Thursday, October 26, 2017

” ከ2004 ጀምሮ እየተሰቃየን ነው። ገዳም እንዳንቀመጥ እየተደበደብን ነው” አባ ገ/ ስላሴ ወ/ሀይማኖት – (በጌታቸው ሺፈራው)


By ሳተናውOctober 26, 2017 19:44
    
እስር ቤት ውስጥ በደል እየተፈፀመባቸው መሆኑን የዋልድባ መነኮሳት ተናገሩ
“ማዕከላዊ ብዙ በደል ደርሶብናል። በአካልም በስነ ልቦናም ብዙ በደል እየደረሰብን ነው።” አባ ገ/ እየሱስ ኪ/ ማርያም


የ”ሽብር” ክስ ቀርቦባቸው ቂሊንጦ የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት እስር ቤት ውስጥ በደል እየተፈፀመብን ነው ሲሉ ዛሬ ጥቅምት 16/2010 ዓም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አመልክተዋል። መነኮሳቱ ማዕከላዊ እስር ቤት ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ከአሁን ቀደም መግለፃቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን በሚገኙበት ቂሊንጦም በደል እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
አባ ገ/ እየሱስ ኪ/ ማርያም “ማዕከላዊ ብዙ በደል ደርሶብናል። በአካልም በስነ ልቦናም ብዙ በደል እየደረሰብን ነው። ፀሎት እንዳናደርግ ተከልክለናል። የሚመጣልንን አንድ ስሃን ምግብ ጠያቂ ከሌላቸው ወንድሞቻችን ጋር እንዳንበላ፣ አብረን እንዳንቀመጥ ተከልክለናል። ጨለማ ቤት ትገባላችሁ እየተባልን ነው። በደል የሚፈፅምብን ኦፊሰር ካህሱ የተባለ የዞን 3 ኃላፊ ነው!” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች በየ ስብሰባው መነኮሳቱ አመፀኞች ናቸው እያሉ ስማቸውን እንደሚያጠፉም እና ” ብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ስማችሁን አስመዝግቦናል” ብለው ክትትል ውስጥ ስለመሆናቸው እንደነገሯቸውም ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። ከኦፊሰር ካህሱ በተጨማሪ ኢንስፔክተር አበበ የተባለ ኃላፊ በደል እንደሚፈፅምባቸው በአቤቱታው ተገልፆአል።
አባ ገ/ ስላሴ ወ/ሀይማኖት በበኩላቸው ዘመድ እንደሌላቸው፣ ገዳም የገቡት አፅመ ቅዱሳንን ወገን አድርገው እንደሆነ ገልፀዋል። “አፅመ ቅዱሳን በዶዘር ሲፈርስ እና የገዳሙ ደን ተጨፍጭፎ ከሰል ሲሆን አቤቱታ ብናቀርብም ማንም ሊሰማን አልቻለም” ያሉት አባ ገ/ስላሴ አቤቱታ በማቅረባቸው ከ2004 ዓም ጀምሮ በደል ሲፈፀምበቸው እንደቆየና ገዳም ውስጥ እንዳይቀመጡም ድብደባ ይፈፀምባቸው እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ባሉበት እስር ቤትም ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን የገለፁት አባ ገ/ስላሴ ” ሀገራችን መንግስት ሳይሆን እግዚያብሄር ነው የሚጠብቃት” ብለዋል።
የመነኮሳቱ ጠበቃ አምሃ መኮንን በበኩላቸው “ደንበኞቼን እያስፈራሯቸው ነው። ስብሰባ ላይም እጅ የሚጠቆመው ወደ እነሱ ነው። የተለየ እንቅስቃሴ አለ ተብሎ በታሰበ ቁጥር እነሱ ከበስተጀርባ አሉበት ይባላሉ።” ሲሉ በመነኮሳቱ ላይ የሚፈፀመውን ወከባና በደል ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

No comments:

Post a Comment