በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመጣል ላይ በሚገኘው ከባድ ዝናብ ምክንያት የተፈጠረው ጎርፍ የሰው ሕይወት ከመቅጠፍ በተጨማሪ፣ በማሳ ላይ የሚገኙ ሰብሎችና የመንገድ አውታሮች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ እየገለጸ ነው፡፡
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በቀናት ልዩነት ለሰዓታት ሳያቋርጥ የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ከሰው ሕይወት በተጨማሪ በርካታ የቤት እንስሳት፣ ከ560 ሔክታር በላይ በሆነ ማሳ ላይ የሚገኝ ሰብል መውደሙ ተገልጿል፡፡ ይህ ጎርፍ ከሮቤ ወደ ጎሮ የሚወስደውን መንገድ በመስበሩ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተገቷል፡፡
በምሥራቅ ሐረርጌ የጣለው ዝናብ ደግሞ የሁለት ሕፃናትን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ከድሬዳዋ ወደ ሐረር የሚወስደውን መንገድ መስበሩ ተገልጿል፡፡
በምዕራብ አርሲ የጣለው ከባድ ዝናብ ወደ ወላይታ በሚወስደው መንገድ ላይ ከፍተኛ መሰንጠቅ አስከትሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ 18 ሜትር ርዝመትና ሦስት ሜትር ስፋት ያለው የመሬት መሰንጠቅ አስከትሏል፡፡
አቶ ሳምሶን እንዳሉት ክስተቱ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲገታ በማድረጉ፣ ባለሥልጣኑ ተለዋጭ መንገድ ቢያዘጋጁም ተለዋጭ መንገዱም በጎርፍ እየተመታ በመሆኑ ጉዳዩን ውስብስብ እንዳደረገው አመልክተዋል፡፡
ከሞጆ ወደ ሐዋሳ በሚወስደው መንገድ መቂ አካባቢ የጣለው ከፍተኛ ዝናብም መንገዱን ከባድ ደለል በማልበሱ የትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ እንከን መፈጠሩ ተመልክቷል፡፡
ከዚህ ባሻገርም አሰላ ከተማን የመታው ጎርፍ የከተማውን መንገዶች መሰባበሩ ተገልጿል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ በአፋር፣ በሰሜን ሸዋ (ሸዋ ሮቢት) ስልጤ ዞን፣ ጂግጂጋ፣ ድሬዳዋ፣ አርባ ምንጭ፣ ደቡብ ወሎና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ የብሔራዊ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እየጣለ ባለው ከፍተኛ ጎርፍ ምክንያት እየተከሰተ ያለው ጎርፍ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በብሔራዊ ደረጃ ዕቅድ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሦስት የተፋሰስ ባለሥልጣንና ሁለት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያሉበት የተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤት ሚያዚያ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጠው ትንበያ፣ በአገሪቱ 400 ሺሕ ዜጎች በጎርፍ ጉዳት እንደሚደርስባቸው፣ 180 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያቸው እንደሚፈናቀሉ ገምቷል፡፡
አቶ ምትኩ እንደሚሉት
የችግሩ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች 200 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እየተሠራጩ ነው፡፡
Reporter Amharic
No comments:
Post a Comment