Sunday, October 29, 2017

በአርባምንጭ ከተማ ሲቃላ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ምንጮች ገልጹ።

ኢሳት ዜና(ጥቅምት 18/2010 ዓም)
በአርባምንጭ ከተማ ሲቃላ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ምንጮች ለኢሳት ገልጹ። በከተማዋ 03 ቀበሌ ድልፋና አዳራሽ 50ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የካድሬዎች መሰብሰቢያ ማዕከል ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ያደረስው ጉዳት መጠነኛ ቢሆንም የአከባቢውን የመንግስት ሃላፊዎች ማስደንገጡን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ማንነታቸው ባልታወቁ ሃይሎች በተወረወረው አንድ ቦንብ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳላደረሰም ታውቋል። ወዲያውኑ አከባቢው በፌደራል ፖሊስና በልዩ ሃይል የተከበበ ሲሆን በጥርጣሬ የተወሰኑ ወጣቶች መታፈሳቸውን ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል በአርባምንጭ የኒቨርሲቲ የሁሉም ግቢዎች የጸጥታ ሃላፊ በሆኑት በሻለቃ አበበ ላይ ባልታወቁ ሃይሎች በተፈጸመ ጥቃት ለህይወት አስጊ በሆነ ጉዳት ሆስፒታ...ል መግባታቸው ተገለጸ። ከስፍራው በደረሰን መረጃ ላይ እንደተጠቀሰው፡ ከህወሀት የደህንነት መስሪያ ቤት ጋር በቀጥታ የሚሰራ ይህ ግለሰብ በተለይ የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎችን በማሰር፡ በማሰቃየት የሚታወቅ ሲሆን በዩንቨርሲቲ ግቢዎች የመንግስት ተቃዋሚ ናቸው ያላቸን በማሳደድ የሚያዋክብ እንደሆነም ታውቋል። ዛሬ ጠዋት በሻለቃ አበበ ላይ በስለትና በድብደባ በተፈጸመበት ጥቃት ወደ አርባምንጭ ሆስፒታል መግባቱን ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና ዛሬ በባህርዳር የወጣቶች የስራ ፈጠራ ኤግዚቢሽን በመካሄድ ላይ እንዳለ ምንነቱ ያልታወቀ ተኩስ በመከፈቱ ዝግጅቱ መቋረጡን አሁን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የተኩሱ ምንነትና ማን እንደሚተኩስ የታወቀ ነገር የለም። ከኢግዚቢሽኑ ቦታ በመቶ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ቤቶች ላይ ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገም ነው ተብሏል።

No comments:

Post a Comment