Wednesday, May 11, 2016

ምዕራብ ዕዝ የታገቱ ሕፃናትን ለማስለቀቅ ኃይል ተመራጭ አይደለም አለ


የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በገቡ የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የታገቱ 125 ሕፃናትን የማስለቀቅ ሒደት ከወታደራዊ ኃይል ይልቅ በድርድር ማስለቀቅ ተመራጭ መሆኑን፣ የመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ማዘዣ አስታወቀ፡፡ ታጣቂዎቹም አግተው ከወሰዷቸው ሕፃናት መካከል 19 ያህሉ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የመከላከያ ሠራዊትና የጋምቤላ ክልል በጋራ አስታውቀዋል፡፡
ሕፃናቱንና የቀንድ ከብቶችን ለማስለቀቅ ኃይል መጠቀም ጉዳቱ የሚያመዝንና የሕፃናቱንም ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ፣ በመከላከያ ሠራዊት ተመራጭ ስትራቴጂ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ሕፃናቱ ታግተው በተወሰዱ በ24ኛው ቀን 19 ሕፃናትን አገራቸው በመመለስ፣ ለጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ማስረከቡ ታውቋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ሙርሌ ታጣቂዎች ለተፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት አፀፋዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ግዳጅ የተሰጠው ምዕራብ ዕዝ ኦፕሬሽኑን ለመጀመር ዝግጅቱን ባጠናቀቀበት ወቅት፣ የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ከሙርሌ ጎሳ ሽማግሌዎች ጋር በመምከር ሕፃናቱ እንዲለቀቁ ተፅዕኖ መፍጠራቸው ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የተቀሩ ታጋቾችንና የተዘረፉ ከብቶችን ለማስመለስ ደቡብ ሱዳን ገብቷል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኰንኖች ከደቡብ ሱዳን ከፍተኛ መኰንኖች ጋር ጋምቤላ ከተማ በመገኘት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ከሥፍራው የደረሰ መረጃ ያመለክታል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ታግተው ተወስደው ከነበሩት ሕፃናት መካከል የተወሰኑት ወደ አገር ቤት መግባታቸውንና የተቀሩትም በቅርቡ እንደሚገቡ ያላቸውን እምነት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት የታገቱ ሕፃናትን ይዞ ጋምቤላ በደረሰበት ወቅት በተደረገው አቀባበል የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍስሐ ኪዳኑ እንደተናገሩት፣ መከላከያ ሠራዊት የታገቱት ሕፃናት ባሉባቸው ቦታዎች ደርሶ ኦፕሬሽኑን ለመጀመር ዝግጁ ሆኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ከኃይል ዕርምጃ ይልቅ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የደቡብ ሱዳን መንግሥት በጠየቀው መሠረት ድርድር ተደርጎ ሕፃናቱ ሊለቀቁ ችለዋል ብለዋል፡፡
‹‹የተቀሩት ታጋች ሕፃናትንና የተዘረፉትን የቀንድ ከብቶች ለማስለቀቅ የተጀመረው ጥረት ይቀጥላል፤›› በማለት ሜጀር ጄኔራል ፍስሐ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ሌተና ጄኔራል ዴቪድ ያውያው የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም አጠናክረዋል፡፡ ሌተና ጄኔራል ዴቪድ እንደተናገሩት፣ ሕፃናቱን የማስለቀቁ ተግባር የመጀመርያው ምዕራፍ እንጂ ማጠቃለያ አይደለም፡፡
የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል አሰቃቂ ጭፍጨፋ በመፈጸም ከ200 በላይ ዜጎችን ሲገድሉ፣ 125 ሕፃናትና ከሁለት ሺሕ በላይ የቀንድ ከብት ይዘው መሄዳቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያውያኑን በጨፈጨፉት ሙርሌዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ እስካሁን በግልጽ ባይነገርም፣ የተወሰዱትን ሕፃናትና የቀንድ ከብቶችን ለማስመለስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው

No comments:

Post a Comment