በልማት ስም ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ለንብረታቸው እና ለመሬታቸው በቂ ካሳ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡ ጥናቱን ያደረገው ራሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እያለ የሚጠራው አካል ሲሆን፣ ባደረኩት ጥናት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ብሏል፡፡ በልማት ስም እየተነሱ የሚገኙ እና ከዚህ በፊትም የተነሱ ዜጎች፣ ለንብረታቸው በቂ ካሳ ያለመክፈል፣ ምትክ ቦታ እና መኖሪያ ቤት ያለመስጠት ችግር በሰፊው እንደሚስተዋልም ተገልጿል፡፡
ጥናቱ ተደረገ የተባለው አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ በተጠቀሱት ቦታዎች ሰፊ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምም ተወስቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተለይ ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ እየተባለ በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች መፈናቀላቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በአብዛኛው ገበሬዎች ተፈናቅለው ፋብሪካ ይገነባባቸዋል ከተባሉ ቦታዎች አብዛኞቹ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የፋብሪካ ግንባታ እንዳልተደረገባቸው ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ፣ የፋብሪካ ግንባታ ተጀምሮባቸው ሳይጠናቀቁ ስምንት እና አስር ዓመት መፍጀታቸውንም ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኮሚሽኑ አጠናሁት ያለው ጥናት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየውን ሐቅ መልሶ ከማስተጋባት በቀር ምንም አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም፡፡ ጥናቱ ተደረገ ቢባልም፣ በጥናቱ መሰረት በልማት ስም የመብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ለተባሉ ወገኖች የተደረገ ማስተካከያ የለም፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የመብት ጥሰት በፈጸሙ አካላት ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመወሰዱ፣ የአሁኑ ጥናት ጉንጭ አልፋ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ተጎጂዎች እንዲካሱ የማያደርግ ጥናት ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ዋጋ እንደሌለውም ታዛቢዎቹ ያክላሉ፡፡ (BBN News 10/5/17)
No comments:
Post a Comment