Monday, May 23, 2016

በኢትዮጵያ ዘረፋው እየተባባሰ መጥቷል – ግብፅ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅሟን በእጅጉ እያሳደገች መሆኑ ታወቀ (የፍኖተ ዴሞክራሲ ራዲዮ አጫጭር ዜናዎች)

አጫጭር ዜናዎች
የወያኔ ዘረፋ ከዓመት ዓመት እየተባባሰ መሄዱ ይፋ ሆነ
የወያኔ ምርጫ ቦርድ የአስራ አራት ፓርቲዎችን ፍቃድ መሰረዙ ታወቀ
ወያኔ በቀሰቀሰው ቀውስ አገሪቱ ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ ማድረጉ ተገለጸ
ግብፅ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅሟን በእጅጉ እያሳዳገች መሆኑ ታወቀ
በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በበረካታ ህዝብ ላይ ደንገተኛ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተገለጸ
የውጭ አገር ዜናዎች
አጫጭር ዜናዎች
 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይባል የነበረውና ዛሬ የስም ለውጥ አድርጎ የአፍሪካ ሕብረት የሚባለው ተቋም መስራቾቹ የወጠኑትን ግብ አሁንም መምታት እንዳልቻለ ዳግም ተዘገብ ። በመጭው ሳምንት የአፍሪካ ቀን በሚል የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው ይህ ተቋም ለባዕዳን የተሸጡ መሪዎችና አምባገነኖች መሰብሰቢያና መሳሪያ ከመሆን አልፎ ለአህጉሪቷ የሚጠቅም ይህ ነው የሚባል ስራ አልሰራም የሚሉ ታዛቢዎች አሁንም ቢሆን ለአፍሪካ አንድነት ጠንቅ
ሆነው ያለው አሜሪካ የጦር ተቋሙ ፔንታጎንና የስለላ ግዙፍ መስሪያ ቤቱ ሲአዬ የአፍሪካ አንድነት እንዳይጠናከር ዋና ዕንቅፋቶች ሆነው ቀጥለዋል ተብለዋል ። በአህጉሪቷ ባሉት የጦርነት ፍንዳታዎች በስተጀርባ የምዕራባውያን እጅ እንዳለ ግልጽ ከሆነ ውሎ አድሯል የሚሉት እነዚህ ተቺዎች የአፍሪካን ሀብት በመዝረፉ ስምሪት ቻይናም ዋና ሆና ብቅ ማለቷንም ጫና ሰጠው አቅርበውታል ። ሁሉም ግን ከአምባገነኖች በስተጀርባ ሆነው አፍሪካን እየጎዱ መቀጠላቸውን ክብደት ሰጥቶ ማየት ይገባል ተብሏል ።
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች መተባበር ተስኗቸው ለሚገኙበት አሳዛኝና ጎጂ ሁኔታ በቅድሚያ ተጠያቂ ራሳቸው ናቸው ቢባልም ህብረት እንዳይመሰረት ዕንቅፋት የሆኑት ሻዕቢያና አሜርካ ናቸው ተባለ ። ይህን ያሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች ግምገማቸውን ሲያብራሩ ሻዕቢያ የሀቀኛ ሀገር ወዳዶች ህብረት መመስረቱ ላለው ዕቅድ ጎጂ ነው ብሎ አምኖ በመቀጠሉ በኤኤፍዲ ምስረታ ጊዜ እንደታየው የህብረት ጥረቶችን በአቋራጭ ጠልፎ እየጣለና በህብረት ደጋፊነት ሽፋን ክፍፍልን እያስፋፋ ሲሄድ ቆይቷል ብለዋል ። የወያኔ ደጋፊ አጋር የሆነችውም አሜሪካ እንዲሁ የህገርን ሉ ዓላዊነት የሚያስከብር ሀገር ወዳድ ሀይል በኢትዮጵያ በስልጣን እንዲመጣ ስለማትፈልግ የሀገር ወዳዶችን ህብረት ከማደናቅፍና ለወያኔ ከመታደግ ወደኋላ ብላ አታውቅም በሚልም ትችት ቀርቧል ። አሜሪካ በተለይ በውጭ ሀገር ሆነ በውስጥ ሰላዮቿና ቅጥረኞቿን አሰማርታ ሀገር ወዳድ ሀይሎችን እየከፋፈለችና እያጠቃች መሆኑን በአሁኑ ጊዜ አሌ የሚል ብዙ ሰው የለም ሲሉ ተቺዎቹ አረጋግጠዋል ። ወያኔና አሜሪካን በመከተል የህብረት ጥረቶችን በዚህም በዚያም የሚያደናቅፉትን አስመሳይ ሀገር ወዳዶችና ተቃዋሚዎችም ሕዝብ እያደር ነቅቶባቸዋልም በሚልም መረጃ ተሰንዝሯል ።
 በቀይ ባሕር አካባቢ እየተካሄደ ባለው የጦር መሳሪያ ንግድ ኢራን፤ግብጽ፤ ሳውዲ አረቢያ፤ ሻእቢያና ወያኔም አሉበት ተባለ። ባለፉት ወራቶች በርካታ ጀልባዎች መሳሪያ ጭነው ወደ ፑንትላንድና የመን ሲጓዙ መያዛቸውን ያጋለጡ ክፍሎች በሶማሊያ ውስጥ አል ሸባብ የተባለውን ጽንፈኛ ቡድን እንዋጋለን ከሚሉት የአፍሪካ ህብረት ሀይሎች ውስጥም ኬንያና ዩጋንዳ መሳሪያ ሲሸጡ መገኘታቸው ተጠቅሰዋል ። የኢራን መሳሪያ የሚላከው ለየመን ሁቲ አማጽያን ብቻ ሳይሆን በሶማሊያ ላሉም ጂሃዲስት ለሚባሉ ሀይሎች ነው ያሉ ክፍሎች ደግሞ ወደ ፑንትላንድ በብዛት እየመጣው ያለ የጦር መሳሪያ አንዱ ዋናው ምንጭ ወያኔ ነው ተብሎም ተጠርጥሯል ።  በቅርቡ የባዕድ የንግድ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ መሬት ቢሮዎችን ከፍተው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ህጎችን ወያኔ ሊያጸድቅ ነው ተብሏል ። የወያኔ ኤኮኖሚ ደቆ ባለበትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሰፈነበት ይህ እርምጃ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል የሚለውን ወያኔ እንዳልመረመረውና ደንታም እንዳልሰጠው ውስጠ አዋቂዎች ይናገራሉ።
 ከወያኔው አየር መንገድ ጋር ንትርክ የገባው የአሜሪካ ፕሪንስ ሰርቪስስ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ለፕሬዚዳንት ኦባማ የተቃውሞ ደብዳቤ መላኩ ተነገረ። ፕሪንስ ሰርቪስስ ተቃውሞ ያሰማው የአሜሪካ መንግስት ምንም ድጋፍ ሳይሰጠው መቆየቱን በተመለከተ ሲሆን የወያኔ ወዳጅ የሆነችው ሂላሪ ክሊንተን የአየር መንገዱ ጠበቃ የሆነው ከሚካኤል አታዲካ የቅርብ ትውውቅ ያላት መሆኗንም አጋልጧል ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚባለው ተቋም በወያኔ ሙሉ ቁጥጥር ስር መግባቱና ከሰራተኞቹ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና የወያኔ አየር መንገድ ይባል የሚሉ ክፍሎች አጋልጠዋል ።
 ወያኔ የሀገር ወደቦችን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ በጅቡቲ ሲጠቀም መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ከሶማሊያ የተገነጠለችው የሶማሌላንድ ወደብን በርበራንም መጠቅም መጀመሩ ሲነገር ቆዩታል ። ጅቡቲ ወደቧን ለዱባይ አኮናትራ ብትቆይም በጅቡቲና ዱባይ መሃል በተነሳው ንትርክ ግንኙነታቸው ሻክሮ አሁን ደግሞ ዱባይ የበርበራን ወደብ ለመጠቀም የ30 ዓመት ፍቃድ፤ሊዝን ወስዳለች ተብሏል ። ወያኔ ይህን ሁኔታ–እንደ አልጄርሱ ስምምነት–ድል ና ጠቃሚ ብሎ ሊያቀርብ ደፋ ቀና እያለ መሆኑን የነቀፉ ክፍሎች የሳውዲና የካታር ወደ ኢርትራ በጦር ደረጃ ሳይቀር መግባት፤ ግብጽ አሁንም ኢላማዋን ያልቀየረች ሆና ባለበት በርበራ ላይ የዱባይ/የአረብ ቁጥጥር መስፈኑ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ሳይሆን ከበባውን የሚያጠናክርና የሚጎዳት ይሆናል ሲሉ ታዛቢዎች ገምግመዋል ። ይህ በዚህ እንዳለ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኔታናሁ በሐምሌ ወር ኢትዮጵያን ይጎበኛል ተብሏል ።
 በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቦሌ ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግንቦት 10 ቀን በህገ ወጥ መንገድ
ተሰርተዋል የተባሉ ቤቶችን ለማፍረስ የወያኔ ፌዴራል ፖሊስና የቤት አፍራሽ ኃይል ቤት ከሚፈርስባቸው ዜጎችና
ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ባደረጉት ግጭት በትንሹ ሰባት ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።
ሕዝቡ ክረምት እየመጣ እያለ ያለማስጠንቀቂያ ቤታችን አይፈርስም ብሎ በማመጹ የወያኔ ፌዴራል ፖሊስ
በጥይት ዜጎችን የገደለ መሆኑ ታውቋል። በተከታታይ ቀናትም አመጽ በማነሳሳትና በመቀስቀስ በሚል ምክንያት
