Thursday, September 28, 2017

በእሬቻ በዓል ላይ የመንግስት ባለስልጣናት ንግግር አያደርጉም ተባለ



 

(ኢሳት ዜና–መስከረም 18/2010) ዕሁድ በሚከበረው የእሬቻ በዓል ላይ የመንግስት ባለስልጣናት ንግግር እንዳያደርጉ መወሰኑን የኦሮሚያ አባገዳዎች ምክር ቤት አስታወቀ።
በበዓሉ ላይ መሳሪያ የታጠቀ የመንግስት ሃይል እንደማይኖርም የኦሮሚያ አባገዳዎች ምክር ቤት ማስታወቁንም የቢቢሲ አማርኛው ክፍል ዘግቧል።
በበዓሉ ላይ የመንግስት ሰዎች ንግግር እንዳያደርጉና ታጣቂዎች በስፍራው እንዳይኖሩ የተላለፈው የአባገዳ ምክር ቤት ውሳኔ የባለፈው ዓመት ዕልቂት ተጠያቂው ማን እንደሆነ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ለተገደሉት ወገኖች መታሰቢያ በመንግስት በቆመው ሀውልት ላይ ‘በድንገት የሞቱ ‘በሚል የተጻፈው ጽሁፍም እንዲፋቅ መደረጉ ታውቋል።
ምክር ቤቱ ቅዳሜ በዋዜማው ባለፈው አመት ለተገደሉት ወገኖች የህሊና ጸሎት እንደሚደረግ አስታውቋል።
መንግስት የተገደሉት ከ50 አይበልጡም ይላል። የዓይን እማኞችና የሆስፒታል ምንጮች ቁጥሩ በትንሹ ከ500 የሚልቅ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በዕለቱ ህይወታቸውን ያጡት በድንገት ነው የሚለው የመንግስት መግለጫ ግን ለብዙዎች አስደንጋጭ ነበር። ከምንም በላይ ይህን አገላለጽ ለተገደሉት ወገኖች በቆመው ሀውልት ላይ እንዲሰፍር መደረጉ ተጠያቂነት ከመሸሽ ባሻገር ታሪክን አጣሞ ለማኖር የሚደረግ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው የሚለው ተቃውሞ ከየአቅጣጫው ሲሰማ ነው የሰነበተው።
በእሬቻ በዓል ለተገደሉት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ተጠያቂ የሆነው መንግስት ራሱ ሀውልት ማቆሙ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየ ሲሆን የበዓሉ ጊዜ መቃረቡን ተከትሎ ጉዳዩ ትኩረትን አግኝቷል። በቅርቡ ከቦረና ኢትዮጵያ በስደት እዚህ አሜሪካን የመጡት አቶ ኡቱካና መሎ ራሱ ገድሎ ሀውልት ያቆመውን የህወሀት መንግስትን ድርጊት ከአንድ የጀርመን የጦር ጄነራል ታሪክ ጋር ያነጻጽሩታል።
ዕልቂት ከተፈጸመበት ቦታ ርቆ የቆመው ሀውልት ላይ የሰፈረው መልዕክት ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል።
ያለቁት ወገኖች የተገደሉበትን ምክንያት ዓለም በቅርበት እየታዘበው በመንግስት በኩል በድንገት የተፈጸመ የሚል መግለጫ በሀውልቱ ላይ መቀመጡ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
ሆኖም የኦሮሚያ አባገዳዎች ምክር ቤት ለቢቢሲ አማርኛ እንደገለጸው በድንገት የሚለው በመታሰቢያ ሀውልቱ ላይ የተጻፈው መግለጫ እንዲፋቅ ተደርጓል። አቶ ኡቱካና መሎ ግን መፋቅ ያለበት ቃሉ ብቻ አይደለም ይላሉ። ሀውልቱም መፍረስ አለበት።
የፊታችን ዕሁድ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል መሳሪያ የታጠቀ ሰው በአካባቢው እንደማይኖር የኦሮሚያ ክልል መንግስት ቀደም ሲል ያስታወቀ ሲሆን የአባገዳዎች ምክር ቤትም ይህንኑ አረጋግጧል።
300 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የአካባቢው ጸጥታ የሚያስክብሩ መመረጣቸውን የገለጸው የአባ ገዳዎች ምክር ቤት መንግስት በበዓሉ ምንም ድርሻ አይኖረውም ሲል አስታውቋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበዓሉ ላይ ንግግር እንደማያደርጉም ተገልጿል። የመንግስት ታጣቂዎች በቦታው እንዳይታዩና ባልስልጣናትም ንግግር እንዳያደርጉ መወሰኑ ለባለፈው ዓመት ዕልቂት ተጠያቂው ምን እንደሆነ ማረጋገጭ ይሰጣል ይላሉ አቶ ኡቱካና መሎ።

No comments:

Post a Comment