ኢሳት ዜና–መስከረም 11/2010) የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚሰራጩ የመገናኛ ብዙሃን ይዘቶች ብሔሮችን ከብሔሮች ጋር የሚያጋጩና ጦርነት ቀስቃሽ ናቸው በማለት አስጠነቀቀ። በህወሃቱ ነባር ካድሬ አቶ ዘርአይ አስገዶም ፊርማ የወጣው ማሳሰቢያ በጥቅል የተቀመጠና ዝርዝር ይዘት የሌለው በመሆኑ ሆነ ብሎ ጋዜጠኞችን ለማሸማቀቅና ለማስፈራራት የወጣ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በኦሪገን ዩኒቨርስቲ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዕጩ ዶክተርና መምህር አቶ እንዳልካቸው ሃይለሚካኤል ለኢሳት እንደገለጹት ከዚህ ማሳሰቢያ በኋላ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች ይኖራሉ። በህወሃት ነባር ካድሬ ዘርአይ አስገዶም የሚመራው የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን በሚሰራጩ ይዘቶች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ስለማሳሰብ በሚል ርዕስ ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ...ያሰራጨው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አገዛዙ የገባበትን አጣብቂኝ እንደሚያመለክት ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ የዘርፉ ሙያተኞች ገልጸዋል። በኦሪገን ዩኒቨርስቲ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዕጩ ዶክተርና መምህር አቶ እንዳልካቸው ሃይለሚካኤል ለኢሳት እንደገለጹት የተላለፈው መመሪያ በስራ ላይ ካለው ህገ-መንግስት አንቀጽ 29 ጋር የሚጻረር፣ጥቅልና ለማንኛውም አይነት ትርጉም ክፍት ነው ብለዋል። እንዲህ እንዲሆን የተፈለገው ሆን ተብሎ በታቀደ ሁኔታ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱንና ጋዜጠኞችን ለማስፈራራት፣ለማጥቃትና መረጃ ለማፈን በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይ በአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት፣በአዲስ አበባ በሚተላለፉ የኤፍ ኤም ሬዲዮኖችና በኦሮሞ ጉዳይ ትኩረት የሚያደርጉ እንደ ኦ ቢ ኤን ያሉ የግል መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ደፈር ማለት የጀመሩትን ጋዜጠኞች ከስራ ለማባረርና ለማሰር የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል። በግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ለብሮድካስት ባለስልጣን ቦርድ ሰብሳቢ የተላከው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የባለስልጣኑ የስራ አመራር ቦርድ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ በአብዛኛው የህዝብ ብሮድካስተሮች በተለያየ ደረጃ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መግለጫዎችንና ዘገባዎችን የማሰራጨት አደገኛ አዝማሚያ መታየቱን ያትታል። ማንኛውም ብሮድካስተር ከየትኛውም አካል የተገኘን ምንጭ በመጠቀም በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ የሚፈጥሩና ግጭትን የሚቀሰቅሱ መግለጫዎችን በማንኛውም የመረጃ ማሰራጫ ዘዴ ማሰራጨትም በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስጠንቅቋል። በብዙ ኢትዮጵያውያንና አለም አቀፍ ተቋማት በአፋኝ ህግነቱ ተጠቃሽ ከሆነው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅን መሰረት በማድረግ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ የህወሃትን የመገናኛ ብዙሃን ሞኖፖሊ ለማጠናከር የታሰበ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። ይህም ቀስ በቀስ የህዝብ ድምጽ ለማፈንና የጋዜጠኞች አንደበት እንዲዘጋ ለማድረግ የታለመ ነው ተብሏል።
No comments:
Post a Comment