Sunday, May 8, 2016

ወደ አገር ውስጥ የገባው የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ኪት ድረጃውን የጠበቀ አይደለም ተባለ (የፍኖተ ዴሞክራሲ ራድዮ አጫጭር ዜናዎች

 

      

dire
ሚያዚያ 29 ቀን 2008 ዓ.ም.
ርዕሰ ዜናዎች
 ወደ አገር ውስጥ የገባው የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ኪት ድረጃውን የጠበቀ አይደለም ተባለ
 ድሬደዋ የጎርፍ አደጋ አጋጠማት
 የሩዋንዳውን አገዛዝ ሲቃወምና ሽብር ሲፈጥ የነበረ ድርጅት ም/ኃላፊ ኮንጎ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ
 ለውጭ ኃይሎች የአገር ሚስጥር አሳልፋችሁ ሰጥታችኋል የተባሉና ከቀደሞ የግብጽ ፕሬዚዳንት ጋር ተከሰው የነበሩ ስድስት ሰዎች የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው
 በሊቢያ ምስራቃዊ ክፍል የአንድነት መንግስቱን መመስረት አስመልክቶ ድጋፋቸውን ለመስጠት በወጡ ሰልፈኞች ላይ ከባድ መሳሪያ ተተኩሶ በርካታ ሰዎች ሞቱ፤
 በምዕራብ ሊቢያም የአይሲስ ኃይሎች የያዙትን ቦታ ለማስለቀቅ ጦር ተላከ ዝርዝር ዜናዎች
 የወያኔ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ እንደገዛ የተነገረለት የኤች አይ ቪ አዔድስ መመርመሪያ ኪት ወደ አገር ውስጥ የገባ ቢሆንም ደረጃውን የጠበቀ አለመሆኑ ታውቋል። ከወራት በፊት ባስተላለፍነው የዜና ዘገባ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሀገር ውስጥ አለመኖሩና በዚህም ምክንያት የኤድስ ምርመራ ለማካሄድ አለመቻሉን መዘገባችን ይታወሳል።፡ችግሩን ለመቅረፍም አለም አቀፍ የጤና ድርጅትና ግብረሰናይ ድርጅቶች በሰበሰቡትና በለገሱት ገንዘብ የኤች አይ ቪ ኤድስ መመርመሪያ መሳሪያ ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ቢገባም የደረጃው ኪት ደርጃውን ያልጠበቀና አስተማማኝ መረጃን የማይሰጥ መሆኑ ታውቋል።፡ይህ ደግሞ በመርማሪዎች ላይ የተሳሳተ መረጃ እንዲሰጥ በማድረግ ዜጎችን ላልተፈለገ አካላዊና ስነልቡናዊ ቀውስ እንደሚያጋልጥ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
 የጎርፍ አደጋ ደጋግሞ የሚያጠቃት ድሬደዋ ሀሙስ ሚያዚያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎርፍ አደጋ መመታቷ ታውቋል። በዚህ የጎርፍ አደጋ የጎርፍ መከላከያ ተብሎ የተገነባው 120 ሜትር ቁመት ያለው ግድብ መፍረሱንም የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል። በዚህ የጎርፍ አደጋ የተነሳ በድሬደዋ የንግድ እንቅስቃሴዎች በተወሰኑ አካባቢዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይካሄዱ የድሬደዋ ባለስልጣኖች ማዘዛቸው ሲታወቅ ለጎርፉ አደጋ ማስጠንቀቂያም የፖሊስ አባላት ጥይት በመተኮስ የማንቃት ስራ እንዲሰሩ ተጠይቋል። ሐሙስ ዕለት የጎርፉ አደጋ በአራት ሰዎች ላይ አደጋ ማድረሱ ሲታወቅ በንብረት ላይ ያስከተለው ጉዳት ግን አልታወቀም። በድሬደዋ በመልካ ጀብዱ አካባቢ ያለ አንድ ድልድይም በጎርፉ አደጋ መወሰዱ ታውቋል።
 በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምስራቃዊ ክፍል ከፍተኛ ግድያና ጭፍጨፋ ሲያካሂድ የቆየውና የሩዋንዳ ነጻ አውጭ ዴሞክራቲክ ኃይሎች የሚል ስም ይዞ ይንቀሳቀስ የነበረው ድርጅት ምክትል መሪ የነበረው ግለሰብ ከአራት ቀናት በፊት ጎማ በተባለችው ከተማ ተይዞ በቁጥጥር የተደረገ ሲሆን ለፍርድ ሊቀርብ እንዲችል ወደ ዋናው የአገሪቱ ከተማ ወደ ኪንሻሳ የተወሰደ መሆኑን የኮንጎ የማስታወቂያ ሚኒስትር ለዜና ምንጮች ገልጸዋል። የሩዋንዳ ነጻ አውጭ ዴሞክራቲክ ኃይሎች የተባለው ግምባር የተፈጠረው በ1986 ዓም በሩዋንዳ ውስጥ እልቂት በፈጸሙና ወደ ኮንጎ በሸሹ የሁቱ ጎሳ አባላት የተቋቋመ ሲሆን ከዚህ በፊት ቀንደኞቹ የድርጅቱ አባላት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ፍርድ ቤት ቀርበው ፍርድ የተሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል። የኮንጎ ባለስልጣኖች በቁጥጥር ስር ያደርጉትን የድርጅቱን ምክትል መሪ ከዓለም አቀፉ ድርጅት ጋር ቅርበት ላላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣኖች የሚያስረክቡ መሆናቸው ከዚያም ወደ ሩዋንዳ እንደሚወሰድ ተገልጿል።
 ለካታር መንግስት ስለላ አካሂደዋል የግብጽን መንግስት ሚስጥሮች አሳልፈዋል ሰጥተዋል በተባሉ ስድስት የቀደሞ ፕሬዚዳንት ሞርሲ ባልደረቦች ላይ አንድ የግብጽ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት የወሰነ መሆኑ ታውቋል። ሞርሲ በዚሁ ጉዳይ ክስ የተመሰረተባቸው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ፍርድ ቤት የሰጣቸው የሞት ፍርዶች እሳቸውን አይጨምሩም። በግብጽ ሕግ መሰረት ማንኛውም የሞት ፍርድ ተግባራዊ የሚሆነው ቅጣቱ በእስልምና ህግ መሰረት መሆኑንና አለመሆኑን መርምሮ ውሳኔ ለመወሰን ስልጣን የተሰጣቸው ሙፍቲ የተባሉት በውሳኔው ላይ ያላቸውን አስተያየት ከሰጡ በኋላ በመሆኑ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለሙፍቲው የተላከ መሆኑ ተገልጿል። የሙፍቲው ውሳኔ ሰኔ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚታወቅ መሆኑ ተገልጿል። የሞት ፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ተከሳሾች ገሚሶቹ ከአገር ውጭ በመሆናቸው በሌሉበት የተሰጠ ፍርድ ሲሆን ውሳኔው በይግባኝ ሊቀለበስ የሞችል መሆኑ ታውቋል።
 የፓሪሱን የሽብር ጥቃት በማካሄድ በኩል ቁልፍ ሚና የነበረ የአብዱልሃሚድ አባውድ ታናሽ ወንድም ያሲን አባውድ ሞሮኮ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉ ከዚህ በፊት የተዘገበ ሲሆን ሽብርን የሚደግፍ ንግግር ተናግረሃል በሚል ክስ ተከሶ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጣ የተፈረደበት መሆኑ ተነግሯል። ጠበቃው ያሲን ወንድሙ ስለፈጸመው ተግባር የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ለመከራከር ቢሞክርም የሽብር ተግባርን ደግፏል በሚል ፍርድ ቤቱ የሁለት ዓመት እስራት ወስኖበታል። ሌሎች አምስት ሰዎች በሽብርና በሌላ ወንጀል ስራዎች ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት በሚደርሱ የእስራት ቅጣቶች እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ የወሰነ መሆኑም ታውቋል።
 አርብ ሚያዚያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በምስራቅ ሊቢያ በምትገኘው በቤንጋዚ ውስጥ የሊቢያን የአንድነት መንግስት ለመደገፍ የሊቢያ መከላከያ ተቋም በጠራው ስብሰባ ላይ የከባድ መሳሪያ ሼል ተተኩሶ አምስት ሰዎች መሞታቸውና 11 ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል። ከባድ መሳሪያው የተተኮሰው ከከተማው በስተሴሜን ካለ ቦታ ወታደራዊ ተቋሙን በሚጻረሩና የአንድነት መንግስቱን መቋቋም በማይደግፉ ኃይሎች መሆኑ ተነግሯል። ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ታጥቂዎች ስር የወደቀችው የቤንጋዚ ከተማ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰባት ከተማ ስትሆን በተደረጉ የእርስ በርስ ግጭቶች በርካታ ነዋሪዎች መሞታቸው ይታወቃል። በጀኔራል ከሊፋ ሃፍታር የሚመራው የሊቢያ ወታደራዊ ተቋም በርካታ ቦታዎችን ከታጠቁ ኃይል ቁጥጥር ነጻ ያወጣ ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑ ታውቋል።
በተያያዘ ዜና በምዕራብ ሊቢያ ከሚስራታ ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አቡ ግሬን የሚባለው መስቀለኛ መንገድ በአይሲስ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በመወደቁ ቦታውን ለማስለቅቀ ከሚስራታ የሚሊሺያ ኃይሎች የተንቀሳቀሱ መሆኑ ተነገሯል፡፤ ሐሙስ ሚያዚያ 26 ቀን የአይሲስ ኃይሎች በቅድሚያ አጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳው ቦምብ ሁለት ፖሊሶችን ከገደሉ በኋላ ባካሂዱት የተጠናከረ ጥቃት ቦታውን ለመቆጣጠር የቻሉ መሆናቸው ታውቋል። በሚስራታ የሚገኙ ሆስፒታሎች ካስተላለፉት መርጃ በውጊያው 8 ዜጎች መሞታቸውና 105 የሚሆኑ የቆሰሉ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል። በሚስራታ የሚገኘው የወታደራዊ ካውንስል መሪ በስራቸው የሚገኙት ወታደራዊ ብርጌዶች ወደ ቦታው ተንቀሳቅሰው አካባቢውን ነጻ እንዲያወጡ ትእዛዝ መስጠታቸውን አስታውቀዋል። የአይሲስ ቡድን ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ሰርት የተባለችውን ከተማ በመቆጣጠር የማሰልጠኛ ካምፑን ያጠናከረ መሆኑ ይናገራል። 5000 አባላት እንዳሉት የሚገመተው አይሲስ በሊቢያ እየጠናቀረ መሄዱ ያሳሰባቸው የአውሮፓ መንግስታት አይሲስ ሊቢያን ማዕከል በማድረግ በአውሮፓ አገሮች ላይ ጥቃቱን ያፋፍማል የሚል ስጋት አላቸው

No comments:

Post a Comment