Friday, May 27, 2016

የካርቱም ፖሊስ ኢትዮጵያውያንን እያሳደደ በማሰር ላይ ነው… Anteneh Yigzaw


የሱዳን መንግስት ፖሊሶች፣ በካርቱም የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከየመንገዱና ከየቤቱ እያደኑ በመኪኖች ላይ በመጫን በጅምላ ወደ እስር ቤት የመወርወር ዘመቻ ጀምረዋል፡፡
ፖሊስ ዋሃዱ አርባይን ወይም ሳኣፋ ዘለጥ እና ዴም በተባሉት የካርቱም ሰፈሮች በከፈተው ዘመቻ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሚገኙ፣ በካርቱም የሚገኙ የአይን እማኞች በላኩልኝ መረጃ ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ኢትዮጵያውያንን እያሳደደ በማሰር ላይ የሚገኘው፣ “ሚጣቃ” ወይም ጊዚያዊ የመኖሪያ ፈቃድ የላችሁም በሚል ሰሰብ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ስደተኞች ግን፣ ሚጣቃ ያላቸውና በህጋዊነት በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ናቸው – ብለውኛል የአይን እማኞቹ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ሚጣቃ እንዳላቸውና ህጋዊ እንደሆኑ ለፖሊሶቹ ለማስረዳትና ነጻ ለመሆን የሚችሉበት ዕድል የላቸውም – አፈሳው በጅምላ ነው፣ ሲሉም ገልጸውልኛል፡፡
በፎቶ ግራፉ ላይ የምታዩዋቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶችም፣ በአስተናጋጅነት ተቀጥረው ለረጅም ጊዜ ሲሰሩ ከቆዩበት አንድ የካርቱም ምግብ ቤት ውስጥ በድንገተኛው ዘመቻ የታፈሱ እንደሆኑ መረጃው ደርሶኛል፡፡
የሱዳን ፖሊስ ሰሞኑን 200 ያህል ኤርትራውያን ስደተኞችን ከየአካባቢው ለቅሞ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጠቆሙኝ የአይን እማኞች፣ ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ላይም ዘወትር ተመሳሳይ እርምጃ የሚወስድ ቢሆንም፣ የዛሬው ግን የተለየና ሰፋ ያለ ዘመቻ ነው ብለውኛል፡፡

No comments:

Post a Comment