የትግላችን መሰረት ህዝባችን ነው እና ህዝባችንን ተደራሽ ለማድረግ የምናደገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል!
ረቡእ ግንቦት 10/2008
ረቡእ ግንቦት 10/2008
ትግል ክስተት ሳይሆን ሂደት ነው፡፡ ይህን ሂደት የሚፈጥሩትም ሆነ ከዳር የሚያደርሱት ደግሞ የትግሉ ባለቤት የሆኑት ህዝቦች ናቸው፡፡ እንደአገራችን ባሉ ዲሞክራሲ ባልዳበረባቸው አገራትና አሁን ባለው አለም አቀፍ ተለዋዋጭ ፓለቲካ የትግል ሂደት እንደ ሜዳ ለጥ ያለና የተደላደለ አይደለም፡፡ እንቅፋትና አሜኬላ የበዛበት፣ በዳገትና ቁልቁለት የተሞላ ነው፡፡ የትግሉ ባለቤቶች በእነዚህ የትግል ተፈጥሯዊ ሂደቶች ውስጥ ሲያልፉ የሚኖራቸው ምላሽ እንደግለሰባዊ ጥንካሬያቸው፣ ለትግሉ እንዳላቸው እምነት፣ እንደ ልምድና እንደተሞክሯቸው ይለያያል፡፡ ጥቂት ነገሮች ውዥንብር የሚፈጥርባቸው እንዳሉ ሁሉ በፕሮፓጋንዳ እና በአሉባልታ ቀርቶ በኃይልም የማይፈቱ ቆራጥ ታጋዮች በርካቶች ናቸው፡፡
የአንድ የትግል ሂደት ከሚገጥሙት ተግዳሮቶች መካከል የብዙሀኑን ህዝብ ስሜት ከነባራዊው ሁኔታ ጋር በማጣጣም ትግሉን ስኬታማ የሚያደርግ የትግል አቅጣጫ መንደፍ ነው፡፡ ይህን የትግል አቅጣጫም የትግሉ ባልተቤት የሆነው ህዝብ በሚገባ ሊረዳው ይገባል። የትግሉን አቅጣጫ ህዝብ በትክክል ካልተረዳው ትግሉን ከዳር ማድረስ አስቸጋሪ ይሆናል። የትግሉ አቅጣጫ በትክክል ለህዝብ ባልደረሰበት ሁኔታ በትግሉ እና በደል በሚፈጥረው ህዝባዊ ቁጭት፣ ይህም በተራው በሚወልደው የህዝብ ስሜት መካከል ክፍተት ይፈጠራል፡፡ አንድ ህዝባዊ ትግል በቀዳሚነት ከሚይዛቸው ተግባራት መካከል የትግልን ሂደት እና አቅጣጫ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ታጋዩ ህዝብ ዘንድ ማድረስ እና ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እና ህዝባዊ መነቃቃትንም መፍጠር አንዱ እና ወሳኙ ጉዳይ ነው። በተለይም ትግሉ የረጅም ጊዜ ትግል በሆነበት ተጨባጭ ከህዝብ ልብ ውስጥ አስጠብቆ ማቆየት እና የህዝብን ወኔ በበዳዮች ብትር ብዛት እንዳይሰበር ተከታታይ እና ቋሚ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራን መስራት የትግሉን ህልውና ማስጠበቂያ አንዱ መሳሪያ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በመንግስት የተጫነብንን ብሄራዊ ጭቆና በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል የትግል አቅጣጫ አስምረን እንገኛለን። ይህ ትግላችን ጨቋኙ ስርዓት ትግስታችን እንዲሟጠጥ፣ ወኔያችን እንዲሰበር በማቀድ በሚከፍታቸው በሮች ውስጥ የሚያስገባ፣ ከተመከረበትና ከታሰበበት የትግል መስመር ወጥተን ግብታዊነትን ወይም ስሜታዊነትን እንድንከተል የሚያደርግ፣ ሁሉን አቀፍ በሆነ መብት የማስከበር ትግል ፋንታ ጥቃቅን ቀዳዳዎችን ብቻ በሚደፍኑ ጊዜያዊ የትግል ስልቶች ተሸብበን እንድንቀር የሚያደርግ ሂደትን የሚከተል አይደለም። ትግላችን የህዝብን ፍላጎት የተረዳ፣ ተለዋዋጭ ስሜትን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማዛመድ እና ሚዛኑን በመጠበቅ ከጊዜያዊ ክስተቶች ይልቅ መርሆች ላይ የተመረኮዘ ነው። ትግላችን ወቅታዊ እና ተጫባጩን የሚያውቅ፣ የግንዛቤ አድማሱ ሰፊ የሆነ፣ የሚጠበቅበትን የተገነዘበ፣ የትግሉን ሂደትና ፍሰት በሚገባ የተረዳ፣ የአገሩን እና የማህበረሰቡን አብይ ችግሮች በመለየት ለችግሮቹ ተጨባጭ መፍትሄ የማስቀመጥ አቅም ያለው፣ እምነቱን በትክክል ተረድቶ ተግባራዊ የሆነ እና የሰለጠነ ማህበረሰብ በመፍጠር ሙሉ መብታችንን የምንጎናፀፍበት እና ይህንም በዘላቂነት የምናስጠብቅበት ትግል ነውና አቋራጭ መንገድ የለውም!
የትግል አቅጣጫችን ራሳችንን በማጎልበት እና በመንግስት ላይ ጫና ሊፈጥሩ የሚችሉ ተለዋዋጭ ስልቶችን ቀርፆ ተግባራዊ ከማድረግ ባልተናነሰ የህዝቡን ግንዛቤ ከትግሉ አቅጣጫ ጋር ተመቻማች እንዲሆን ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት። ለትግላችን ስኬታማነት የተነደፈው የትግል አቅጣጫ ብቻውን በቂ አይደለም። ይህንን የትግል አቅጣጫ ተግባራዊ የሚያደርገው ህዝብ አቅጣጫውን በትክክል ተረድቶ፣ ይህንንም ጠብቆ እና አስጠብቆ በሚያደርገው የትግል እንቅስቃሴ ጭምር መሆኑንም በትክክል እንረዳለን።
በቀጣይ የትግል አቅጣጫችን እና ከህብረተሰባችን የሚጠበቀውን አስተዋጾ በተመለከተ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ እነዚህን ስራዎች ህዝብ ጋር ለማድረስ ያሉን አማራጮች ውስን በመሆናቸው ማህበራዊ ድህረ-ገፅን በጊዜያዊ አማራጭነት ለመጠቀም ተገደናል። በዚህም ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ ርእሶች በፅሁፍ ሲዳሰሱ ቆይተዋል። ይህ ግን ብዙሃኑን ህዝብ ለመድረስ አላስቻለንም። ችግሩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ቁጥር አናሳነት ብቻ እንዳለመሆኑ መጠን ማህበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም እድሉ ያለው ህብረተሰባችንም መልእክቱን ሊያገኝ የሚችልባቸውን መንገዶችን ማመቻቸት እና አማራጮችንም ማቅረብ ያስፈልጋል። በዚህ ዙሪያ በቀጣይ ሰፊ ስራ ይጠብቀናል። በመሆኑም እስካሁን ከምናስተላልፋቸው የፅሁፍ መልዕክቶች ባሻገር በተለያዩ ርዕሶችና የትግል አቅጣጫችን ዙሪያ ሳምንታዊ የድምፅ መልዕክቶችን መጀመር ቀዳሚ አማራጭ እና ለቀጣይ ስራ አጋዥ ተደርጎ ተወስዷል። ከዚህ አንጻር እስካሁን በጽሁፍ የተለቀቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ጨምሮ ተከታታይ መልእክቶችን በቅርቡ በአላህ ፍቃድ በድምጽም የምናደርስ ይሆናል። ይህ ጅምር በሙያው ችሎታ እና ፍላጎት ያላቸው እህትና ወንድሞች ለትግሉ ቀጥተኛ አስተዋጾ ለማድረግ የሚያስችል አንድ በር ነው እና ይህን ሀላፊነታችንን ሁላችንም እንወጣ ዘንድ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
ትግላችን በተጠናከረ መልኩ ሁሉን አሳታፊ ሆኖ ይቀጥላል!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment