡ ፈታኝ ቢሆንም፣ በሚያስማሙ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል።እንዲህ ሲል ትእዛዝ እየሰጠሁኝ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ለምን እንደዚያ እንደሚያስቡት አላውቅም። ሐሳብ ነው እያቀረብኩ ያለሁት።
2. የሰለጠነ፣ የመቻቻል ፖለቲካን ማራመድ ያስፈልጋል። የሰለጠነ ፖለቲካ የዴሞክራሲ ካምፑን የሚያሰፋ ነው። ከኛ ጋር የማይሰማማዉን ሁሉ ሳይቀር ወያኔ፣ ሆዳም ፣ ባንዳ እያለን የምንሰድብ ከሆነ ብቻችንን ነው የምንቀረው። እንደዉም ፖለቲካችን ከኢሓዴግ ወገን ያሉትን ወደኛ የማምጣት ሥራን ማካተት ሁሉ አለበት። ኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉትን በሐሳብ ማሳመን ከቻልን፣ እነርሱ ደግሞ ሄደው በደርጅታቸው ዉስጥ ተጽኖም ሊያመጡ ይችላሉ። ዝም ብሎ ቁም ነገር የሌለው፣ ያከረረ. የጥላቻ ፣ የንዴት ፖለቲካ የትም አያደርሰንም። ፖለቲካ ማለት ወዳጆችን ደጋፊዎች ማፍራት ነው። የስድብ፣ የእልህ፣ የንዴት ፖለቲክ ሰዉን የሚገፋ እንጂ የሚሰብ አይደለም።
3. ሕዝብን በየክልሉ ማደራጀት ያስፈለጋል። የፖለቲክ ሥራ አዲስ አበባ ባሉ ጽ/ቤቶች ወይንም ከኢሳት ወይን አሜሪካን ዽምጽ ወይም ፓልቶክ ጋር በስልክ የሚደረግ ቃለ ምልልስ አይደለም። የፖለቲካ ሥራ ወደ ሕዝብ ወርዶ ህዝብን ማደራጀት ይጠይቃል። ወደ ህዝብ ያልወረደ ትግል ዋጋ የለውም።
4. የድርጅት መሪዎች አምባገነን እንዳይሆኑ የሚቆጣጠር አሰራር መኖር አለበት። የድርጅቶች ተቋማት ጠንካራ መሆን አለባቸው። በቅንጅት ጊዜ ሲያምሱን የነበሩት እነ ኢንጂነር ሃይሉ ሻወል ነበሩ። በመኢአድ ዉስጥ የአቶ ማሙሸትና የአቶ አበባው ዉዝግብ ነበር ደርጅቱን የጎዳው። በሰማያዊ ዉስጥም የነበረዉን የምናወቀው ነው። መሪዎች ሲበጠብጡ …
5. ትግሉ ከኤርትር መንግስት ነጻ መሆን አለበት። ከሻእቢያ መመሪያ እየተቀበሉ የሚደረግ ትግል ከወዲሁ የሞተ ነው። ብዙ አርቆ ማሰብም አይስፈልግም። ኢትዮጵያዉይን አይኖቻችንን በዉስጣችን ያለው ሃይል ላይ እንጂ አስመራ ላይ ማድረግ የለብንም። ይኸው ላለፉት 25 በአስመራ ተረዳን እያሉ እንታገላለን የሚሉ ደርጅቶች ብዙ ነበሩ። ግን አንድ ቀበሌ ለመቆጣጠር ቻሉ ? መልሱን ለአንባቢያን።
6. ትግሉ ያለው ኢትዮጵያ ዉስጥ ነው።ዲሲ፣ ወይ ጀርመን፣ ወይ ሲያትል ፣ ወይ አስመራ አይደለም።
ወገኖች ኢሕአዴግን በጣም ስለጠላን፣ በጣም ስለረገምነው፣ በጣም ጠዋትና ማታ አመራሮችን ስለዘለፍን፣ ነጋ ጠባ በራዲዮና ቴለቭዥን ፕሮፖጋንዳ ስለሰራን፣ አንድ ሺህ የፖለቲክ ደርጅቶችን ስላኮቶሎተልን፣ በየሰብሰባዎችን ስለፎከርን እና “ወያኔ አለቀላት” ስላለን፣ አሁን ያለውን ስርዓት አንለወጥም። አንሞኝ። በጭራሽ አንለዉጥም።፡ ከዚህ በፊት እንዳልኩት 25 እንዳከበርን 50 የወርቅ እዩቤልዩ እናከብራለን። በግሌም ውጤት በማያመጣ ትግል ላይ ጊዜ ማጥፋት አልፈለግም። በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ መሰረታዊ ለዉጦች የማይታዩ ከሆነ ፣ የሰለጠነ ፖለቲካ የሚያራመድና የሚመራ ድርጅት ወይንም የድርጅት ስብስበ ከሌለ የፖለቲካ እንቅስቃሴዬን መመርመር ያለብኝ ይመስለኛል። ለማንኛውም እስቲ የሚሆነውን ሁኔታ በቅርበት እንከታተላለን። ለጊዜው ትኩረቴ መኢአድ እና ሰማያዊ ላይ ነው። መኢአድ ጠቅላላ ጉብዬን በተሳካ ሁኔታ አድርጓል። አዲስ አመራር መርጧል። ሰማያዊም ያሉ ችግሮቻቸውን በዉይይት ለመፍታት ተሰማምተዋል። ምናልባት እነዚህ ደርጅቶች ቀደም ሲል ከሚያደርጉት በተሻለ ሁኔታ ጠንካራ ሆነው ሊወጡ ይችሉ ይሆናል።
(በነገራችን ላይ ሐሳብን በሐሳብ መመከት ተስኗችሁ ወደ ስድብ የምትሄዱ፣ “ወያኔ፣ ሆዳም ሰላይ ” ወዘተረፈ ለምትሉ ወገኖች የፈለጋችሁን የማለት መብታችሁን እያከበርኩ፣ በናንተ እንዲህ ማለት ቅንጣት ያክል እንደማልነቃነቅ እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ። እኔ የምታዘዘው ለፈጣሪዬና ለሕሊናዬ ነው። ነጻነቴንም እወደዋለሁ።፡ የአገራችን ፖለቲክ ድብቅ እና ዉስጥ ዉስጡን ነው። እኔ ፖለቲካችን ግልጽነት ሊኖረው ይገባል ባይ ነኝ። በመሆኑም ይጠቅማል ብዬ እስካሰብኩ ድረስ መጦመሬን እቀጥላለሁ። ደስ የማትሰኙ ካላችሁምንም ማድረግ አልችልም። ጽሁፎቼን አለማንበብ ትችላላችሁ። ያስገደዳችሁ የለም። ስድባችሁን ግን እዚያው የለመዳችሁበት ቦታ አድርጉት)
No comments:
Post a Comment