Wednesday, May 4, 2016

ከሊማሊሞ እስከ ሽሬ – Muluken Tesfaw


ከሊማሊሞ እስከ ሽሬ  Muluken Tesfaw

ሁለት ብርድ ልብስ ለብሼ ባድርም የደባርቅ ብርድ የሚቻል አልነበረም፡፡ በጠዋት ተነስቼ ወደ አውቶቡስ መናኻሪያ ሔድኩ፡፡ መናኻሪያ አካባቢ የማየው ሁሉ ወፍራም ጋቢ ወይም ፎጣ የለበሰ ነው፡፡ ጋቢ አልነበረኝም፤ ቢሆንም ወፍራም ጃኬት ለብሻለሁ፡፡ አውቶቡስ ተራ ስሔድ የአዲ አረቃይ መኪና እንደማገኝ ተስፋ አድርጌ ነው፡፡ ከጎንደር የሚነሳውን የሽሬ መኪና አዲ አረቃይ ወይም ጠለምት ጠብቄው በጊዜ ተከዜን ለመሻገር ነበር ሐሳቤ፡፡ ነገር ግን አውቶቡስ ተራ ስገባ ‹‹ሽሬ መሔድ ከፈለግክ መኪና አለ›› አለኝ አንድ ጋቢ የተጠቀለለ ደላላ፡፡ ሲናገር ካፉ ነጭ ትንፋሸ ይወጣል፡፡ ብርድ ሲሆን የተለመደ ነው፤ ከእኔም ጋር ይኖራል፡፡
ደላላውን ተከትዬ ስሔድ አንዲት ዳብል ጋቢና ፒክ አፕ ጀርባ 140 ብር ከፍየ እንድገባ ተነገረኝ፡፡ መኪናዋ የመጣችሁ ከአዲስ አበባ እኔ የማላውቀው የፌደራል መሥሪያ ቤት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ‹‹ኢት›› የሚል አራት ቁጥር ታርጋ አላት፡፡ አለቃቸው ጋቢና ከሾፌሩ ጋር አለ፡፡ አንደኛው ሠራተኛ ከእኔና አንድ ሌላ ሰው ጋር ለሦስት ከጀርባ ተጋራን፡፡ በአጋጣሚ ይሁን በሌላ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ አሁን አሁን ትግሬዎችን ሁሉ በጥርጣሬ ስለምንመለከት ‹‹ለእኔ የተላኩ ሰዎች ይሆኑ እንዴ?›› ብዬ ብጠራጠርም አብሮ ከመጓዝ ውጭ አማራጭ አልነበረኝም፡፡
የሊማሊሞን ደገል ተያያዝነው፡፡ ወሬ የለም፤ የትግርኛ ሙዚቃ ብቻ ተከፍቷል፡፡ የሊማሊሞ ገደል ባገራችን ካሉት አስፈሪና አስጨናቂ መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከአዲስ አበባና ከመሀል አገር መኪና እየነዱ የሚመጡ ሾፌሮች ደባርቅ ላይ ሲደርሱ ሾፌር በአበል ቀጥረው ነው ዛሪማ ድረስ የሚያደርስላቸው፡፡ የሊማሊሞ ገደል አስፓልት አይደለም፡፡ የገደሉ ክፋት መጨረሻው በደንብ አይታወቅም፡፡ የመኪና መገልበጥ አደጋ ቢደርስ በትክክል መጨረሻው የት እንደሆነ አይታይም፡፡ ግን የሚገርመው ሊማ ሊሞ ገደል አደጋ ብዙ ጊዜ አይደርስም፡፡ የገደሉ መንገድ የተሠራው በጣሊያኖች ሲሆን የገደሉ ስያሜም የተገኘው ዲዛይኑን ባዘጋጀው ሊማሊም በተባለ ግለሰብ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ገደሉ መካከል ላይ ላይ ትንሽ ግንብ ቤት ነገር አለች፡፡ የመሀንዲሱ መቃብር ነች አሉ፤ አብረው የነበሩት ጓዶች፡፡ ከደባርቅ ዛሪማ እስከምንደርስ ድረስ ገደል ነው የወረድነው፡፡ ደባርቅ ከባህር ወለል በላይ 2235 ሜትር ሲሆን ዛሪማ ግን ከአንድ ሺህ ሜትር በታች ነው፤ በትንሹ ከ1300 ሜትር ያላነሰ ርዝመት ወደ መሬት ስምጥ ገብተናል ማለት ነው፡፡
የሊማሊሞን ገደል ልንጨርስ ስንል ‹ድብ ባህር›› የተባለች መንደር አለች፡፡ የሚገርም ነው ድብ ባህር በታች እያሉ ዘፋኞች ሁሉ የሚቀኙላት መንደር ይህች አትመስለኝም ነበር፡፡ ድብ ባህር ለምን ስያሜዋን እንዳገኘች አላውቅም፤ ግን ምንም አይነት ባህርም ሆነ ውሃ አካል የለም፡፡ ገደሉን ስንጨርስ ‹‹ዛሪማ›› ከተማና ወንዝ እናገኛለን፡፡ የዛሪማን ወንዝ ስንሻገር ከኋላ የተቀመጠው ሰው አንደኛው ‹‹ወደ ትግራይ ክልል ገባን›› አለ፡፡ ከዚህ በኋላ አዲ አረቃይ የሚባል ወረዳ የአማራ ክልል ስላለ ወደ ትግራይ ክልል የገባን አልመሰለኝም በማለት በትህትና ለመጀመሪያ ጊዜ ተነፈስኩ፡፡ በእርግጠኛነት ወደ ትግራይ ክልል እንደገባን አወራልን፤ ሆን ብሎ ለማናገር ይሁን የማያውቀው ሆኖ መገመት አልቻልኩም፡፡ ጉንጭ አልፋ ንግግር መሆኑን ሳውቅ ዝም አልኩ፡፡
አዲ አረቃይ ቁርስ ስንበላ የአማራ ክልል መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ ከእኛ ጋር ከኋላ የተቀመወጠው ሰው ሲያወራ ፈጠን ይላል፡፡ እኔ መጫወቱን ሳልፈልገው ቀርቼ ሳይሆን ሥርዓታችን በሰዎች መካከል የፈጠረው ያለመተማመን ስሜት ስላለ ዝም ማለትን መርጫለሁ፡፡ አዲ አረቃይ ላይ ሆነን ወደ ደባርቅ አቅጣጫ ስንመለከት ወደ እምብርተ መሬት የሰጠምን ያክል ይሰማናል፡፡ አንድ ቀን አዲ አረቃይ ባድር ዙሪያዋን የከበቧት አምባዎችና ገደላ ገደሎች ተንደው የሚያጠፏት ስለሚመስለኝ እንቅልፍ አይወስደኝም፡፡ አዲ አረቃይን ከሦስት ዓመት በፊት አውቃታለሁ፡፡ ያኔ የወልቃይት የስኳር ፕሮጀክት የዋልድባ ገዳምን አደጋ ጥሎታል በተባለ ጊዜ ገዳሙን ለማየት ሒጄ ነበር፡፡ ደርሶ መልስ ለሰላሳ ስድስት ሰዓታት ያክል በእግሬ ተጉዣለሁ፡፡ የአርማ ደጋ በርሃን አቆራርጨዋለሁ፡፡ ወደ ገደሉ ቀና ስል የአስግዲት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ታየኝ፡፡ ከዋልድባ እንደተመለስን የአዲ አረቃይ ወጣቶች እግሬን ያጠቡኝ አስግዲት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ የአዳርቃይ ከተማ ከሦስት ዓመት በፊት የማውቃት ናት፡፡ የተለየው ነገር መንገዱ አስፓልት ነው፡፡ ከጎንደር ስንመጣ እስከ ደባርቅ ድረስ ከሽሬ ስንመጣ ደግሞ አስከ ዛሪማ ድረስ የአስፓልት መንገድ አለ፡፡ የሊማሊሞ ነገር ግን መላ የተበጀለት አይመስልም፡፡ ጣሊያን ከ70ና 80 ዓመት በፊት የሠራችውን መንገድ በዚህ ዘመን ማደስ አለመቻላችን በዕውነት የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ የቴክኖሎጂያችን እድገትና ምጥቀት አልፎ አልፎ ጠጠርና አሸዋ ከመድፋት የዘለለ አልሆነም፡፡
ባለ መኪናዎቹ ምን እንደሚሰሩ ባላውቅም በምናገኛቸው ወረዳዎች ሁሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየገቡ ትንሽ ትንሽ ጊዜ ያባክናሉ፡፡ ከአዲ አረቃይ ሦስት ሰዓት ተኩል ሲሆን ወደ ጠለምት ጉዞ ጀመርን፡፡ ጠለምት በቀድሞው የጎንደር ክፍለ አገር በአሁኑ የትግራይ ክልል ሥር የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ከወልቃይት ጠገዴ ጋር የአማራ የማንነት ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዷ የጠለምት ወረዳ ናት፡፡ ጠለምት የንግድ ተቋማት ማስታዎቂያዎች በሙሉ በትግርኛ የተጻፉ ናቸው፡፡ ብዙ ሰው የሚያወራው ትግርኛ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ከአዲ አረቃይ ድረስ ያለው ርቀት በጣም ቅርብ ነው፡፡
የአማራ የማንነት ጥያቄ የሚያነሳ ማኅበረሰብ ግን ደግሞ የአማራ ማንነት የሌለው ሲሆን ግራ ተጋባሁ፡፡ ሆኖም ግራ መጋባቴን ለማጥራት ግማሽ ሰዓት ብቻ በቂዬ ነበር፡፡ ጠለምት የኤርትራውያን ስደተኞች መኖሪያ ናት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኛ ማቆያ ካምፕ ሠርቶባታል፡፡ የስደተኞች ካምፕ በግምት ከከተማው አምስት ኪሎ ሜትር ያክል ይርቃል፡፡ ሁሉም ስደተኞች ትግርኛ ተናጋሪ ኤርትራውያን ናቸው፡፡ ጠለምት ከትግራይ ክልል የመጨረሻው ሩቁ ቦታ ሲሆን የስደተኞች ካምፕ እነ ሽሬን፣ አደዋንና አክሱም ከተሞችን አልፎ ጠለምት ላይ ለምን እንደተቋቋመ የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡ ኤርትራውያኑ ትግርኛ ተናጋሪ ስለሆኑ አማርኛ የሚያዘወትረውን የጠለምት ሕዝብ ላይ የቋንቋ የበላይነትን ለማሳደር ነው፡፡ ስለዚህ የጠለምት ትግሬ ትግሬ መሽተት ግልጽ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መንደር በስፋት ማይጸብሪን ያስከነዳታል፤ ይበልጣል፡፡ የስደተኞች ብዛትና የከተማዋ ነዋሪ ብዛትም የሚነጻጸር አይመስለኝም፡፡
ገንዘብ ከፍለን የምንጓዘው ሰዎች ቡና እየጠጣን ቁጭ አልን፡፡ ባለ መኪናዎቻችን ለግማሽ ሰዓት ከቆዩ በኋላ መጡ፡፡ ወደ ተከዜ ጉዞ ጀመር፡፡ ጠለምትን ጨርሰን ገደሉ ጫፍ ስንደርስ የተከዜ ወንዝ ተኝቶ ታየን፡፡ ገደሉ የአባይ በርሃን ይመሳሰላል፡፡ ጎሃ ጽዮን ወይም ደጀን ላይ ሆነን ወደ ታች አባይን ተኝቶ እንደምናየው አይነት፡፡ ከአባይ በሁለት ነገር ይለያል፡፡ የመጀመሪያው የጎርጁ የአባይን ያክል ትልቅ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ብዙም ልምላሜ የለውም፡፡ በጠለምት በኩል የገደሉ ጫፍ ላይ ሆነን ስንመለከት የተከዜ ወንዝ ማዶ ዳር ላይ ካለች ትንሽ መንደር ውጭ ሰው በርሃው ውስጥ አይኖርም፡፡ ወደ ታች ወረድን፡፡ ሙቀቱ ጨምሯል፡፡ የአማራና የትግራይ የተፈጥሮ ድንበር ከሆነው የተከዜ ወንዝ ደረስን፡፡ ወንዙ ላይ የተጋደመውን የብረት ድልድይ ተሻገርን፡፡ በሽሬ በኩል ወንዙ ዳር ትንሽዬ መንደር አለች፡፡ ውሃ ጠምቶን ስጡን አልናቸው፡፡ ሰጡን፤ ልንጠጣው ስንል ግን ከተከዜ ወንዝ የተቀዳ መሆኑን ነገሩን፡፡ ይህ ወንዝ ሰዎች ይዋኙበታል፤ ልብሳቸውን ያጥቡበታል፤ ዓሳ ያሰግሩበታል፤ እንስሳት ይጠጡታል፡፡ ስለዚህ እዚህ የተቀዳውን መጠጣት አደጋ አለው ብለን ተውነው፡፡ የምኒልክ ብርጭቆ እዚች መንደር የእርጎ መጠጫ ነው፡፡ እዚያ በርሃ ላይ አንድ ምኒልክ እርጎዬን ገለበጥኩ፡፡ ይህች መንደር ከነእርጎዋ እንደ በርሃ ገነት (ኦሲስ) ናት፡፡ የመንደሯ ነዋሪዎች አማርኛ ብዙ አይችሉም፡፡ መኪናዋ ውስጥ የነበርነው ሁላችንም እርጎ ጠጥተናል፡፡ ተከዜ ሲባል እርጎ ትዝ ይለኝ ይሆናል፡፡ መኪናችን ተነሳ፤ በርሃን ወጥተን እዳጋቡና የተባለች ከተማ ደረስን፡፡
ሽሬ እንደገባን ከባለ መኪናዎቹ ጋር ተለያየን፡፡ ስሜን አልያዙም፤ ስማቸውን አልያዝኩም፡፡ ስልኬን አልያዙም፤ ስልካቸውን አልያዝኩም፡፡ በዝምታ ጀምረን በዝምታ ጨረስን፡፡ የሽሬ ከተማ ትልቅና ዘመናዊ ከተማ ነው፡፡ መሃል ከተማው ተጋዳላይ ሐየሎም አርአያ ሬዲዮ ይዞ ተቀርጧል፡፡ ወደ ሽራሮና ኹመራ፣ ወደ ደደቢና እዳጋቡና፣ ወደ አክሱምና አድዋ በዚህ በኩል እለፉ እያለ ዛሬም ትእዛዝ የሚሰጥ ይመስላል፡፡ የሽሬ ከተማ አቀማመጡ ሜዳ ነው፤ ሕንፃዎቹ ዘመናዊ ናቸው፡፡ መንገዶቹም ጽዱና ማራኪ ናቸው፡፡ በዕውነት ከዚህን ያክል ርቀት በኋላ ይህን የመሠለ ውብ ከተማ አገኛለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ሽሬና አብዛኛው የትግራይ ከተሞች ወደ ፊት እንደምናየሁ የንግድ ድርጅቶች ማስታዎቂያዎች በሙሉ ማለት ይቻላል፤ በአማርኛ የተጻፉ ናቸው፡፡ ሕንፃዎቹ በሙሉ አማርኛን በደንብ ይናራሉ፡፡ ጠለምት ላይ ካለው እጅግ ተቃራኒ ነው፡፡
