Sunday, September 24, 2017

የስኳር ፋብሪካዎች በመለዋወጫ ዕቃ እጦት ስራ አቁመዋል


Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |


 


በኢትዮጵያ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች በመለዋወጫ ዕቃ እጦት ስራ ማቆማቸው ተጠቆመ፡፡ የቢቢኤን ምንጮች እንደጠቆሙት፣ መተሐራ፣ ፊንጫ እና ወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች ለጥገና ተብለው ስራ ካቋረጡ ሳምንታት ቢቆጠሩም፣ መንግስት የመለዋወጫ ዕቃ ማቅረብ ባለመቻሉ ስራ ፈትተው ቆመዋል፡፡ የፋብሪካዎቹ ሰራተኞች መንግስት የመለዋወጫ ዕቃ እንዲያቀርብላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

የስኳር ፋበሪካዎቹ የተገጠመላቸው ቦይለር ጥገና እንደሚያስፈልግው የገለጹት የስኳር ፋበሪካው ሰራተኞች፣ በተጨማሪም የተርባይን ግዢ ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዳልሰጣቸው ሰራተኞቹ አክለው ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው እና ጥያቄ የቀረበለት የስኳር ኮርፖሬሽን ፋብሪካዎቹ ላቀረቡለት ጥያቄ ምላሽ ያልሰጠው በምን ምክንያት እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ምንጮች እንደሚጠቁሙት፣ ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹ ለሚያስፈልጋቸው የመለዋወጫ እና የጥገና ዕቃዎች ምላሽ ያልሰጠው በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ነው፡፡ የመለዋወጫ ዕቃዎቹ በአብዛኛው ከውጭ የሚገዙ እንደመሆናቸው፣ ሀገሪቱ አሁን ካለባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንጻር ፋበሪካዎቹ የሚያስፈልጋቸውን የጥገና ዕቃ ማቅረብ አልተቻለም፡፡

በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የስኳር እጥረት መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንድ ኪሎ ስኳር እስከ 60 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ የሚገልጹት መረጃዎች፣ መንግስት ለህብረተሰቡ ማቅረብ ያለበትን ያህል ያስኳር ፍጆታ እያቀረበ እንዳልሆነም ከመረጃዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በሀገሪቱ የስኳር እጥረት በተከሰተበት በዚህ ሰዓት መንግስት ወደ ኬንያ ስኳር መላኩ ተቃውሞ ሲያስነሳበት የከረመ ሲሆን፣ ወደ ኬንያ የተላከው ከ44 ሺህ በላይ ስኳርም ተረካቢ አጥቶ ሞያሌ ድንበር ላይ ጸሐይ እና ዝናብ እየተፈራረቀበት ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment