Monday, October 23, 2017

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በነዳጅ ዋጋ ላይ አስደንጋጭ ጭማሪ እንደሚደረግ ታወቀ


  


(BBN) ከቀጣዩ የህዳር ወር ጀምሮ በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል ከወዲሁ ታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ የተደረገውን የብር ምንዛሪ ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ ዕቃዎች ላይ ጭማሪ መደረጉን መዘገባችን ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ከዚሁ የብር ምንዛሪ ለውጥ ጋር ተያይዞ የነዳጅ ዋጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ጀምሮ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ27 የኢትዮጵያ ብር እንዲመዘነር ተመን ካወጣ በኋላ፣ በሀገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ ንሯል፡፡

ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርትን ከውጭ የምታስገባ እንደመሆኗ፣ በየዓመቱ ለነዳጅ በቢሊዬን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ወጪ ታደርጋለች፡፡ ሀገሪቱ ወደ ሀገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶች በወጪ ረገድ ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዘው ነዳጅ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ምርቱ ግዥ የሚፈጸምበት በውጭ ምንዛሪ መሆኑ ደግሞ፣ ለነዳጅ የሚወጣውን ገንዘብ እጥፍ እንደሚያደርገው ይነገራል፡፡ ሀገሪቱ በዶላር ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጓን ተከትሎ፣ በቀጣይ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣው ገንዘብ የዚያኑ ያህል ከፍ እንደሚል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በተደረገው የብር ምንዛሪ ለውጥ መሰረት፣ ከዚህ ቀደም ሲወጣ በነበረው የነዳጅ ዋጋ ላይ የአስራ አምስት በመቶ ጭማሪ ሊደረግ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ለኑሮ ውድነት መከሰት ምክንያት ከሚሆኑ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ሲሆን፣ ዋጋው መጨመሩን ተከትሎ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ለውጥ ይደረጋል፡፡ ይህም ከክፍለ ሀገር ለሚመጡ እህሎች እና ሌሎች ዕቃዎች መጨመር ምክንያት እንደሚሆን የሚናገሩ ታዛቢዎች፣ ከቀጣይ ወር ጀምሮ ይደረጋል ተብሎ የታሰበው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፣ በሀገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ይበልጥ እንደሚያንረው ታዛቢዎቹ ይገልጻሉ፡፡ የብር ምንዛ ለውጥ ከተደረገ በኋላ በተለያዩ ሸቀጦች እና ዕቃዎች ላይ አስደንጋጭ የዋጋ ጭማሪ
መደረጉን መዘገባችን ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment