Sunday, October 22, 2017

የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻ (False Flag Operation)


Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |


{{{ ኢትዮጵያውያን ሆይ፣ ንቁ! አሁን ወቅቱ የሽብር ነው! … “ሕወሓት ሰራሽ የሽብር ዘመቻዎች” ሊበረክቱ ይችላሉ፡፡ }}}

በናስሩዲን ኡስማን

ሕወሓት መራሹ መንግሥት አንድ በጣም የተካነበት “የቀውስ አፈታት ዘዴ” አለው ህዝብን ማሸበር! … የሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ፣ ሊመልስ የማይፈልገው ወይ የማይችለው ጠንካራ ጥያቄ ከህዝብ ሲቀርብለት፣ ወይም ህዝብ ሕጋዊ መብቱን ለማስከበር በአንድነትና በጽናት ሲታገለው፣ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “ሽብር ተኮር የቀውስ አፈታት ዘዴ”ን ይጠቀማል፤ ወይም ሚስጥራዊ የሽብር ዘመቻ ያካሂዳል፡፡ … አንድን ፖለቲካዊ ዓላማ ለማሳካት ሲባል በምሥጢር ተሸርቦ፣ በረቀቀ መንገድ የሚፈፀም እንዲህ ዓይነት የቀውስ መፍቻ ‹‹መንገድ›› … “የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻ” (False Flag Operation) በመባል ይታወቃል፡፡

የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻዎች የተለያዩ የፖለቲካ ዓላማዎችን ለማሳካት ሲባል ይፈፀማሉ፡፡
1. በሐሰተኛ ሰንደቅ ዘመቻ ለማሳካት ከሚፈለጉ ዓላማዎች አንደኛው፣ “በደለም፣ ገደለም የሰላም ዋስትናዬ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነው” ብሎ ሕዝቡ እንዲያምን ስነ ልቡናዊ ጫና መፍጠር ነው፡፡ ይህን ጫና ለመፍጠር የሕወሓት መራሹ መንግሥት የደኅንነት ክፍል የህዝብን ሰላም የሚያናጉ፣ ህዝቡን በጣም የሚያሸብሩና፣ ደኅንነት እንዳይሰማው የሚያደርጉ የተለያዩ የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻዎች ሊያቀናብር ይችላል፡፡ በሀገራችን ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት፣ የሕወሓት የደኅንነት ክፍል የሃይማኖት ማዕከላት (ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ) ማቃጠልን ጨምሮ፣ በርካታ የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻዎች አቀናብሮ ሥራ ላይ አውሏል፡፡ አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያን ወይም የመስጊድ መቃጠልን ያስከተሉ ሁከቶች በገለልተኛ አጣሪ ቡድን አልተመረመሩም፡፡ ……………… ለምን?

በሐሰት ሰንደቅ ዘመቻዎች የሰዎች ህይወት ይጠፋል፣ ንብረትም ይወድማል፡፡ ብዙዉን ጊዜ ፖለቲካዊ ዓላማን ለማሳካት ተብሎ የሚቀናበሩ የጥፋት ዘመቻዎችን ተከትሎ፣ በፊልም የተደገፈ የፕሮፖጋንዳ ዶክመንታሪ ይቀርባል፡፡ የሁከቱ መንስዔ በገለልተኛ አጣሪ ቡድን ሳይመረመር፣ በፕሮፖጋንዳ ዶክመንተሪዎቹ ላይ ለደረሰው የሰዎች ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም የሆነ ቡድን ተጠያቂ ይደረጋል፡፡ …
2. ሌላው የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻ ዓላማ፣ ህዝብ ለመብቱና ለነፃነቱ፣ ለፍትኅና ለዴሞክራሲ ወዘተ. የሚያደርገውን ሰላማዊ ትግል ማጠልሸት ነው፡፡ የሕወሓት የደኅንነት ክፍል ይህን ዓላማ ለማሳካት ሁለት ዓይነት መንገዶች ይጠቀማል፡፡ አንደኛው ሕጋዊ መብታቸውን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ በሚታገሉ ዜጎች መካከል የተደራጀ “የሁከት ግብረ ኃይል” በማሰማራት፣ ሰላማዊውን እንቅስቃሴ ወደ ሁከት መቀየር ሲሆን፣ ሁለተኛው መንገድ ራሱ ባደራጃቸው የሁከት ኃይሎች ህዝብን ሰላም የሚነሳ የሁከት ተግባር እንዲፈፀም ማድረግ ነው፡፡
3. ሦስተኛው የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻ ዓላማ፣ የመንግሥት ኢ ፍትኃዊ አገዛዝ አንገሽግሾት ተቃውሞውን እያሰማና የለውጥ ጥያቄ እያቀረበ ያለ ህዝብ ብሶቶቹን፣ ፍትኃዊ ጥያቄዎቹን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ “ሰላሙ እንዲጠበቅለት”፣ “የመንግሥት ያለህ!” ብሎ እንዲጮህ የሚያስገደድ ሁነት መፍጠር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ህዝቡ “ከፋም ለማ፣ ኢ ፍትኃዊም ቢሆን፣ የሰላሜ ዋስትና ይኸው መንግሥት ነው” ብሎ እንዲያምን አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የመንግሥት የደኅንነት ተቋማት ህዝቡ እንዲህ ያለ ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ በሚያካሂዱት የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ንብረቶችን (ለምሳሌ፣ የከተማ አውቶብሶችን ወዘተ.) የማቃጠል እና ከዚያም የከፋ እርምጃን ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ በዛሬው ዘመን፣ በሥልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ቡድን፣ ጥቅሙን ለማስጠበቅና የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም ሲል፣ ይህን መሰል ሸፍጥ መሥራቱ አዲስ ነገር ባይሆንም፣ አብዛኛው ህዝብ ግን መንግሥት እንዲህ ያለ ሥራ ይሠራል ብሎ አይጠረጥርም፡፡ …
4. ሌላው የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻ ዓላማ ህዝብን ከህዝብ ጋር ማቃቃር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ሰላም የሚነሳው ሕወሓት፣ ለብዙ ዓመታት ሲያናቁራቸው የኖሩት የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች፣ አንድነታቸውን እያጠናከሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ ሕወሓት ህዝብን ከህዝብ ጋር የማጣላት ዓላማዬን ያሳኩልኛል ብሎ የሚያምንባቸውን የሐሰት ሰንደቅ ዘመቻዎች ከማካሄድ ወደኋላ ይላል ብሎ ማሰብ በጣም የዋህነት ነው፡፡ በግሌ በቅርቡ በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጠረውን “ግጭት” በሐሰት ሰንደቅ ዘመቻ መነጽር ነው የምመለከተው፡፡
የግጭቱን መንስዔ በጥልቀት የሚመረምር ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ግጭቱ ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች ሄዶ፣ የገለልተኛ ምርመራ ሪፖርት እስካላቀረበ ድረስ ነገሩን በዚህ መነጽር ከማየት ውጪ ምን የተሻለ አማራጭ ይኖራል?!

No comments:

Post a Comment