በርካታ ሰዎች ተወስደው መታሰራቸውም ተዘግቧል። ባለስልጣኖቹ የዜጎችን ቤት አፍርሰው ቦታውን ኢንቬስተር
ለተባሉ ሀብታሞች ለመስጠት እንዳቀዱ ተደርሶበታል።
 በዚህ ሳምንት የወያኔ አግአዚ ጦርና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በዓላማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጽመው
ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። ተማሪዎቹ የተደበደቡት በሰላማዊ መንገድ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ የመብት ጥያቄ
በማንሳታቸው ሲሆን ብዙዎቹ ከቀላል መፈንከት እስከ ስብራት ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል።
የወያኔ ዘረፋ ከዓመት ዓመት እየተባባሰ መሄዱ ይፋ ሆነ
 ዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት ለወያኔ ፓርላማ ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት ላይ ከዓመት ዓመት የገንዘብ መባከንና የንብረት ዘረፋ እየተካሄደ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ለገንዘብ ብክነቱ እንዲያመች የገንዘብ ክፍያዎች በአብዛኛው የሚፈጸሙት የሂሳብ አሰራርን በጣሰ መልኩ እንደሆነ ተገጿል፡፡ በዚህ መሠረት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሂሳብ አሰራር ያልተወራረደ የሚባል ሂሳብ የተዘረፈ ማለት እንደሆነ ከፍተኛ የሂሳብ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በሪፖርቱ ላይ ከተገለጹት ጉዳዮች መሀል የወያኔ ሹመኞችን አረመኔነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየው የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎችን ለአርሶ አደሮች እየሸጠ መሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይም የአምስት መቶ ሰባ ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው መድሀኒቶች በመድሀኒት ፈንድ አቅርቦት መጋዘን ውስጥ መገኘታቸው ተጨማሪ ዘግናኝ ጉዳይ ሆኗል፡ ፡ መድሀኒቶቹ የተቀመጡት አዲስ ከሚገቡ መድሀኒቶች ጋር እየተመሳጠሩ ሊታደሉ እንደሆነ የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ያስረዳሉ፡፡ በርካታ ንብረትም እንደተዘረፈ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ በኢትዮጵያ ብዝሀ-ህይወት ኢንስቲቲዩት ስም ከተመዘገቡ መኪናዎች አስሩ መዘረፋቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ ይህ ድርጊት መሬት ውስጥ እንደሚባሉት የጠፉት ሰማያ ስምንት የኮንዶሚኒየም ህንፃዎች ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዘረፋ ላይ ግንባር ቀደም የሆኑት ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የትምህርት ሚንስቴር፣ ምርጫ ቦርድ፣ መከላከያ ሚንስቴር፣ ደብረ ማርቆስ
ዩኒቭርሲቲ፣ ወላታ ሶዶ ዩኒቭርሲቲ፣ ሐዋሳ ዩኒቭርሲቲ፣ ባህር ዳር የኒቭርሲቲ፣ መቀሌ ዩኒቭርሲቲ ሲሆኑ በአጠቃላይ ዩኒቭርሲቲዎቹ የዘረፋ ተቋማት እንደሆኑ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በተመሳሳም አብዛኛዎቹ ሆስፒታሎችም በዘረፋ የተጨማለቁ እንደሆነ ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል፡፡

የወያኔ ምርጫ ቦርድ የአስራ አራት ፓርቲዎችን ፍቃድ መሰረዙ ታወቀ

