Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity Satellite Radio News
የግንቦት 01 ቀን 2008 ዓ.ም. (May 09, 2016 NEWS)
#ከሞጆ ደረቅ ወደብና ከጂቡቲ ወደብ በወቅቱ ዕቃቸውን የማያነሱ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃዳቸው ሊቀማ ነው
#ሩዋንዳ ውስጥ በከባድ ዝናም ምክንያት 500 ቤቶች ፈርሰው ከ40 በላይ ሰዎች ሞቱ
#በሶማሊያ ዋና ከተማ አልሸባብ በሰነዘረው ጥቃት ሁለት የፖሊስ መኮንኖችና ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ
#በግብጽ ከአይሲስ ጋር ግንኙነት ያለው አንድ ቡድን ስምንት ፖሊሶችን ገደለ
#አንድ የጂሃዲስቶች ቡድን ምክትል ኃላፊ በማሊ የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ዋለ
በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የተከማቹት ኮንቴኔሮች ባስቸኳይ ካልተነሱ ውርስ እንደሚሆኑ በመግለጽ የወያኔ መሪዎች መመሪያ ማስተላልፋቸውን ከጥቂት ቀና በፊት ባስተላልፈነው ዜና መግለጣችን ይታወሳል። የወያኔ ባለስልጣኖች በጉዳዩ ላይ በሰጡት ተጨማሪ መመሪያ ከጂቡቲና ከሞጆ ሸቀጦቻቸውን በወቅቱ የማያነሱ ነጋዴዎች ከአስመጭነት ስራቸው ሊታገዱ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። ነጋዴዎቹ በደረቅ ወደብ ያላቸውን ዕቃ ለማውጣት ከአገዛዙ አካላት ጋር በመነጋገር መፍትኄ ለመፈለግ ያቀረቡትን ጥያቄ የወያኔ መሪዎች ውድቅ ያደረጉት ሲሆን የተወረሱትን ሸቀጦች አስመልክቶ የተበላሸው እንደሚጣልና ያልተበላሸው በጨረታ እንደሚሸጥ ገልጸዋል። በንግዱ ስራ ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች የወያኔ ባለስልጣናት የሰጡት መመሪያና ትዕዛዝ ዱብ ዕዳ እንደሆነባቸውና የነጋዴውን ችግር ያላገናዘበ የአገሪቱንም ሁኔታ ያላጤነ ነበር በማለት ገልጸው የተሰጠው መመሪያና ትዕዛዝ ሆን ተብሎ ከአንድ ዘር ውጭ ያሉ ነጋዴዎችንና አስመጭዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የታቀደና የታለመ መሆኑን ይናገራሉ።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በሩዋንዳ ከተማ በማከታተል በጣለው ከባድ ዝናም ምክንያት የመሬት መደርመስ ተፈጥሮ 40 ሰዎች የሞቱ መሆናቸው የዜና ምንጮች ዘግበዋል። የጣለው ከባድ ዝናም ከፍተኛ የሆነ የመሬት መደርመስን ያደረሰ ሲሆን 500 መኖሪያ ቤቶችን እንዳልነበሩ አፍርሷል። በሩዋንዳ የዘንድሮ የክረምት ወራት ከወትሮው ለየት ያለ ከበድ ያለ ዝናም መዝነቡ እየተነገረ ሲሆን በኬኒያም ባለፈው ሳምንት የጣለው ከባድ ዝናም ለ42 ሰዎችም መሞትና ለበርካታዎች መቁሰል ምክንያት የሆነውን ባለስድስት ፎቅ ሕንጻ የደረመሰ መሆኑ ይታወቃል።
ዛሬ ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሶማሊያ አልሸባብ የተባለው ቡድን አባላት የሆኑ ሁለት ግለሰቦች በፈንጅ የጠመደ መኪና እያሸረከሩ በሞቃዲሾ ዋና ከተማ በሚገኘው የትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤት ላይ ባካሄዱት ጥቃት ቢያንስ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች ሌሎች ሌሎች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውና ዘጠኝ ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል። በመኪናው ላይ የነበረ የቡድኑ አባል የመስርያ ቤቱን ቅጥር ግቢ በሚጠብቁት ላይ ተኩስ ከፍቶ ጥቃት ሲሰነዝር በጥይት ተመቶ የሞተ ሲሆን የመኪናው አሽከርካሪ በፈንጅው ራሱን አጥፍቷል። በሱማሊያ ተዳክሟል እየተባለ ሲነገርለት የቆየው አልሸባብ ጥቃቱ እያጠናከረ መምጣቱ ባለስልጣኖችን እያሳሳሰበ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
እሁድ ሚያዚያ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በግብጽ ዋና ከተማ በካይሮ ሄልዋን በሚባለው አካባቢ በካሚዮን ላይ የተጨኑ አራት ታጣቂዎች በአንድ የፖሊስ ቫን መኪና ላይ ባካሄዱት የሩምታ ተኩስ በመኪናዋ ውስጥ የነበሩ ስምንት ፖሊሶች መገደላቸው ታውቋል። በሲና ባህረሰላጤ የሚንቀሳቀሰው እና ከአይሲስ ጋር ግንኘነት እንዳለው የሚነገርለት አሸባሪ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል። “የሲና ክፍለሀገር” በሚል ራሱን የሚጠራው ይኸው ቡድን የቀደሞ ፕሬዚዳንት ሞርሲ ከስልጣናቸው ከተነሱ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በሲና ባህረ ሰላጤ በመቶ የሚቆጠሩ የግብጽ የጸጥታ ኃይል አባላትን የገደለ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በካይሮ በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት እየሰነዘረ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በብሩንዲ ዋና ከተማ በተለያዩ ቦታዎች በተጣሉ የእጅ ቦምቦች ሶስት ሰዎች ተገድለው ከ20 በላይ ሰዎች የቆሰሉ መሆናችው ታውቋል። አርብ ሚያዚያ 28 ቀን 2008 ዓም በተወረወረ የእጅ ቦምብ 8 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ቅዳሜ ሚያዚያ 29 ቀን በአንድ አነስተኛ ገበያ ላይ የተወረወረ ቦምብ ሁለት ሴቶች መግደሉ ተዘግቧል፡፤ እሁድ ሚያዚያ 30 ቀን ብዊዝ በሚባለው አካባቢ በአንድ የመጠጥ ቤት ውስጥ ቦምብ ተወርውሮ አንድ ሰው መሞቱና 5 ሰዎች መቁሰለቻው የዜና ምንጮች ተናግረዋል። የብሩንዲው ዋና ከተማ የቡጁምቡራ ከንቲባ ሰኞ ግንቦት 1 ቀን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሸባሪዎች የሚሏቸው የሽብር ተግባር እያስፋፉ የመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው ሽብረተኞችን ጨርሶ ለማጥፋት አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በብሩንዲ በተከሰተው የፖሊቲካ ውጥረት በርካታ ሰዎች መገደላቸውና በብዙ ሺ የሚቆጠሩ መሰደዳቸው ይታወቃል።
የማሊ የጸጥታ ልዩ ኃይሎች አንድ የጂሃዲስት መሪ ነው ተብለው የሚጠረጠር ግለሰብ በቁጥጥራችው ስር ያደረጉ መሆናቸው እሁድ ሚያዚያ 30 ቀን 2008 ባለስልጣኖች ለዜና ምንጮች ከሰጡት መረጃ ለማወቅ ተችሏል። ያኩባ ቱሬ እየተባለ የሚጠራውና አንሳር ዲን የተባለ ድርጅት ሁለተኛ ሰው እንደሆነ የሚነገርለት ግለስብ የተያዘው ሐሙስ ሚያዚያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. መሆኑን ባለስልጣኖቹ ጨምረው የገለጹ ሲሆን ከአንድ ወር በፊት የቡድኑ ዋና መሪ በደቡብ ማሊ ግዛት ውስጥ ተያዞ በቁጥጥር ስር መደረጉ ይታወቃል። ቡድኑ በደቡብ ማሊ እና በቡርኪና ፋሶ ለሚንቀሳቀሱ ሌሎች የጂሃዲስት ቡድኖች መሳሪያ በማቀበል ስራ ላይ እንደተሰማራ ይጠረጠራል።
No comments:
Post a Comment