Sunday, May 8, 2016

በዓለም የፕሬስ ቀን መሪ ቃል የቀመረች ብቸኛዋ አገር – ጦቢያ!! ( ኤልያስ )


በዓለም የፕሬስ ቀን መሪ ቃል የቀመረች ብቸኛዋ አገር - ጦቢያ!!
• ከተጠያቂነት የመሸሽያ አዲሱ ስትራቴጂ “ፈርሙልኝ” ሆኗል
• ‹‹ብዝሃነት››ን በተመለከተ አገራዊ መግባባት ላይ አልተደረሰም
እንኳን ለዓለም አቀፉ የፕሬስ ቀን አደረሳችሁ! ይባል አይባል ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለነገሩ እንኳን ለማርች 8 የሴቶች ቀን አደረሳችሁ እንደማለት እኮ ነው፡፡ ወይም ደግሞ እንኳን ለዓለም የውሃ ቀን አደረሳችሁ —- ሊሆንም ይችላል፡፡ (የውሃ ቀን የሚባል በዓል አለ እንዴ?!) በነገራችን ላይ በመላው ዓለም የፕሬስ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በቅርቡ የወጡ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ የፕሬስ አፈናው በርትቷል፡፡ ጋዜጠኞች በጨቋኝ መንግስታት ይታሰራሉ፤ይገደላሉ፤ለስደትም ይዳረጋሉ፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ በአይሲስ አንገታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ የተቀሉትን ጋዜጠኞች ሳይጨምር ነው፡፡
የየአገሩ መንግስታት ጋዜጠኞች ላይ እንዲህ አብረው መነሳታቸው ዓለም ወደ አምባገነን ሥርዓት እያመራች መሆኑን መጠቆምያ ፍንጭ እንደይሆን ክፉኛ ያሰጋል፡፡ ያለዚያማ በብዕር ለሚፋለም ጋዜጠኛ፣ እስርና ግድያን ምን አመጣው? ለመጽናኛ ያህል ከጥቂት ወራት በኋላ ስልጣናቸውን የሚለቁት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ሰሞኑን ከፕሬስ ጋር በነበራቸው የመጨረሻ የእራት ምሽት ላይ ባደረጉት ቀልድና ትረባ የበዛበት ንግግር፤ፕሬሱ ለዲሞክራሲያቸው መጎልበት ላደረገው አስተዋጽኦ ዕውቅና እና አድናቆት ቸረውታል፡፡ (ከሩቅ የተሰማ ቢሆንም የተስፋ ሽልን ያላውሳል!)
በነገራችን ላይ በእኛም አገር ባለፈው ማክሰኞ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን በፓናል ውይይት ተከብሮ ውሏል፡፡ በዓሉ ዓለማቀፍ ቢሆንም፣እኛ ያከበርነው በራሳችን አገር በቀል መሪ ቃል መሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ (አያደርገውም እንዴ?) እናላችሁ —– የተለያዩ ባለድርሻ  አካላትን በውዝግብ እንዳናወጠ የተነገረለት  መሪ ቃል፤ “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር – ኢትዮጵያ” የሚል ነው፡፡ (#ባደረገላት” ብሎ ከንፈር መምጠጥ አይቻልም!) አንድ ነገር ልንገራችሁ አይደል—-ይሄን መሪ ቃል ያዘጋጀው  የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ከሆነ አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው፡፡ (በይዘቱ ሳይሆን በቋንቋው እጥር ምጥን ማለት!)  ለምን መሰላችሁ — ከዚህ ቀደም የወጡ በርካታ መፈክሮች የተንዛዙና ስሜት የማይዙ ነበሩ፡፡ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙሃኑ፡፡ ቆይ እስቲ ለመጨረሻ ጊዜ የሰማችሁት መሪ ቃል ትዝ ይላችኋል? እኔ አስታውሳለሁ፤ችግሩ ግን ሙሉውን አይደለም፡፡ “ሩቅ አልማ ሩቅ—ለመድረስ — የምትታትር አገር—” የሚል  መሰለኝ፡፡ (ሩቅ ስለተባለ እኮ ቋንቋውም የግድ መርዘምና መራቅ የለበትም!) እንደውም ተመራጩ እኮ ሩቅ ሃሳብን በቅርብ ቋንቋ መግለጽ ነው፡፡