 ወያኔ ምርጫ ቦርድ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት አስራ አራት የወያኔ ተቃዋሚ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን ፍቃድ መሰረዙን አስታውቋል፡፡ ወያኔ አሁን ፍቃዳቸው መሰረዙን ይፋ ያደረጋቸው ድርጅቶች በተለያየ መንገድ እያዳካማቸውና እያሽመደመዳቸው እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ከእነዚህ ከተሰረዙት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህ ድርጅት የተመሰረተው በ1997 ዓ.ም. የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በህብረት ለመታገል በተስማሙበት መሰረት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ኢሕአፓ የዚህ ህብረት አባል በመሆን የበኩሉን ጠንካራ ተሳትፎ አድርጎ እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡
ወያኔ በቀሰቀሰው ቀውስ አገሪቱ ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ ማድረጉ ተገለጸ
 ወያኔ ሕዝብን በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጎሳ በጎጥ ከፋፍሎና ሕዝብን እያፈነና እያሰረ ሕዝብን ማሸበር እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም 25 የግፍ አገዛዝ አመታት አሳልፏል፡፡ ወያኔ እራሱ በፈጠረው የጎሳ ፖለቲካና የግፍ አገዛዝ ዘመኑን ለማርዘም ካለ በቂ ጥናት በርካታ ሕዝብን የሚጎዱና የሀገርን አንድነት የሚንዱ እኩይ ተግባራትን እየፈጸመ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ከወያኔ ውስጥ አወቆች የሚወጣው መረጃ የሚያስረዳው ወያኔ በስጋ መወጠሩን ነው፡፡ በትግራይ ወርቅ አውጪዎች ታፍነዋል፡፤ በጋምቤላ ታፍነው ከተወሰዱት ህፃናት እስካንሁን ከሰማንያ ከመቶ በላይ የሚሆኑት አልተመለሱም፡፡ በቅርቡ ቤንሻንጉል ድንበር አካባቢ እርሻ ላይ የነበሩ ገበሬዎች ከሱዳን ድንበር ዘለው በገቡ ታጣቂዎች ታፍነው ተወስደዋል፡፡ እስካሁንም በወያኔ በኩል ምንም የተባለ ነገር አለመኖሩ ሕዝቡን መስቆጨቱ ታውቋል፡፡ ወያኔን እያተራመሰ ያለው ግብፅ ሙሉ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ እግረኛ ጦሯን ሰሜን ሶማሌ ሀርጌሳ ላይ ማስፈሯ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰቱ የፍንዳታ አደጋዎችና የታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴን ከኤርትራ ጋር በማያያዝ ያቀርብ የነበረው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግብፅን ሊጨምር እንደሚችል እነዚሁ ወያኔ ውስጥ ያሉ ይህን መረጃ ያደረሱን ያስረዳሉ፡፡
ግብፅ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅሟን በእጅጉ እያሳዳገች መሆኑ ታወቀ
 የግብፁ አህራም ጋዜጣ እንደዘገበው በአሁኑ ሰዓት ግብፅ የነበራትን 32 ሺ 15 ሜጋ ዋት ሰሞኑን ግንባታቸው ተጠናቆ ሥራ የጀመሩት ሲጨመሩ 35 ሺ 615 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ኃይል እንዳላት ተገልጿል፡፡ አትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታመርተው ከ2 ሺ 400 ሜጋ ዋት በላይ እንደማይበልጥ የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከንፋስ ኃይልና በቅርቡ ግንባታው እንደተጀመረ የተነገረለት የግልገል ግቤ 3 እና ቅዠት የሆነው የዓባይ ግድብ ከተጠናቀቁ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት ኃይል ከአስር ሺ ሜጋ ዋት በላይ እንደማዘል የታወቀ ነው፡፡ የሚገርመው ወያኔ ከግብፅ ጋር በዓባይ ግድብ ላይ ለገጠመው ግብግብ እያቀረበ ያለው ከግድቡ የሚወጣውን ኃይል ሃምሳ ከመቶ የሚሆነውን ሱዳንና ግብፅ እንዲጠቀሙበት ለመደራደሪያነት ማቅረቡ ነው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የግብጽ ኢጂሳት የሚባለው የስለላ ሳተላይት በአባይ ላይ ይሰራል የተባለውን ግድብ በቅርብ እየተከታተለ መሆኑ ሲነገር በግድቡ ላይ ዋና ስራ መቆሙን ወይም መጓተቱን ለመሰለል መቻሉም ተዘግቧል ።

በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በበረካታ ህዝብ ላይ ደንገተኛ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተገለጸ
 ከሚያዚያ ወር አጋማሽ አንስቶ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እደረሰመሆኑ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወቃል፡፡ በጅጅጋና በድሬዳዋ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በመላው አገሪቱ እየተዳረሰ መሆኑን ከየአካባው ከሚደርሱን መረጃዎች መረዳት ችለናል፡፡ እስካሁን ወደ 200 ሰዎች በጎርፍ አደጋ ብቻ ህይወታቸውን እንዳጡ ከሚደርሱ መረጃዎች ተገንዝበናል፡፡ በወላይታ የደረሰው የመሬት መንሸራተት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ስጋት አለ፡፡ በዋና ዋና ከተሞች አደጋ ቢደርስ ይህን ለመከላከል የተዘጋጀ አቅም ያለው ተቋም አለመኖሩም በዚያው ልክ ተጋልጧል ።
የውጭ አገር ዜናዎች
 የደቡብ አፍሪካ እውቁ ታጋይና የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ሚስተር ኔልሰን ማንዴላ የዛሬ 54 ዓመት
በዘረኛው የደቡብ አፍሪካ የነጮች መንግስት ሊያዙ የቻሉት በአሜሪካ የስለላ ተቋም በሲ አይ አባል ጥቆማ አንድ
የእንግሊዝ ጋዜጣ አጋልጧል። በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማት የነበሩት የሲ አይ ኤ አባል ዶናልድ ሪካርድ
ከመሞታቸው በፊት “ የማንዴላ ጠመንጃ” ( “Mandela’s Gun”) በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ፊልም ዳይሬክተር
ላደረጉላቸው ቃለ ምልልስ በሰጡት መልስ ኔልሰን ማንዴላን ማጋለጣቸውን ያመኑ መሆኑን ሰንደይ ታይምስ
የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ እሁድ ግንቦት 7 ቀን ባወጣው እትሙ ገልጿል። ከዚህ በፊት የሲ አይ ኤው ድርጅት
ሚስተር ማንዴላን ከመያዛቸው በፊት ሲከተታል የነበረ መሆኑና በመጨረሻም እንዲያዙ የጠቆመው የዚሁ ድርጅት
አባል ነው የሚለው ወሬ በሰፊው ሲሰራጭ የኖረ ቢሆንም የሲ አይ ኤ ባለስልጣኖች በተለያዩ ጊዜያት ሲክዱ
ቆይተዋል። ማንዴላ ለረጅም ጊዜ በልዩ ልዩ መንገድ ከደቡብ አፍሪካ የጸጥታ ኃይሎች ሲያመልጡ ከቆዩ በኋላ
ተይዘውና ተፈርዶባቸው ለ27 ዓመታት ያህል በእስር ቤት አሳልፈዋል። ማንዴላ ሲመሩት የቆየቱ የአፍሪካ ብሔራዊ
ኮንግሬስ በሬገን ዘመነ መንግስት በአሜሪካ ሽብረተኛ ድርጅት ሊስት ውስጥ ተመዝግቦ የቆየ ሲሆን ሽብረተኛ
የሚለው ስም የተነሳለት በ2000 ዓም መሆኑ ይታወቃል።
 በኮንጎ ዴሞክራቲክ ረፐብሊክ ሊደረግ በታቀደው ብሔራዊ ምርጫ በግምባር ቀደምትነት ተወዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ
የተባሉት ሚስተር ካቱምቢ ለህክምና ወደ ደቡብ አፍሪካ የሄዱ መሆናቸው ተገለጸ። ግለሰቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሄዱት በመንግስት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የውጭ አገር ወታደሮችን በገንዘብ ቀጥረሃል የሚል ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ በቁጥጥር ስር ውለው ክሳቸው እንዲታይ ፍርድ ቤቱ ማዘዣ በሰጠበት ቀን ነው። የሚስተር ካቱምቢ ጠበቃ የተሰነዘረባቸው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑና በሚገባ ለመከላከል የሚቻል መሆኑን ገልጾ ሚስተር ካቱምቢ ቀደም ብሎ በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በፓሊሶች በተተኮሰ አስለቃሽ ጋዝ ሚስተር ካቱምቢ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ሰውነታችው እየተዳከመ በመምጣቱ ለህክምና ወደ ደቡብ አፍሪካ ሂደው መታከም ግድ ሆኖባቸዋል ብሏል። የአገሪቱ አቃቤ ህግ ሚስተር ካቱምቢ ተመልሰው ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፈቃደኛ እስከሆኑ ድረስ እንዲወጡ ፈቅዷል። ሚስተር ካቱምቢ የደቡብ ካታንጋ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩና የአፍሪካ ሻምፒዮን ዋንጫን በተደጋጋሚ የወሰደው ቲፒ ማዜምቤ የተባለው የእግር ኳስ ክለብ ፕረዚዳንት በመሆን ያገለገሉ ሃብታም የንግድ ሰው ሲሆኑ በሕዝቡ ተወዳጅነት ያላቸው መሆኑ ይነገራል። ቀደም ብሎ የገዥው ፓርቲ አባል የነበሩ ቢሆንም ሚስተር ካቢላ የአገሪቱ ህገ መንግስትን በመጻረር ለሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ተዘጋጅተዋል በማለት ሌላ ፓርቲ የመሰረቱና ለመወዳደር የተመዘገቡ ናቸው። በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ስላላቸው ምርጫውንም ያሸንፋሉ የሚለው ግምት ከፍተኛ ነው። ህገ መንግስት ከሚፈቅደው ውጭ ሚስተር ካቢላ ለሶስተኛ ጊዜ ለምርጫ ሊቀርቡ ይችላሉ የሚለው ዜና የምዕራብ አገሮች እየተከታተሉት መሆኑ ተገልጿል። ሰሞኑን የሚስተር ካቢላ ተቃዋሚዎች ወደ አሜሪካ በመሄድ በሚስተር ካቢላ አገዛዝ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል። በፖለቲካ ውጥረት ምክንያት የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ሊባባስ ይችላል የሚለውም ስጋት ከፍተኛ ነው።
 የ25 አገሮች ተወካዮች በቪየና ባደረጉት ስብሰባ በቅርቡ ለተቋቋመው ለሊቢያ የአንድነት መንግስት የወታደራዊ ስልጠናና የመሳሪያ እርዳታ ለማድረግ ተስማምተዋል። ስምምነቱ ቀደም ብሎ በሊቢያ ላይ የተደረገው የመሳሪያ ዕቀባ በአንድነት መንግስቱ ወታደራዊ ኃይል ላይ እንዳይደረግና ለዚሁ ኃይ የመሳሪያና እርዳታና ወታደራዊ ስልጠና እንዲደረግ ነው። በሌሎች ሚሊሺያ ቡድኖች ላይ የሚደረገው ማዕቀብ የሚቀጥል መሆኑ ተገልጿል። ይህ በተደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለአንድነት መንግስት ታዛዥ የሆነ የሊቢያ ጦር ቀደም ብሎ በአይሲስ ኃይሎች ተይዞ የነበረውንና አቡ ግሬን የተባለውንና ሁለት ታላላቅ መንገዶች የሚገናኙበትን ቁልፍ ቦታ ከአይሲስ ኃይሎች አስለቅቆ የያዘ መሆኑን ገልጿል። ይኸው ጦር በተጨማሪም አይሲስ ወደ ተቆጣጠራትና በርካታ ኃይሎች በማስፈር ወታደራዊ ይዞታውን አጠናክሮ ወደ ሚገኝባት ሰርት ወደተባለችው ከተማ ሄዶ ከተማዋን ለማስለቀቅ ጥረት አድርጓል። ሁለትንም ቦታዎች ለማስለቀቅ በተደረጉ ውጊያዎች የአንድነት መንግስቱ 32 ወታደሮች የተገደሉበት መሆኑና ሌሎች 50 የሚሆኑ የቆሰሉ መሆኑን ገልጿል። የሊቢያ አንድነት መንግስት የአይሲስ ኃይሎችን ለመደምሰስ ተዋጊ አይውሮፕላኖች እንዲሰጡት የምእራብ መንግስታትን ጠይቋል።
 በዚህ ሳምንት ከፓሪስ ወደ ካይሮ ሲበር የነበረ አንድ የግብጽ የመጓጓዣ አውሮፕላን በአየር ላይ እንዳለ በደረሰበት አደጋ ሚዲትራኒያን ባህር ላይ ወድቆ መሰባበሩ ተነግሯል። 56 መንገደኞች እና 10 የአውሮፕላኑ ሰራተኞች አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው አውሮፕላን የጠፋው ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ በግብጽ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 8 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ ለግብጽ የአየር ክልል 10 ማይልስ ያህል ሲቀረው እንደነበር ተነግሯል። መሬት ባለ መሳሪያ የተመዘገቡ መረጃዎች አውሮፕላኑ ግንኙነት ከማቋረጡ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ በአውሮፕላኑ የመጸዳጃ ክፍል ውስጥ እና በኢሌክቶርኒክስ መሳሪያ አካባቢ ጭስ የነበረ መሆኑ የተዘገበ ቢሆን በእርግጠኛነት የአደጋው መነሻ ምን እንደሆነ እስካሁን ለማወቅ አልተቻለም። የግብጽ ባለስልጣኖች አውሮፕላን በሽብር ተግባር ተመቶ ወድቋል የሚል መላ ምት
ሲሰጡ የፈረንሳይ ባለስልጣኖች ደግሞ የአደጋው መነሻ ይህ ነው ብሎ ለመደምደም መረጃ የለም ብለዋል። የአውሮፕላኑን አካልና በተለይም ድምጽና መረጃ የሚቀዳውን መሳሪ ያ ለማግኘት ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ኃይሎች ፍለጋቸውቸውን በሰፊው የቀጠሉ መሆናቸው ታውቋል። ባለፈው መጋቢት ወር አንድ የግብጽ አውሮፕላን ተጠልፎ ወደ ሳይፕረስ እንዲበር ከተደረገ በኋላ ጠላፊው እጁን መስጠቱ ይታወቃል። በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ውስጥ ደግሞ አንድ የሩሲያ አውሮፕላን ከሻርም አል ሼክ የመዝናኚያ ቦታ ተነስቶ ወደ ሩሲያ ሲበር በሲና በረሃ በፈንጅ በመመታቱ አውሮፕላን ተሰባብሮ በውስጡ የነበሩ 224 ሰዎች በሙሉ መሞታቸው ይታወሳል።
 ብሩንዲ ውስጥ የሚታየወን የእርስ በርስ ግጭት ለማብረድ አንድ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ኃይል ወደ ብሩንዲ እንዲሄድ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተቀነቀነ ያለውን ሀሳብ የአፍሪካ ኅበረት የሚደግፍ መሆኑን የሰብአዊ መብት ዘገባ ገልጿል። ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የጸጥታ ካውንስል አለም አቀፍ ወታደራዊ ኃይል ወደ ብሩንዲ እንዲላክ የወሰነውን ውሳኔ የብሩንዲ መንግስት በጽኑ በመቃወሙ ምክንያት የአፍረካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ የሰረዘው መሆኑ ይታወሳል። የአፍሪካ ኅብረት የሰባአዊ መብት ዘገባ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ኃይል እንዲላክ የሚለውን ሀሳብ ያቀረበው ሙያተኞች በቅርቡ በብሩንዲ ተገኝተው መረጃዎችን ካሰባሰቡ በኋላ መሆኑ ታውቋል።
 ሕጻናት የአይምሮ በሸተኞች ሆነው እንዲወለዱ ያደርጋል የሚባለው ዚካ ቫይረስ በደቡባዊ አሜሪካ በተለይም በብራዚል ውስጥ በሰፊው መከሰቱ የዓለም አቀፍ ህብረተሰብን አሳስቦ የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ኬፕ ቬርድ ተብላ በምትጠራው በአፍሪካ ሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ደሴት ውስጥ የገባ መሆኑ በዚህ ሳምንት ተነገረ። እስካሁን ድረሰ በኬፕ ቬርዴ ደሰት 7000 በበሽታው የሚጠረጠሩ ሰዎች እንዳሉና ከእነዚህም ውስጥ 180 የሚሆኑ እርጉዝ ሰዎች እንደሆኑ በተጨማሪም ሶስት ሕጻናት የአይምሮ ጉዳተኛ ሆነው መወለዳቸውን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በሽታው ወደ አገራቸው እንዳይገባ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ድርጅቱ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።

No comments:

Post a Comment