ከአዲረመጽ ወደ ወልቃይት ሊወስደኝ የሚችል ሰው እንዲመጣ አስቀድሜ አመቻችቼ ነበር፡፡ ከሽሬ አዲ ረመጽ ወደ 150 ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ አዲ ረመጽ የወልቃይት ወረዳ ዋና ከተማ ነው፡፡ ስያሜው ትግርኛ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹እሳት፣ የሚፋጅ፣ ረመጥ አገር›› ማለት ነው፡፡ በቀድሞው ዘመን የትግራይ ገዥ የነበረ ራስ ሐጎስ የተባለ ልዑል የተከዜ ወንዝን ተሻግሮ ወልቃይትን ይወራል፡፡ ራስ ገብረ ማርያም የተባለው የወልቃይት ልዑል ደግሞ በጊዜው ጠገዴ ነበር፡፡ ራስ ገብረ ማርያም ኃይሉን አሰባስቦ ልዑሉን ከነሠራዊቱ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ተከዜን አሻግረው ሲመለሱ አካባቢውን ራስ ጎሹ ለተባለ ሌላ ልዑል እንዲጠብቅ አደረጉ፡፡ በዚህም ‹‹ይህ የረመጥ አገር ነው›› ለማለት አዲረመጽ አሉት፤ ጦርነቱን በማስታወስ፡፡
ከወልቃይት የመጣው ሰው ቀድሞኝ ደርሷል፡፡ ይህ ወዳጄ ‹ግህንብ› ከተባለውን የምድር ውስጥ እስር ቤት በሕይወት የወጡ አንድ ወልቃይቴ አባት ከማይጋባ እንዲመጡ አድርጓል፡፡ ግህንብ የተባለው ማሰቃያ እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የቆየና በኋላ በመኪና ፈርሶ ትንሽየ አዲስ ዓለም የተበላች ከተማ የተመሠረተችበት አዲ ረመጽ አቅራቢያ ያለ ቦታ ነው፡፡ ስለሆነም ከማይጋባ የመጡት የ60 ዓመት አካባቢ ጎልማሳ ግህንብ የተባለውን ቦታ የነበረበትን በትክክል ስለሚያውቁ እንዲያሳዩን ነበር፡፡ በአናቱም ከወልቃይት የመጣው ሰው ከማንነት አስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር በቅርበት ስለሚሠራ ከጠጉረ ልውጥ ሰው ጋር መታየቱ አደጋ ስላለው በአንጻሩ ደግሞ ማይጋባ የሚኖሩት አዛውንት ምንም ዓይነት ንክኪ ስለሌላቸውው ከእርሳቸው ጋር እንድሔድ ነበር፡፡ አልቤርጎ በእነርሱ መታወቂያ ተከራየሁ፡፡ ሦስታችንም ከሆቴሉ ገባን፡፡
ከአዲ ረመጽ የመጣው ወዳጄ ከማይጋባ ያስመጣውን አባት ስለኔ ለምን እንደመጣሁ፣ ማወቅ የምፈልገውን ሁሉ ዘርዝሮ አስረዳቸው፡፡ ግራ የመጋባት ስሜት ታየባቸው፤ ፊታቸው ሲቀያየር አስተዋልኩ፡፡ ውሳኔያቸውን ቀይረዋል፡፡ ወይ እኛን አላመኑንም፤ አሊያም በጣም ፈርተዋል፡፡ ግህንብ ለሦስት ዓመት ተኩል ታስረዋል፡፡ አብረዋቸው ታስረው የነበሩት ጓዶቻቸው በሕይወት አልወጡም፡፡ ከአዲ ረመጽ የመጣው ወዳጄም ይህን ታሪኩን ስለሚያውቅ ነበር እንደሚረዱን የተማመነው፡፡