እንዳልኳችሁ—-እኔ በቋንቋው በኩል ተመችቶኝ ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ ክፉኛ የነቀፉት ቋንቋውን ነው – መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይገልጽም በሚል፡፡ ግን እንዴት? “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር – ኢትዮጵያ”  (አይደለችም  እንዴ?) አሁን ለክርክር የማይመቸው ምኑ  መሰላችሁ? ብዝሀነት በሚለው ቃል ዙሪያ አገራዊ መግባባት ላይ (consensus) አለመደረሱ ነው፡፡ ብዝሀነት፤ለኢህአዴግ  ምንድን ነው? ለተቃዋሚዎችስ? ለጋዜጠኛውና ለምሁሩስ?  አንድ የማንክደው ሃቅ አለ፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብቻ 10 ደርሰዋል፡፡ ገና የብሮድካስቲንግ ሳይጨመር ማለት ነው፡፡ (ሁሉም ግን ከፖለቲካ የጸዱ ናቸው!) ኢቢኤስ፣ቃና፣ዋልታ፣ጆሲ፣ኢኤንኤን፣የኢቢሲ ቻናሎች– ወዘተ፡፡ ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያን በተመለከተ ደግሞ ቀድሞ የነበሩት 3 የግል ኤፍኤሞች ላይ በቅርቡ 3 ተጨምረዋል፡፡ (ብዝሃነት ቁጥር ነው እንዴ?)
በእርግጥ የግል ፕሬሱን ከጠየቃችሁኝ —- እንደ ባራክ ኦባማ It is a bit complicated. ማለቴ አይቀርም፡፡ (ኦባማ በቅርቡ ዘ አትላንቲክ ከተሰኘው መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ከሳውዲ ጋር ወዳጅ አይደላችሁም ወይ ሲባሉ የሰጡት ምላሽ  ነው) እናላችሁ —  እንኳንስ የፕሬሱን ብዝሃነት ልናነሳ፣ለራሱ እኮ የአደጋ ቀጠና ውስጥ ነው ያለው፡፡ (“እዬዬም ሲዳላ ነው” አሉ!!)
ወዳጆቼ፤ኢህአዴግ ግለሰቦችን የመሸለምና ዕውቅና የመስጠት ባህል ስለሌለው ነው እንጂ የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ የአገሪቱ ብሔራዊ ተሸላሚ ይሆን ነበር፡፡ (መረጃ ሲቆፈር ቢዋል ጠብ በማይልባት አገር፣ጋዜጣ እየሸጡ ለመንግስት ግብር መክፈል በእርግጥም አስማተኛ መሆንን ይጠይቃል!) በነገራችሁ ላይ እሱም ሳይሸልም እንደ አንዳንድ ምቀኛ መንግስታት ሌላም ወገን አይሸልምህም ብሎ ቢገግም ኖሮ አደጋ ነበር፡፡ (ፈጣሪ በስንቱ ልበድላቸው ብሎ መሆን አለበት!) ኢህአዴግ የግል ፕሬሱን የመሸለም ግዴታ ባይኖርበትም፣(ያውም እየተቸው?) የኢትዮጵያን ህዝብ ግን ሳይወድ በግድ መሸለም ይኖርበታል!! ለምን መሰላችሁ? ለ25 ዓመት ላሳየው ትዕግስትና ሁሉን ቻይነት! ለዚህ ባለውለታ ህዝብ ግን ኢህአዴግ ቢያንስ ራሱን ከመልካም አስተዳደር ጉድለቶች አጥርቶ፣ የበቃ የነቃ ሥልጡን መንግስት ሊሆንለት አልቻለም፡፡ በነገራችን ላይ ጦቢያ “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር” መሆን አለመሆኗም ጭምር የመልካም አስተዳደር ጉዳይ እኮ ነው፡፡
ባለፈው ሰሞን የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፤በከፍተኛው የፖለቲካ አመራሩ አካባቢ ያለ ወገንተኝነት፣ቁርጠኝነት ማነስና ኪራይ ሰብሳቢነት ካልተፈታ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ፈታኝ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡ (እውነታቸውን እኮ ነው!) የምክር ቤት አባላት ለወ/ሮ አስቴር ያነሱት ጥያቄና የተሰጣቸው ምላሽም ታዲያ እውነት እውነት የሚሸት ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴው ለምን እንደሚንከባለልና ከፍተኛ አመራሩ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ ተጠያቂ የማይሆንበት ምክንያት እንዲገለጽላቸው የምክር ቤት አባላት የጠየቁ ሲሆን ሚኒስትሯ በሰጡት ምላሽ፤መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመረው ትግል የሚንከባለልበትና በተለያየ ደረጃ የሚገኝበት ምክንያት ራሱ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነና መነሻውም ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የከፍተኛ አመራሩ ደካማነት፣ቁርጠኛ አለመሆን፣ውግንና የመሳሰሉት ባህሪያት ንቅናቄውን በግለት ለማስቀጠል እንቅፋት እንደሆነም ወ/ሮ አስቴር በግልጽ ተናግረዋል፡፡
ለነገሩ የታችኞቹን ብቻ በማባረር የሚሳካ ቢሆንማ፣ እስካሁን አንዳች ለውጥ እናይ አልነበር፡፡ (ከየቦታው እኮ በብዙ ሺ የሚገመቱ የበታች ሃላፊዎች ተሸኝተዋል!) ለነገሩ አዲሶቹስ እንዴት ነው የሚተኩት የሚለውም አጠያያቂ እኮ  ነው፡፡ ከቀድሞው በተለየ መንገድ የሚመለመሉበት መንገድ ካልተቀየሰ፣ከበፊቱ የተለየ ውጤት እንደማናገኝ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (ኢህአዴግ መቁረጥ ግዴታው ነው!)
እኔ የምለው ግን —- “የመልካም አስተዳደር ጉድለት” የሚባለው …ችግር ከመሬት ወረራ ጀምሮ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ኃጢአትና ወንጀሎችን በውስጡ አጭቆ — በዚሁ ለስላሴ ስሙ ጸና ማለት ነው? (ስሙና ውክልናው እኮ ፈጽሞ አይገናኝም!) የመልካም አስተዳደር ጉድለት ለሚባለው ጉዳይ  ውክልናውን የሚመጥን የጠገነነ ስያሜና  ለመንግስት መ/ቤቶቻችን ጉራማይሌ ወይም እኩሌታው እንግሊዝኛ ያልሆነ መጠሪያ የሚያወጣልን አገር አቀፍ  ተቋም ማቋቋም ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ (ችግሩ ቢባል ቢባል ያልተፈታው፣ምናልባት የሚመጥነው ስያሜ ስላላገኘ ቢሆንስ?) በነገራችን ላይ — የመንግስት መ/ቤቶችና የታሸጉ ውሃ ምርቶች ስያሜ ሲታይ እኮ፣ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የነበርን ነው የምንመስለው፡፡ እዩልኝ ዝርዝራቸውን—-ሃይላንድ፣ሪል፣አኩዋ ሴፍ፣የስ፣ዋን፣አቢሲኒያ ስፕሪንግ፣ብሉ ወዘተ— (የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታችንን በውሃ ላይ ጨረስነው እኮ?)
አሁን የማወጋችሁ ጉዳይ ደግሞ በዓይነቱ ለየት ያለና በእጅጉ የሚያስገርም ቢሆንም ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ ለምን ቢሉ——ተጠያቂነትን ለመሸሽ ወይም ለማይመለከተው ወገን ለማስተላለፍ ከሚደረግ ሙከራ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው፡፡ እኔ እንደውም ፣“አዲሱ ከተጠያቂነት የመሸሽያ ስትራቴጂ” ብዬዋለሁ፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ? ነገርዬው የዕድሜ ባለጸጋ ከሆነው አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተምያ ቤት ጋር የተገናኘ  ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ የመንግስት ልማት ድርጅት ይሄን ስትራቴጂ የፈጠረው በጥናት ላይ ተመስርቶና አስቦበት ሳይሆን ድንገት ነው – ከችግር፡፡ (አበሻ “የቸገረው እርጉዝ ያገባል” እንደሚለው ማለት ነው!)
እናላችሁ ምን ሆነ መሰላችሁ—ባለፈው ሳምንት ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በርካታ ጋዜጦች በተመሳሳይ ጊዜ ለህትመት ሳይገቡበት አልቀሩም፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ በዛ ያሉ የእንኳን አደረሳችሁ ማስታወቂያዎች የያዙ ነበሩ፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ማተምያ ቤቱን በሥራ ሊያጨናንቀው እንደሚችል ገመተ፡፡ በሥራ ማጨናነቅ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በቀናቸው ሊያወጣቸው እንደማይችል አቅሙን ተጠራጠረ፡፡ ይሄኔ ነው የማተምያ ቤቱ ሃላፊዎች ከተጠያቂነት የማምለጪያ ስትራቴጂው ብልጭ ያለላቸው፡፡ እናም በዓለም አቀፍ የቢዝነስ አሰራር ፈጽሞ ያልተለመደ ቢሆንም ለጋዜጣ አሳታሚ ደንበኞቻቸው እንዲህ አሏቸው፡- “በሥራ መደራረብና በማተምያ ማሽኖች ችግር የተነሳ  ጋዜጣችሁ በቀኑ ላይወጣ ስለሚችል ለሚደርሰው ኪሳራ ሃላፊነቱን እንወስዳለን ብላችሁ ፈርሙልን”  (#በእኛ አቅም ማነስ ለኪሳራ ብትዳረጉ ተጠያቂ አይደለንም፤አለመሆናችንንም በፊርማችሁ አረጋግጡልን” ማለት እኮ ነው!) በነገራችን ላይ የሃላፊነት ፊርማውን መጠየቅ የነበረባቸው እኮ አሳታሚዎቹ ነበሩ፡፡ ከቀድሞ ተሞክሮ ግን እንኳንስ ገና ወደፊት ለሚደርስ ኪሳራ፣በተደጋጋሚ ለደረሰባቸውም ኪሳራ አጥብቀው እንደማጠይቁ የተገነዘበው ብርሃንና ሰላም ግን ቀደማቸውና ከተጠያቂነት የማምለጪያ ስትራቴጂውን አመጣላቸው፡፡ (ፈርሙልኝ ጉድ አፈላ እኮ!)
የሚያስገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ከጥቂት ወራት በፊት ማተምያ ቤቱ በተደጋጋሚ ጋዜጦችን እያዘገየ በማውጣቱ አሳታሚዎች ያሰሙትን የመረረ እሮሮ ተከትሎ፣ “ከእንግዲህ ወዲህ ጋዜጦች በእኛ ምክንያት ዘግይተው ሲወጡ የሚደርስባችሁን ኪሳራ ለመሸፈን እንፈርምላችኋለን” ብሎ ነበር፡፡ ግን ምኑ ሞኝ ነው፤አለ እንጂ አላደረገውም፡፡ አለማድረጉም በራሱ መንገድ (በመንግስት ልማት ድርጅት አሰራር ማለቴ ነው) ጠቅሞታል፡፡ ጭራሽ “በራሴ አቅም ማነስና ችግር ሳቢያ ለሚደርሰው ኪሳራ ተጠያቂ እንደማታደርጉኝ ፈርሙልኝ” ብሎ አረፈው፡፡ (only in Ethiopia ይሏል ይሄ ነው!) በነገራችን ላይ በዘንድሮ በዓል ማተምያ ቤቱ እንደፈራው አልተከሰተም፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ (በተዓምር በሉት!) ጋዜጦች ከሞላ ጎደል በቀናቸው ወጥተዋል፡፡ (በሌሎች በዓላት እኮ የዓውዳመት ህትመቶች ከበዓሉ ሁለትና ሶስት ቀናት በኋላ ሁሉ ወጥተው ያውቃሉ፡፡) እንዲያም ሆኖ ግን አሳታሚዎች አንጋፋውን ማተምያ ቤት እንደ ዘንድሮም ታዝበውት አያውቁም፡፡ ለነገሩ ላለፉት 25 ዓመታት በአቅም እሱን የሚተካከል  የግል ማተምያ ቤት ሳይከፈት የቀረው ለምን እንደሆነ ባይነገረንም፣ እንደ “ደንብ አምስት” ድራማዋ ውዴ መጠርጠር አያቅተንም፡፡ ግን እኮ ይሄም ራሱ የቀለጠ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment