ኢትዮጵያዊያን ሯጮች በካናዳ ኦታዋ ማራቶን ድል ቀናቸው!
ዘገባ – በናታ
በካናዳዋ ኦታዋ የጎዳና ላይ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊያን በሁለቱም ጾታዎች ድል ቀንቷቸዋል። እ.ኤ.አ. በ1975 የተጀመረው ታሪካዊው የኦታዋ የሩጫ ውድድር በማራቶን ክብረወሰኑ የተያዘው በኢትዮጵያዊያን አይበገሬ ሯጮች ሲሆን በወንዶች የማነ ጸጋዬ 2:06:54 በመግባት የክብረወሰኑ ባለቤት ሲሆን በእንስቶች ደግሞ ትእግስት ቱፋ 2:24:30 በመግባት የስፍራው የእንስቶች ቁንጮ ናት።
በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር የወርቅ ደረጃ በተመደበው በፈታኙ የማራቶን ሩጫ ውድ ድር ላይ ኢትዮጵያዊያኑ አንጸባራቂ ድል አስመዝግበዋል። ይህም ከማራቶን ድሎች እየራቀች ለነበረችው ኢትዮጵያ ተስፋ ፈንጣቂ የድል ብስራት ነው። እሁድ እለት በተካሄደውና ሞቃታማውን የአየር ሁኔታ ታግለው ድል ማስመዝገብ የቻሉት አትሌቶቻችን በወንዶች ምድብ ዲኖ ሰፊር 2:08:14 በሆነ ሰዓት በቀዳሚነት ሲገባ እሱን በመከተል የ19 ዓመቱ ወጣቱ ተስፈኛው ሹራ ኪታታ 2:10:04 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ ኬንያዊው ዶሚኒክ ኦንዶሮ 2:11:39 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
በእንስቶች ምድም ደግሞ ድንቋ ራጭ ኮረን ጃለላ ስምንቱን ኪሎ ሜትሮች ብቻዋን በመሮጥ በአንደኝነት አጠናቃለች የገባችበትም ሰዓት 2:27:06 ሲሆን እስዋን በመከተል አበሩ ማከሪያ፣ ሰቻሌ ደላሳ እና ማክዳ አብደላ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ የአገርዋ ልጆች በመግባት ሜዳሊያውን ኢትዮጵያዊያን ጠራገው ወስደውታል። አበሩ ማከሪያ 2:29:51 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ፣ ሰቻሌ ደላሳ 2:32:46 በሆነ ሰዓት በመግባት ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን ፈጽመዋል።
No comments:
Post a Comment