ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል ለማክበር ቢሾፍቱ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። ነገ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አምቦ እና ጅማን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች እንግዶች ወደ ቢሾፍቱ እየገቡ ነው። የጸጥታ አስከባሪዎች አስለቃሽ ጭስ የሚተኩሱ መሳሪያዎች ታጥቀው ይታያሉ። በከተማዋም ጥብቅ ጥበቃ በማድረግ ላይ ናቸው። በከተማ አደባባዮች በባህላዊ ልብሶች ያጌጡ የአካባቢው ነዋሪዎች እና እንግዶቹ ይታያሉ። መዝናኛ ቤቶች እርጥብ ሳር (ቄጤማ) ጎዝጉዘዋል። በዓሉ የሚከበርበት የሆራ አርሰዲ ሐይቅ አቅራቢያን ጨምሮ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ኢሬቻን የሚዘክሩ ማስታወቂያዎች ተሰቅለዋል። ወጣቶችም ጽዳት በማካሔድ ላይ ይገኛሉ። ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ ወደ ከተማዋ የሚዘልቁ እንግዶች እና መንገደኞች ከሚጓዙበት ተሽከርካሪ ወርደው በጸጥታ ኃይሎች ይፈተሻሉ። የከተማዋ ነዋሪዎች የምሥጋናው በዓል እንደ ባለፈው ዓመት ተቃውሞ ሊደመጥበት ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ለዶይቼ ቬለ ወኪል ተናግረዋል። (ፎቶ-ከተስፋለም ወልደየስ ማኅደር)
No comments:
Post a Comment