By ሳተናው
ስዩም ተሾመ
ይህ “ከከፍተኛ የደህንነት ኃላፊዎች አፈትልኮ ወጣ” የተባለው መረጃ ለመጀመሪያ ግዜ የደረሰኝ ባለፈው ሳምንት ሲሆን የስልክ ቃለ ምልልስ ይህን ማያያዣ (Link) በመጫን ማዳመጥ ይቻላል። በተደጋጋሚ እንዲህ ያለ የማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ስለሚደርሰኝ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም። ባለፈው ሳምንት መረጃውን ያደረሰኝ ግለሰብ ትላንትም በድጋሜ ከአሜሪካ በቀጥታ የስልክ መስመር ደውሎ ስለሁኔታው በዝርዝር ገለፆልኛል። ከግለሰቡ ጋር ያደረኩትን የስልክ ቃለ ምልልስ ቀድቼዋለሁ። ሁለተኛውን የስልክ ቃለ ምልልስ ይህን ማያያዣ (Link) በመጫን ማዳመጥ ይቻላል፡፡
ከላይ የቀረቡት የስልክ ቃለ ምልልሶች የድምፅ ጥራታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ የቃለ ምልልሱን ዋና ሃሳብ እንደሚከተለው በአጭሩ እገልፃለሁ። ከላይ የተጠቀሰው ግለሰብ ከከፍተኛ የደህንነት ኃላፊዎች እና የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር ቅርበት እንዳለው ይናገራል። ለምሳሌ፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ሬድዋን ሁሴን እና ከከፍተኛ የደህንነት ሃላፊዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ እንደሚወያይ ገልጿል፡፡ ይህ ውስጥ አዋቂ እንደሚለው፣ በሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ፣ እኔን ጨምሮ በሦስት ፀሃፊዎች ላይ “መወገድ አለባቸው” የሚል ትዕዛዝ መተላለፉን ገልጿል። ከላይ ከተጠቀሰው ግለሰብ በተጨማሪ፣ ለደህንነት ሰዎች ቅርበት ያላቸው ሌሎች ጓደኞቼ “ስዩም ተሾመ መወገድ አለበት” የሚለው ውሳኔ መተላለፉን እንደሰሙ በመጠቆም ስጋታቸውን ገልፀውልኛል።
ይህን ከመስማቴ በፊት፣ ትላንት ጠዋት ብዙ የፌስቡክ ጏደኞቼ ከአሉላ_ሰለሞን ገፅ ላይ የተወሰደ ምስል ልከውልኝ ነበር። ከታች እንደሚታየው አቶ አሉላ ሰለሞን እኔ እንድታሰር በይፋ ጥሪ አቅርቧል። ውስጥ አዋቂው “ከአሉላ ሰለሞን ጋር እንዴት ስዩም ተሾመ ይወገድ ትላለህ” ብሎ ለረጅም ሰዓት እንደተከራከረው በመግለፅ ከፅሁፉ በስተጀርባ ያለውን እውነታ፣ በተለይ የአቶ አሉላ ሰለሞን የፖለቲካ አቋም በግልፅ ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት፣ አቶ አሉላ ሰለሞን እንደ እኔ የተለየ አቋምና አመለካከት የሚያራምዱ ግለሰቦችን ያለምንም ጥፋትና ማስረጃ እንዲታሰሩ በይፋ ጥሪ ከማቅረብ ጀምሮ ያለፍርድ “መገደል አለባቸው” ብሎ እንደሚከራከር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ህግ በሰፈነበት አሜሪካን ሀገር ተቀምጦ በኢትዮጲያኖች ላይ የሽብር ወንጀል እንዲፈፀም ጥሪና ቅስቀሳ እያደረገ እንደመሆኑ በህግ ሊጠየቅ ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment