የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ሦስት ሠራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት፣ 18,880,000 ብር ወጪ አድርገው ለሌሎች በማስተላለፍ የጥቅሙ ተካፋይ ሆነዋል ተብለው ተጠርጥረው ሚያዝያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተጠቀሰውን ገንዘብ ወጪ እንዲሆን ያደረጉት የባንኩ ደንበኛ ከሆነው ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ የባንክ ሒሳብ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩት አብዱራህማን አህመድ፣ ሊንዳ አስፋውና ዘካሪያስ ጥላሁን የተባሉ ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡ ከተጠቀሰው ድርጅት ሒሳብ ላይ ገንዘቡን ተቀናሽ በማድረግ ገቢ ያደረጉት ዎክላ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለተባለው ድርጅት መሆኑን፣ ድርጊቱን እያጣራው የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አሳውቋል፡፡
ዎክላ በሐሰተኛ ሰነድ የተቋቋመ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑን፣ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብርሃንና ሰላም ቅርንጫፍ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ ተቋማት ሒሳብ ላይ ተቀናሽ በማድረግ እነ ኃይለ ማርያም ቤጌናና እነ ድረስ አበበ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በድርጅቱ ስም ሒሳብ በመክፈት ገቢ አድርገውለታል የተባለ ድርጅት መሆኑን የምርመራ ዘርፉ አክሏል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ቀሪ ምርመራ እንዳለው በማሳወቅ ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ምርምራ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዶ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ለግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
No comments:
Post a Comment