Monday, October 23, 2017

በበደሌ ቡኖ የተከሰተው ግጭት ከተገለጸው በላይ መሆኑ ታወቀ


          


በኦሮሚያ ቡኖ በደሌ ዞን ውስጥ የተከሰተው ግጭት በመንግስት ከተገለጸው በላይ መሆኑን መረጃዎች አመለከቱ፡፡ በግጭቱ የተነሳ የሟቾች ቁጥር ተብሎ በመንግስት በኩል የተገለጸው 14 ሲሆን፣ ዛሬ ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ግን የሟቾችን ቁጥር 20 አድርሰውታል፡፡ በግጭቱ ከአማራውም ሆነ ከኦሮሞው ወገን የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት መረጃዎች፣ የአማራ ተወላጅ ሟቾች ቁጥር ግን ከፍ እንደሚል ይጠቅሳሉ፡፡ ግጭቱ የተካሔደው በገጀራ ጭምር መሆኑ ደግሞ የአሰቃቂነቱን ጥግ እንደሚያሳይ ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡
በግጭቱ ላይ አንዳንድ የኦሮሚያ ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች መሳተፋቸው ደግሞ፣ ግጭቱ በመንግስት አቀነባባሪነት ሆን ተብሎ የተፈጸመ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹ ወገኖች፣ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ደግሞ ሰመኑን በአማራ እና በኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ የተፈጠረው የአንድነት ስሜት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ይህ ሁኔታ መንግስትን በፍጹም አላስደሰተውም›› የሚሉት ታዛቢዎቹ፣ ይህን የአንድነት ስሜት ለማደፍረስ በቀጣይም በተለያዩ አካባቢዎች እንደኪሰቱ የሚደረጉ ግጭቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከወዲሁ ይናገራሉ፡፡
ስለ ግጭቱ የዘገቡ የገዥው ፓርቲ ልሳን የሆኑ ሚዲያዎች፣ ከዚህ ቀደም ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ ጉዳዩን በሰበር ዜና ጭምር በማጋጋል ሁለት ብሔሮች እየተጋደሉ እንደሚገኙ አድርገው መዘገባቸውን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ በመንግስት ሚዲያዎች እንዲህ ያለ አጋዳይ ዜና መስራት አስነዋሪ መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ጉዳዩንም በጽኑ አውግዘዋል፡፡ የዜናው አዘጋገብ መንግስት በሀገሪቱ የብሔር ግጭት እንዲነሳ ምን ያህል አሰፍስፎ እንደሚገኝ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በኦሮሚያ ቡኖ በደሌ ዞን ውስጥ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ፣ በአካባቢው ለዘመናት ሲኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል፡፡ ብዙዎችም ጥቃቱን ሽሽት ጫካ ውስጥ ተደብቀው እንደሚገኙ እና አስቸኳይ እርዳታ እንደሚሹ ከስፍራው እየወጡ ያሉ መረጃዎች በመጠቆም ላይ ናቸው፡፡ (BBN Radio)

No comments:

Post a Comment