[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ ስልክ ደወለላቸው]
- ሄሎ ዳዲ፡፡
- አቤት ጐረምሳው፡፡
- በሚቀጥለው ሳምንት ከከተማ እወጣለሁ፡፡
- የት ልትሄድ ነው ደግሞ?
- ወደ ላንጋኖ እሄዳለሁ፡፡
- እና ምን ፈልገህ ነው?
- ቪ8 እንድትሰጠኝ ነው፡፡
- እኔስ ምን እይዛለሁ?
- ቤት አዲስ ሜርሴዲስ አለ አይደል እንዴ?
- ልጄ እሱን አንተ ይዘኸው ብትሄድ ይሻላል፡፡
- አይ ከከተማ ስለምወጣ ቪ8ቱ ይሻላል ብዬ ነው?
- ቢሆንም ሜርሴዲሱ ለእኔ ጥሩ አይደለም፡፡
- እንዴ የ2016 ሞዴል ነው እኮ ዳዲ?
- ለዚያ እኮ ነው ልጄ፡፡
- እንዴት ማለት ዳዲ?
- ዓይን ውስጥ ያስገባኛል፡፡
- አልገባኝም ዳዲ፡፡
- ያው እሱን ይዤ ስንቀሳቀስ ብዙ ሀብት እንዳለኝ ሰዎች ያውቃሉ፡፡
- ምን ችግር አለው?
- ችግር አለው፡፡
- ይኸው ትልቅ ፋብሪካ አለን አይደል እንዴ?
- እ…
- ደግሞ አዲሱ ሆቴላችን ከተማችን መሀል አይደል እንዴ ያለው?
- ለሰው ሆቴል አለን እያልክ ታወራለህ እንዴ?
- ጓደኞቼ መቼ ነው እናንተ ሆቴል መጥተን የምናድረው ይሉኛል እኮ?
- አንተም የእኛ ነው እያልክ ታወራለህ?
- ጓደኞቼ በየቦታው ሕንፃ አላቸው እኮ፤ ምን ችግር አለው?
- ትልቅ ችግር አለው፡፡
- እሺ አሁን መኪናውን ምን ላድርግ?
- በቃ ሌላ ቪ8 ተከራይ፡፡
- መቼም በየወሩ ከምትሰጠኝ 20 ሺሕ ብር ተቆራጭ ላይ ክፈል አትለኝም?
- ተከራይና ቢሮ ላከው፡፡
- ምኑን?
- ቢሉን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ የፋይናንስ ኃላፊው የቪ8 መኪና የኪራይ ቢልና ሌሎች ቢሎችን ይዞ ቢሯቸው ገባ]
- ክቡር ሚኒስትር መኪና ተከራዩ እንዴ?
- የምን መኪና?
- ይኸው የቪ8 የመኪና ኪራይ ቢል መጥቶልኝ ነው፡፡
- ለአንድ ሳምንት ቪ8 ፈልጌ ነው፡፡
- የእርስዎ ቪ8 ምን ሆነ?
- ለልጄ ነው የፈለግኩት፡፡
- ታዲያ ሒሳቡን ማን ነው የሚከፍለው?
- መሥሪያ ቤቱ ነዋ፤ ደግሞ ስለዚህም እኔ እንዳስብ ትፈልጋለህ?
- ያው ክቡር ሚኒስትር …
- ስማ ዝም ብለህ ሒሳቡን ክፈል፡፡
- ሌላም ቢል መጥቶልኝ ነበር፡፡
- ምንድን ነው እሱ?
- ከላውንደሪ ቤት የ15 ሺሕ ብር ሒሳብ እንዲከፈል የሚል ነው፡፡
- መክፈል ነዋ እሱንም፡፡
- ማለቴ ምን አሳጥበው ነው ብዬ ነው?
- ስማ ሸሚዝ እኮ በየቀኑ ነው የምቀይረው፡፡
- ኧረ በቀን ሦስቴ ራሱ ቢቀይሩ ይኼን ያህል ሊመጣ አይችልም፡፡
- እንዴ የቤተሰቤም ልብስ እኮ እዚያ ነው የሚታጠበው?
- ክቡር ሚኒስትር ባለፈው እኮ ሁለት የልብስ ማጠቢያ ማሽን ተገዝቶልዎታል፡፡
- አጣቢ ሰው አጣኋ?
- እንዴ አራት የቤት ሠራተኞች እኮ ነው የቀጠርንልዎት?
