(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 17/2010)ፈረንሳዊው ፍራንሷ ጂራርድ ዘመቻ ማካሄጃ መረብ በመክፈት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የያዙትን ሃልፊነት እንዲለቁ በአለም አቀፍ ደረጃ ዘመቻ ጀመረ። ዘመቻውን በተለያዩ አለም የሚገኙ ነዋሪዎችና ኢትዮጵያውያን እየደገፉት መሆኑም ታውቋል። ዶክተር ቴድሮስ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ዘመቻ የተከፈተባቸው የዚምባቡዌውን ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ለአለም ጤና ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው መሾማቸውን ተከትሎ ነው። በቅርቡ የዚምባቡዌውን ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ለአለም ጤና ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው በመሾማቸው ከፍተኛ ነቀፌታና ትችት የደረሰባቸው የጤና ድርጅቱ ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የያዙትን ሃላፊነት እንዲለቁ በአለም አቀፍ ደረጃ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነው። በተባለው የዘ...መቻ ማካሄጃ መረጃ መረብ ዘመቻውን የጀመረው አንድ በፈረንሳይ ፓሪስ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ሲሆን ዘመቻውን በፍጥነት በተለያዩ አለም የሚገኙ ነዋሪዎችና ኢትዮጵያውያን እየደገፉት ይገኛል። ፈረንሳዊው ፍራንሷ ጂራርድ ዘመቻውን ለምን እንደጀመረ ላይ በሰጠው ማብራሪያ በሰብአዊ መብት ረገጣና ሀገራቸውን ከዳቦ ቅርጫት ወደ ባዶ ቅርጫት የቀየሩትን እንዲሁም በሀገራቸው የጤና ጥበቃ ማሽቆልቆል ተጠያቂ የሆኑትን የዚምባብዌውን ፕሬዝዳንት ለበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት በማጨታቸውና ዶክተር ቴድሮስ ለያዙት ቦታ የማይመጥኑና የድርጅቱን ክብርና ዝና የሚጎዱ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲለቁ ይጠይቃል። የዘመቻው ጀማሪ ጨምሮ እንዳስታወቀው ዶክተር ቴድሮስ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የማይለቁ ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ መንግስታት ለእርሳቸው ያላቸውን የድጋፍና የእውቅና ድምጽ እንዲነፍጓቸው ዘመቻ እንደሚከፈት አስጠንቅቋል። ሌሎች በተለያየ አለም የሚገኙ የተለያየ ዜግነት ያላቸው የዘመቻው ደጋፊዎች እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ዘመቻውን በመፈረም ባሰፈሩት አስተያየት ዶክተር ቴድሮስ በህገወጥ ጅምላ ግድያ፣እስራት እንዲሁም ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በማሰርና በማሰቃየት ተጠያቂ የሆነው የህወሃት ቡድን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ በመሆናቸው እንዲሁም የሳንባ ነቀርሳና ኤች አይ ቪን ለመከላከል ከአለም አቀፍ ተቋማት የተሰጠን ገንዘብ በማባከን የሚጠየቁ በመሆናቸው የአለም ህዝቦች ጤናንና ደህንነትን የሚያስተዳድር ተቋም ሃላፊ ለመሆን ብቁ አይደሉም ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። በአለም አቀፍ የፖለቲካ ትንተናቸውና እንዲሁም በሲ ኤን ኤን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አስተያየት በመስጠት የሚያውቁት ፍሪዳ ጊቲስ ረቡዕ በዋሽንግተን ፖስት ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የዶክተር ቴድሮስ የማመዛዘንና የመወሰን አቅም ሙጋቤን በማጨታቸው ብቻ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ብለዋል። ጸሀፊው ሲቀጥሉም ዶክተር ቴድሮስ ሙጋቤን ማጨታቸው ምናልባትም የሙስና ውጤት ሊሆን ስለሚችል መመርመር አለበት ብለዋል። ጊቲስ እንዳሉት ዶክተር ቴድሮስ የአፍሪካ ብቸኛ እጩ መሆናቸው ሁሉንም ያስደሰተ ጉዳይ አልነበረም ምክንያቱም አሉ ጸሀፊዋ ዶክተር ቴድሮስ የአንድ ጨቋኝ አገዛዝ አመራር አባል የነበሩና አገዛዙም ንጹሃንን በማሰቃየትና ምርጫን በማጭበርበር የሚታወቅ ነው ብለዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ያሉ ችግሮችን በማጋለጥ ስራ የሚታወቀው ዩ ኤን ዋች የተባለው ድርጅት ሃላፊ ሂለል ኑወር እንዳሉት ደግሞ ዶክተር ቴድሮስ ለድርጅቱ ሃላፊነት ቦታ በሚወዳደሩበት ወቅት ሙጋቤ የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር እንደነበሩና ለዶክተር ቴድሮስ መመረጥ ድጋፍ እንዳደረጉ አስታውሰው አሁን ዶክተር ቴድሮስ መልሰው ሙጋቤን ለበጎ ፍቃድ አምባሳደርነት ማጨታቸው ውለታ ለመመለስ መፈለጋቸው ግልጽ ነው ብለዋል። ዶክተር ቴድሮስ ከሳምንት በፊት ሙጋቤን ማጨታቸውን ተከትሎ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችና ሀገራት መሪዎች ተቃውሟቸውን መግለጻቸው ይታወቃል። የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ አላስፈላጊ የአፕሪል ዘፉል ቀልድ መስሎኝ ነበር ሲሉ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በትዊተር እንዳስታወቀው የዶክተር ቴድሮስ ሙጋቤን ማጨት እጅግ አስደንጋጭ ነበር በመሻሩም እፎይታ ተሰምቶናል ብለዋል። እናመሰግናለን WHO ሁለተኛ ግን እንዳይደገም ይላል ባለፈው ሳምንት በዚምባቡዌ የአለም ጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት አጥር ላይ የተጻፈ መልዕክት። ዩ ኤን ዋች የተባለው ተቋም በሳምንቱ መጀመሪያ በዶክተር ቴድሮስ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ መጠየቁ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment