Monday, May 2, 2016

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በትራፊክ አደጋ 2,978 ሰዎች ሞተዋል::ከ564 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ወድሟል May 2, 2016

Contact us: eramharic@googlegroups.com
ቆንጅት ስጦታው Comments ↓
በየዓመቱ አሳሳቢነቱ እየጨመረ የመጣው የትራፊክ አደጋ በዚህ ዓመት የከፋ መሆኑን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የሟቾች ቁጥር 2,978 መድረሱን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ በንብረትም በ ኩል ያደረሰው ጉዳት እየጨመረ የመጣ መሆኑን፣ በተመሳሳይ ወቅት ግምቱ ከ564 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰም ተገልጿል፡፡
በባለሥልጣኑ የትራፊክ ደኅንነትና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስሜ በላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው የውይይት መድረክ ላይ ለባለድርሻ አካላት ባቀረቡት ሪፖርት፣ በበጀት ዓመቱ የትራፊክ አደጋ ያስከተለው የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ገር ሲነፃፀር ‹‹እጅግ አስደንጋጭ›› መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በዘጠኝ ወራት ብቻ የተከሰተው የሞት አደጋ አምና ከነበረበት በ11 በመቶ በመጨመሩ የ2,978 ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ጊዜ ውስጥ አደጋው በ4,898 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ሲያስከትል አምና በተመሳሳይ ወቅት የነበረው 3,966 እንደነበር፣ ዘንድሮ 5,110 ቀላል ጉዳት ሲመዘገብ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የነበረው ጉዳት 4,581 እንደነበርም አቶ ስሜ ጠቁመዋል፡፡ የንብረት ጉዳቱም ቢሆን አምና ተመዝግቦ ከነበረው 509 ሚሊዮን ብር ዘንድሮ በተመሳሳይ ወቅት የተመዘገበው የ60 ሚሊዮን ብር ጭማሪ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ለአደጋው መከሰት ምክንያቶች ያሏቸውን በርከት ያሉ ጉዳዮች የዘረዘሩት አቶ ስሜ፣ ጠቅለል ያለው ችግር ከአሽከርካሪዎች፣ ከተሽከርካሪዎች፣ ከሥልጠና እንዲሁም ከሕግ አስፈጻሚ ባለሙያዎች ጋር እንደሚያያዝ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የትራፊክ አደጋ በአገሪቱ ላይ የተደቀነ ትልቅ ፈተና እየሆነ በመምጣቱ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ሁላችንም ልንፈትሽ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
በአሽከርካሪዎች በኩል ከልክ ያለፈ ፍጥነት አንዱ ችግር መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህ ደግሞ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ዋና ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
ከዕቃ አስጫኝ ነጋዴዎች መካከል አሽከርካሪዎች በፍጥነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲደርሱ ጉርሻ የሚያዘጋጁ እንዳሉም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በትራፊኮች በኩል አሉ ያሏቸውን ችግሮች፣ ‹‹ከትራፊክ ፖሊሶች መካከል ሕግ የሚጥሱ አሽከርካሪዎችን ከማስተማር ይልቅ ለመቅጣት አቅደው የሚወጡ አሉ፤›› ብለዋል፡፡
ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮችና ተሳታፊዎችም አስተያየቶች አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን በብዛት ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ከብቃት ማረጋገጫና ከሥልጠና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከቱ የቀረቡት አስተያየቶች አመዝነው ታይተዋል፡፡
‹‹ማንኛውም ሠልጣኝ የሚፈልገውን የመንጃ ፈቃድ ደረጃ በቀላሉ ይወስዳል፡፡ እርከኑን አይጠብቅም፡፡ አንድ ሠልጣኝ በቀጥታ የተሳቢ መኪና መንጃ ፈቃድ የሚወስድበት አገር ነው ያለን፡፡ ይህ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱ እስካልተቀየረ ድረስ በየጊዜው የከፋ ችግር መታየቱ አይቀርም፤›› ሲሉ አንድ ተሳታፊ ገልጸዋል፡፡ እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹አሽከርካሪ ከተሽከርካሪ ጋር አብሮ ማደግ አለበት፤›› ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
የውይይቱ ሌላ ተሳታፊ በበኩላቸው ተተኪ አሽከርካሪዎችን በመቅጠር እንዲለማመዱ አለማድረግ ሌላው ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡
‹‹አንድ አሽከርካሪ ከጂቡቲ አዲስ አበባ ያለረዳት 22 ጎማ ያለው መኪና የሚያሽከረክርበት ልማድ ነው ያለን፤›› በማለት መፍትሔ መፈለግ ይገባል ብለዋል፡፡
ማሠልጠኛ ተቋማት ውስጥ ባረጁና ደረጃቸውን ባልጠበቁ መኪናዎች የሠለጠኑ አሽከርካሪዎች፣ አዲስ መኪና ላይ ተንጠልጥለው መሪ በመጨበጥ የሚያሽከረክሩበት አሠራር በራሱ አደጋ እየፈጠረ መምጣቱንም አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published.

7 + = 13

No comments:

Post a Comment