Thursday, October 26, 2017

በአማራነታቸው ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን እስረኞች ተናገሩ




በአማራነታቸው ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን እስረኞች ተናገሩ
” አማራ አህያ ነው። ግማሹ ደግሞ ጅብ ነው። አህያውን በጅብ እናስበላዋለን እያሉ ይደበድቡኝ ነበር።” ዘመነ ጌቴ
” እኔ የታሰርኩት አማራ ስለሆንኩ ነው። ማዕከላዊ አንተ ሆዳም አማራ እየተባልኩ ነበር የምመረመረው” ሰይድ ኑርሁሴን ሰይድ
(በጌታቸው ሺፈራው)

በአማራነታቸው ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ እስረኞች ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ገለፀዋል። ዛሬ ጥቅምት 16/2010 በዋለው ችሎት በርካታ ተከሳሾች አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን አብዛኞቹ በአማራነታቸው ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። በእነ ክንዱ ዱቤ መዝገብ 2ኛ ተከሳሽ የሆነው ዘመነ ጌቴ ” አማራ አህያ ነው። ግማሹ ጅብ ነው። አህያውን በጅብ እያስበላን ፀጥ እያደርገዋለን። እንኳን አማራን ሶማሊንም ፀጥ አድርገነዋል” እያሉ ይደበድቡት እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
“እኛ አማራ ወይንም ኦሮሞ መሆን ፈልገን አልተወለድንም። ግን በዘራችን ምክንያት በደል እየደረሰብን ነው” ያለው ዘመነ ማዕከላዊ በተፈፀመበት ድብደባ ጆሮ እና አይኑ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ገልፆአል። ” ማዕከላዊ የተሰበረው አጥንቴ፣ የተጎዳው አይንና ጆሮዬ ሳይድን አሁንም ቂሊንጦ እየተደበደብኩ ነው። የመኖር ዋስትና የለኝም” ብሏል። አቶ ዘመነ በአማራነቱ ጥቃት እየደረሰበት መሆኑን ሲገልፅ ዳኞች ሊያስቆሙት ሲሞክሮ ችሎት ውስጥ የነበሩት በኦነግና በግንቦት ሰባት የተከሰሱ እስረኞች “የተፈፀመውን ነው የሚናገረው። ይናገር!” እያሉ በማጉረምረም በአንድ ላይ በፍርድ ቤቱ ላይ ጫና ሲያሳድሩ ለመታዘብ ተችሏል።
ከአቶ ዘመነ ጌቴ በተጨማሪ በእነ ተሻገር ወልደሚካኤል ክስ መዘገብ 3ኛ ተከሳሽ የሆነው ተስፋሁን ማንዴ ” አማራ ደደብ ነው!” እየተባለ በማንነቱ እንዲሸማቀቅ መደረጉን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል። በዚሁ መዝገብ 6ኛ ተከሳሽ ሰኢድ ኑርሁሴን በበኩሉ ” እኔ የታሰርኩት በአማራነቴ ነው። ማዕከላዊ ሆዳም አማራ እየተባልኩ ተመርምሬያለሁ” ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሾቹ በደል ያደርሱባቸው የነበሩት የማዕከላዊ መርማሪዎች ችሎት ውስጥ እንዳሉ ገልፀው ሲያሸማቅቋቸው የነበሩ አካላት ችሎት ውስጥ መገኘት እንደሌለባቸው አመልክተዋል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ” እነሱን ችሎት ገብታችሁ አትከታተሉ የምንልበት ስልጣን የለንም” ሲል የእስረኞችን አቤቱታ ሳይቀበለው ቀርቷል።
በሌላ በኩል የወልቃይት ማንነት ጉዳይ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት እነ መብራቱ ጌታሁን አቃቤ ህግ ያቀረበው ማስረጃ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበር ቢሆንም ብይኑ አልተሰራም በሚል ለህዳር 11/2010 ተለወጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። 1ኛ ተከሳሽ መብራቱ ጌታሁን “እኛ በመታሰራችን ቤተሰቦቻችን ችግር ውስጥ ወድቀዋል” ብለዋል። በተጨማሪም ሀምሌ 5/2008 ጎንደር በተያዙበት ወቅት ፖሊስ የያዘባቸው ገንዘብ እንዳልተመለሰላቸውና ደረሰኝም እንዳልተሰጣቸው ገልፀዋል።
እነ ክንዱ ዱቤ ለህዳር 11 እንዲሁም እነ ተሻገር ወልደሚካኤል ለህዳር 15 / 2010 ተቀጥሮባቸዋል።

No comments:

Post a Comment