- ገና ሌላ ለመጨመር እያሰብኩ ነው፡፡
- ምን ሊያደርጉልዎት?
- በቃ የመንግሥት ፖሊሲ እኮ የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡
- ግን ሌላው የገረመኝ የጫማ ማስጠረጊያ ተብሎ የመጣው ሁለት ሺሕ ብር ነው፡፡
- ውይ ያ ምስኪን ሁለት ሺሕ ብር ክፈሉኝ አለ?
- ያላችሁበትን ክፍለ ከተማ ነዋሪ ጫማ ጠርጐ ነው ሁለት ሺሕ ብር ክፈሉኝ ያለው?
- ምን አሁን ሁለት ሺሕ ብር ገንዘብ ናት ብለህ ነው?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ስንት ኢትዮጵያዊ ደመወዙ ሁለት ሺሕ ብር አይሞላም እኮ?
- ኢትዮጵያውያን ግን ምትሃተኞች ናቸው ልበል?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት ነው በሁለት ሺሕ ብር ከወር እስከ ወር የሚኖሩት?
- ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር እነዚህ ክፍያዎች ሊያስጠይቁን ይችላሉ፡፡
- በማን ነው የሚያስጠይቀን?
- በኦዲተሮቹ፡፡
- እኔ ምላሽ እሰጣቸዋለሁ፡፡
- ምን ሊሏቸው?
- ሚኒስትር ነኝ!
[የክቡር ሚኒስትር ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- ባለጉዳይ አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ባለጉዳይ?
- ኧረ ይኸው ስንት ወራት ሙሉ ነው የተመላለሰው?
- ስንቶች ለዓመታት ተመላልሰዋል አይደል እንዴ? ይኼ አዲስ ነገር መሆኑ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ይኼኛው ግን ትንሽ ያሳዝናል፡፡
- ምኑ ነው የሚያሳዝነው?
- ዕንባውን እያፈሰሰ ነው፡፡
- እና እኔ ዕንባ ጠባቂ ነኝ?
- ታዲያ ዕንባ አስፈሳሽ ነዎት?
- ወሬኛ፣ አስገቢው በይ፡፡
[ባለጉዳዩ እያለቀሰ ቢሯቸው ገባ]
- ምን ሆነሃል?
- ክቡር ሚኒስትር ያልሆንኩት ምን አለ?
- እስቲ ንገረኝ፡፡
- ከውጭ ነው የመጣሁት፡፡
- ኒዮሊብራሊስት ነህ?
- ኧረ ኢንቨስት ላደርግ ነው የመጣሁት፡፡
- ምንድን ነው ኢንቨስት ያደረግከው?
- ይኸው ፋብሪካ ለመክፈት አስቤ ነው አገሬ የገባሁት፡፡
- እና ምን ተፈጠረ?
- ቦታ ተረክቤ፣ ማሽኖች ገዝቼ ሥራ ልጀምር ነበር፡፡
- ታዲያ ለምን አትጀምርም?
- ይኸው ቦታዬ ሊወሰድብኝ ነው፡፡
- ለምንድን ነው የሚወሰድብህ?
- ለባለይዞታዎቹ ካሳ አልከፈልክም ተብዬ፡፡
- ካሳ መንግሥት አይደል እንዴ የሚከፍለው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔም እሱን ብዬ ያልደረስኩበት ቦታ የለም፡፡ እእእ…
- ኧረ አታልቅስ፣ ዘመድ ሞቶብሃል እንዴ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማን ነው የሞተብህ?
- ፍትሕ፡፡
- ፍትሕማ አልሞተም፡፡
- እንዴት አልሞተም?
- ባለፈው ሳምንት ሲከበር ነበር፡፡
- ምንድን ነው የተከበረው?
- የፍትሕ ሳምንት!
[የክቡር ሚኒስትሩ የቢዝነስ ፓርትነር ስልክ ደወለላቸው]
- ክቡር ሚኒስትር ሰሙ እንዴ?
- ምኑን ነው የምሰማው?
- ከተማው ውስጥ የሚወራውን ነዋ፡፡
- ምንድን ነው የሚወራው?
- ወደብ ላይ ያለው ዕቃችን ሊወረስ ነው፡፡
- ምናለ ልንወርስ ነው ብለህ ብታወራ?
- ቢሆንማ ደስ ይለኛል፡፡
- ከወር በፊት ያመጣናቸው አምስት ኮንቴይነሮች ሊወረሱ ነው እያልከኝ ነው?
- አይ እሱ ሳይሆን እዚህ ደረቅ ወደብ ላይ ያሉት ሦስት ኮንቴይነሮች፡፡
- ለምንድን ነው የሚወረሱት?
- ከስድስት ወራት በላይ የቆዩ ኮንቴይነሮች ሊወረሱ ነው እየተባለ ነው፡፡
- ስማ እኛ እኮ ኮንቴይነሮቹን ዓመት ያቆየናቸው በመንግሥት ችግር ነው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- መሥሪያ ቤታችን ሙሉ የቢሮ ዕቃ ይቀይራል ብለን አስበን ነው ዕቃዎቹን ወደ አገር ውስጥ ያስገባነው፡፡
- የለም የለም፣ የመሥሪያ ቤታችሁ ሙሉ የቢሮ ዕቃ መቀየር አለበት ብለን አስበን ነበር ያስገባነው፡፡
- ምን ፀጉር ትሰነጥቃለህ? ያው ነው፡፡
- እና ምን ይሻላል?
- ስማ እኔ እወርሳለሁ እንጂ…
- እ…
- አላስወርስም!
[አንድ ባለሀብት ክቡር ሚኒስትሩ ጋ ደወለ]
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ምን ይሻለኛል?
- የሚሻልህንማ አንተ ታውቃለህ፡፡
- ዕቃዬ እኮ ሊወረስብኝ ነው፡፡
- ከወደቡ ላይ በጊዜ ማንሳት ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ክፍያ አለቅ ብሎኝ ነው ዕቃውን ማውጣት ያቃተኝ?
- መጀመሪያውኑ መንግሥትን ተማምነህ ማን ዕቃ ጫን አለህ?
- እንዴ የመንግሥትን ጨረታ አሸንፌ እኮ ነው?
- አስገባ ሲልህ ነበራ ማስገባት የነበረብህ?
- እና ምን ይሻላል?
- መንግሥት ከሚወርስብህ…
- ምን ሊሉኝ ነው?
- እኔ ልውረስብህ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]
- እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በአምላክህ እንዳልልህ፣ አምላክህ ገንዘብ ነው አንተ፡፡
- በገንዘብህ በሉኛ?
- እሺ በቪላህ፣ በፎቅህ፣ በመሬትህ፣ በሆቴልህ፡፡
- ለማንኛውም የምሥራች፡፡
- ምሥር ብላ ነው የሚባለው?
- ምን በወጣኝ? ባይሆን ስቴክ ብላ በሉኝ፡፡
- በል ኮንቴይነር ብላ፡፡
- አሜን ክቡር ሚኒስትር፣ ኧረ መርከብ ሙሉ ኮንቴይነር ብላ በሉኝ፡፡
- ለመሆኑ ምን ተገኝቶ ነው?
- በኢትዮጵያ የሚሊየነሮች ቁጥር በ130 ፐርሰንት ጨመረ እኮ፡፡
- ሌት ተቀን የምንሠራው ለምን ይመስልሃል?
- ባለፈው እኔና እርስዎ ብቻ በዚህ ሊስት ውስጥ መካተታችን ትንሽ ቅር አሰኝቶኝ ነበር፡፡
- ምን ነካህ? በአሁኑ ከእኔ ቤተሰብ ብቻ እዚህ ሊስት ውስጥ የገባነው በትንሹ ወደ 20 እንደርሳለን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በእኔም በኩል ወንድሞቼ፣ አክስቶቼ፣ ልጆቼና ሚስቴ ተጨምረው አሥር ደርሰናል፡፡
- ገና ከዚህም ባለፈ ማደግ አለብን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በሚቀጥለውማ ይኼ ዕድገት ወደ ገጠሩ ክፍልም ማስገባት አለብን፡፡
- ገጠር ስትል?
- ገጠር ያሉት ዘመዶቻችንም በዚህ የሚሊየነሮች ሊስት ውስጥ መካተት አለባቸው፡፡
- እኔማ ከዚህም ያለፈና የተለጠጠ ዕቅድ ነው ያለኝ፡፡
- ምን ዓይነት የተለጠጠ ዕቅድ?
- እኛ ራሳችን ከሚሊየነሮች ሊስት ውስጥ ወጥተን ሌላኛውን ሊስት መቀላቀል አለብን፡፡
- የትኛውን ሊስት?
- የቢሊየነሮቹን!
- Reporter Amharic
No comments:
Post a Comment