Sunday, May 1, 2016

ዓቃቤ ሕግ በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ዋስትና ላይ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

 


ኤርሚያስ አመልጋ
ኤርሚያስ አመልጋ
የሚያዙበት በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ቼክ የማውጣት (የመጻፍ) ወንጀል የቀረበባቸው ክስ ዋስትና እንደማያስከለክል ተገልጾ፣ የተፈቀደላቸውን የ600 ሺሕ ብር ዋስትና በመቃወም የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡
የሥር ፍርድ ቤት ማለትም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ተጽፎ በቀረበለት የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራችና የቦርድ አባል አቶ ኤርሚያስ ላይ የተመሠረተውን ክስ ተመልክቶ፣ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ የቀረቡትን የሚያዙበት በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ቼክ የማውጣት (የመጻፍ) ወንጀል መርምሮ ነው ውሳኔ የሰጠው፡፡ ለስድስት ሰዎች የጻፉት ደረቅ ቼክ የገንዘብ መጠን በድምሩ 4.8 ሚሊዮን ብር መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በኩባንያው ስም ከተሰበሰበ ገንዘብ ላይ ለስድስት ሰዎች የጻፉት የገንዘብ መጠን ያን ያህል የሚባል አለመሆኑን አብራርቷል፡፡
በመሆኑም ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67(ሀ)ን ጠቅሶ ማለትም፣ ‹‹በዋስትናው ወረቀት የተመለከቱትን ግዴታዎች አመልካቹ የሚፈጽም የማይመስል የሆነ እንደሆነ ዋስትና ይከለከላል፤›› በሚለው ድንጋጌ መነሻነት ተከሳሹ ወደፊት ጥፋተኛ ቢባሉ፣ በእያንዳንዱ ክስ የሚጣልባቸው ቅጣት ሲደመር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልና ዋስትና ቢፈቀድላቸው ሊጠፉ እንደሚችሉ በማስረዳት፣ የዋስትና መብታቸው እንዲታለፍ ያቀረበውን ክርክር የሥር ፍርድ ቤቱ አልፎታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ያለፈበትን ምክንያት እንዳብራራው ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው መከራከሪያ ሐሳብ በቂ፣ ጠንካራና አሳማኝ ምክንያቶችን አላቀረበም፡፡ በመሆኑም ዋስትና የማግኘት ግዙፍ የሆነው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት በውሳኔው አስረድቷል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በ600 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁና ከአገር እንዳይወጡ ለኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ተመሳሳይ ሥጋቱን በመግለጽ፣ ውሳኔው ውድቅ ተደርጐ አቶ ኤርሚያስ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ አመልክቶ ነበር፡፡
ዳኛ ዳኜ መላኩ፣ ዳኛ ገበየሁ ወርቁና ዳኛ ከድር አልይ የተሰየሙበት ይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ብይን ክሱ የቼክ ጉዳይ መሆኑን፣ ገንዘቡም 4.8 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ከሥር ፍርድ ቤት የውሳኔ መዝገብና ከዓቃቤ ሕግ የመቃወሚያ አቤቱታ ሰነድ መረዳቱን ገልጿል፡፡ በመሆኑም የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ዋስትና እንደማያስከለክል ገልጾ፣ ዓቃቤ ሕግ ግን የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግለት በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67(ሀ) መሠረት ሥጋቱን በማሳወቅ የተከራከረ ቢሆንም፣ የሥር ፍርድ ቤት እንዳልተቀበለው በመግለጽና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ውሳኔውን ውድቅ እንዲያደርግለት መሆኑን አስታውሷል፡፡
ችሎቱ የዓቃቤ ሕግን አቤቱታና የተጠርጣሪውን ጠበቆች መልስ ሲመረምር የዓቃቤ ሕግ ሥጋት በበቂና በጠንካራ ምክንያቶች የተደገፈ አለመሆኑን በመግለጽ፣ የሥር ፍርድ ቤት በ600 ሺሕ ብር ዋስትና ተጠርጣሪው እንዲለቀቁና ከአገር እንዳይወጡ የሰጠው ትዕዛዝ የሚነቀፍ ሆኖ እንዳላገኘው በማስታወቅ የይግባኝ አቤቱታውን እንዳልተቀበለው አስረድቷል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታውን እንዳልተቀበለው የገለጸው ጠዋት 4፡30 ሰዓት አካባቢ በመሆኑ፣ ማስፈቻ አስጽፈው ለማስፈታት የተሰጠውን ብይን በመያዝ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሄዱት የአቶ ኤርሚያስ ቤተሰቦች ግን እንዳሰቡት እንዳልተሳካላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ብይን ግልባጭ የደረሰው የሥር ፍርድ ቤት ቀደም ብሎ አቶ ኤርሚያስ በዋስ እንዲለቀቁ ማዘዙን ገልጾ፣ አሁን የሚጽፈው የማስለቀቂያ ወረቀት ሳይሆን ፖሊስ እስካሁን ለምን እንዳለቀቃቸው ማብራሪያ እንዲሰጠው መሆኑን እንደነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን ካፀደቀ እንዲፈቱም መጻፍ ያለበት እሱ መሆኑን የተረዱት ቤተሰቦቻቸው ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተመለሱ ቢሆንም፣ ‹‹ዳኞች የሉም ነገ (ዛሬ) ተመለሱ›› በመባላቸው መመለሳቸውንና አቶ ኤርሚያስም በዕለቱ አለመፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ስለሰጠው ብይን የተሰማቸውን የተጠየቁት የአቶ ኤርሚያስ ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ፣ ‹‹ሕግ አሸነፈ፤›› በማለት አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment