Sunday, May 8, 2016

30 ኢትዮጵያውያት በዱባይ ኤርፖርት ኢሚግሬሽን የደኅንነት ሠራተኞች ወደ ዱባይ እንዳይገቡ ተከልክለው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ፡፡


30 ኢትዮጵያውያት በዱባይ ኤርፖርት ኢሚግሬሽን የደኅንነት ሠራተኞች ወደ ዱባይ እንዳይገቡ ተከልክለው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ፡፡
በፍላይዱባይ የአየር በረራ በአንዴ ከአዲስ አበባ ከተጓዙት መካከል 30 ኢትዮጵያውያት፣ በዱባይ ኤርፖርት ኢሚግሬሽን የደኅንነት ሠራተኞች ወደ የተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ የንግድ ከተማ ዱባይ እንዳይገቡ ተከልክለው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የፍላይዱባይ የበረራ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር እንዳረጋገጠው ከሆነ፣ ሴቶቹ መንገደኞች ሕጋዊ የቪዛና የበረራ ቲኬት ይዘው የተጓዙ ቢሆንም፣ የጉዞ ምክንያታቸው ‹‹ለጉብኝት›› የሚል በመሆኑ ለኤርፖርቱ ኢሚግሬሽን ሠራተኞች አሳማኝ ባለመሆኑ ምክንያት ሊመለሱ ችለዋል፡፡
የአየር መንገዱ ጽሕፈት ቤት እንደሚለው፣ ኤርፖርቱ አንድ ተጓዥ ተመልሶ ወደ አገሩ እንደሚገባ የሚገልጽ የደርሶ መልስ ትኬት መያዙን፣ እንዲሁም በአገሪቱ ለሚኖረው ቆይታው በቂ ስፖንሰር እንዳለው፣ አልያም በቂ ገንዘብ መያዝ አለመያዙን አረጋግጦ ማሳለፍና መከልከል የተለመደ ነው፡፡ ይኼኛውን ድርጊት ለየት የሚያደርገው ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከአንድ በረራ መመለሱ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ተጓዦቹ ሕገወጥ እንዳልሆኑ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ዋቢ በማድረግ ገልፍ ኒውስ እንደዘገበው፣ በተለያዩ የበረራ አገልግሎት መስመሮች በየቀኑ በግምት ከ500 በላይ የቤት ሠራተኞች ወደ ዱባይ የሚገቡ ሲሆን፣ በጉብኝት ቪዛ ገብተው እዚያው አገር ለሚገኙ ደላሎችና ኤጀንሲዎች ከፍ ያለ ገንዘብ በመክፈል ቪዛቸውን ወደ ‹‹የሥራ ፈቃድ›› አስቀይረው ይኖራሉ፡፡
ቀደም ሲል በሠራተኛነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚደረግ ጉዞን የኢትዮጵያ መንግሥት ማገዱ የሚታወስ ሲሆን፣ አዲስ አዋጅ ቢወጣም ሕጋዊ ጉዞ ነገ ዛሬ ይከፈታል ሲባል እስከ ዛሬ እንደተዘጋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በሕጋዊና በሕገወጥ መንገድ በአየርም በምድርም በርካታ ኢትዮጵያውያት ወደ አካባቢው መጓዝ አለማቆማቸው ይነገራል፡፡

No comments:

Post a Comment