አዛውንቱ ጥርት ባለ አማርኛ ተናገሩ፤ ‹‹እንዲያው ልጄ ይህ ታሪክ ላንተም አይጠቅምህም፡፡ እንኳን ላንተ ልነግርህ ሁኔታውን ሳስብ በራሱ ያመኛል፡፡ ያን ስሜት ስለማታውቁት እኔን የሚሰማኝ አይሰማችሁም፡፡ ልጄ ይቅርብህ፤ ግድየለህም›› ሐሳባቸውን ደመደሙ፡፡ እንዴት ማሳመን እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ዝም አልኩ፡፡ የአዲ ረመጹ ወዳጄ ተደናገጠ፤ ምክንያቱም ሁላችንም ሽሬ የተገናኘንበት አንዳችም ሌላ ምክንያት የለንም፡፡ ‹‹ይሄ ልጅ እኮ አዲስ አበባ ድረስ የመጣው የእኛን ጉዳይ ለማጣራት ነው፡፡ በደንብ ማገዝ አለብን›› ተናገረ፡፡ ‹‹እኔ የምኖረው እዚሁ እነሱ መካከል ነው፤ ሚስቴና ልጆቼ ትግሬ ናቸው፡፡ እኔ ደሙ ስለለኝ ነው እንጅ ከእኔ በላይ ትግሬ የት አለ? ዕውነቴን ልጆቼ!›› ተናገሩ፡፡
‹‹እኔ ብዙ የጭፍጨፋ ታሪኮችን ስለማውቅ ቢነግሩኝ ችግር የለውም፤ አይገርመኝም፡፡ እና ለማጣራትም እንዲመቸኝ እርስዎ የሚያውቁትን ይንገሩኝ›› አልኩ፡፡ ‹‹ግህንብ መሬት ተቆፍሮ የተሠራ ዋሻ ነው፡፡ ስንቱ ሰው አልቋል መሠለህ! እንጀራ በመርዝ እየተሰጣቸው ያለቁት ስንት መሰሉህ፡፡ እነ አምሳሉ አምባቸውን የመሠሉ ፓይለቶች ሁሉ እኮ ያለቁት እዚያው ነው፡፡ ለሦስት ዓመት ጨለማ ውስጥ ኖሬያለሁ፡፡ ባቴ ላይ (እግራቸውን እያሳዩ) ትል ይረግፍ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ሲጮኹ እንሰማለን፤ ከእንቅልፍ ስንነቃ አናገኛቸውም፡፡ አስከሬናቸው የት እንደሚጣል አናውቅም፡፡ አሁን ድረስ ገበሬዎች ሲያርሱ እኮ የሰው አጽም ይወጣል፡፡ ስንቱን አማራ ከአዲስ አበባ ድረስ እያመጡ ጨርሰውታል መሰለህ! የግህንብን ሥቃይና ታሪክ ስንቱ ተወርቶ ያልቃል ልጄ›› ሲሉ የሚናገሩት እንዳያመልጠኝ ‹‹ሪከርድ ላድርገዎት›› አልኳቸው፡፡
‹‹ልጄ እኔ የምኖረው እነርሱ መካከል ነው፤ እኔ እኮ ትግሬ ማለት ነኝ፡፡ ታሪኩም ላንተ አይጠቅምህም››
‹‹ታዲያ ትግሬ ቢሆኑ ነው ይህ ሁሉ ማዓት የደረሰብዎት?›› አልኳቸው፡፡ መናገር አልቻሉም፡፡ ድፍን አደረጉት፡፡ ሪከርድ ላድርግዎት ብዬ ባላቋርጣቸው ቢያንስ ብዙ ሊናገሩ ይችሉ ነበር፡፡ የተግባባን መስሎኝ ተሸወድኩ፡፡ ድምጻቸውን ለማስቀዳት ቀርቶ ለመናገርም አይፈለጉም፡፡ ደጋግመው የሚናገሩት ‹‹ከእኔ በላይ ማን ትግሬ አለ?›› የሚል ሐረግ ነው፡፡ ከፍርሃት የመነጨ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አብረውኝ እንኳን አዲ ረመጽ ሊገቡ ደደቢትም ድረስ ሊሸኙኝ አልፈለጉም፡፡ ተሰናበትኳቸው፡፡ ወዳጄ ተናደደ፡፡
ይህ ወዳጄ ‹‹ሽሬን ቶሎ ለቀህ ውጣ፤ የሚሆነው አይታወቅም›› አለኝ፡፡ ከሽሬ አክሱም 65 ኪሎ ሜትር ያክል ነው፡፡
አክሱም፤ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment