Wednesday, September 20, 2017

ግዜ እየጠበቀ የሚፈነዳው የመለስ ቦንብ – ይገረም አለሙ


Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |


 


ሰሞኑን ከምሥራቁ የሀገራችን አካባቢ የምንሰማው ወሬ ሰው ለሆነ ፍጡር ሁሉ ለአእምሮ የሚከብድ ነው፡፡ ሁል ግዜ ነገሮች አዲስ ለሚሆኑባቸው ትናንትን በመርሳት ስለነገም በማሰብ ለማይደክሙ ለእለት ለእለቱ ብቻ ለሚጮሁት ካልሆነ በስተቀር ይህ አሁን እየተፈጸመ ያለው ነገር መች እንደሚሆን ለማወቅ አልተቻለ ካልሆነ በስተቀር አንድ ቀን ያውም ከዚህ በከፋ መልኩ ሊፈጸም እንደሚችል ወያኔ ሥልጣን በያዘ ማግስት የተረዱ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ጩኸዋል፣ ስጋታቸው ገልጸዋል፣ ፍራቻቸውን ሊያጋሩን ሞክረዋል፡ማን ሰምቶ እንጂ፡፡

የጎሳ ፌዴራሊያዊ አከላለል ጉዳየ ሲወሳ በተለይም የሶማሊ ጉዳይ ሲነሳ የሚታወሱኝ መቼም ልረሳቸው የማልችልና በተለያየ ግዜ የጠቀስኳቸው አጭሩ ቀጭኑ ልበ ደንዳናው ደፋሩ ሀገር ወዳድ አንደበተ ርቱኡው ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ ናቸው፡፡ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በተመራው የህገ መንግሥት ጉባኤ በህዝብ ተመርጠው ተካፋይ ነበሩና የክልሎችን ስያሜ ሲጸድቅ አባቶቼ እናቶቼ ወንድሞቼ ጌቶቼ እባካችሁ የክልሎችን አከላለልና ስያሜ ሲሆን በዚህ መልኩ ባናደርገው አይሆንም ካላችሁ ደግሞ የሶማሌ ክልል መባሉ ቀርቶ ነገ የሚሆነው አይታወቅምና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ቢባል በማለት ላቀረቡት ተማጽኖ የወረደባቸው ውርጅብኝ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በፖለቲካ ስካር ከናወዘ አእምሮና በጎሰኝነት ስሜት ከተከፈተ አንደበት ይወጡ የነበሩ ቃላቶች ሻ/ቃ አድማሴን ማሸማቀቅም ሆነ ከአቋማቸው ዘነፍ ማድረግ ባይችሉም ሂደቱን በቴሌቨዥን ለተከታተለው የሚያሳፍርና የሚያበሳጭ ነበር፡፡ ሻ/ለቃን አድንቀን በሌሎቹ አፍረንና ተናደን የአንድ ሳምንት የቡናና የድራፍት ቆይታ ማድመቂያ ከማድረግ አልፈን ተንገሽግሸን ያደረግነው ነገር የለም እንጂ፡፡ ያን የተናገሩና ለተናጋሪዎቹ ያጨበጨቡ በዛ አዳራሽ ታድመው የነበሩ ሁሉ መቼም ሰው በሚለው የወል መጠሪያ የሚጠሩና ቢጠቀሙበትም ባይጠቀሙበትም ከትከሻቸው በላይ የተጎለተ ጭንቃላት ያላቸው ናቸውና ዛሬ የሚፈጸመውን እልቂት ሲያዩ ሲሰሙ ምን ብለው ይሆን! ዶ/ር ነጋሶ በግዜ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ የጠየቁ በደላቸውንም ተናዘው ንስሀ የገቡ በመሆኑ ከላይ የገለጽኩት አባባል አይመለከታቸውም፡፡
በታሪክ የሚታወቀው ቅኝ ገዚዎች ነበሩ የሚገዙትን ሀገር ለቀው ሲሄዱ በእጅ አዙር ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ሀገሪቱንም በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ለመግዛት እንዲያስችላቸው ግዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ቦንብ በመቅበር የሚታወቁት፡፤ የታላቋ ሶማሊያ ቅዠት የእንግሊዝ ውጤት ነውና ለዚህ በአብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ወያኔ ምንም እንኳን ከመነሻው ዓላማ አድርጎ የታገለው የትግራይ መንግሥት ለመሆን ቢሆንም እድል ቀንቶት የአለም ሁኔታ ማለት የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ረድቶት፣ የእኛም እኛነት አግዞት ለትንሽ ዓላማ ተነስቶ ትልቅ ድል ከተቀዳጀና ኢትዮጵያን ለመግዛት ሲበቃ ለወንበሩ ማስጠበቂያ ለስልጣን ዘመኑ ማረዘሚያ የተለያዩዩ ነገሮችን ሊጠቀም ቢችልም ይህን በቅን ገዚዎች ሲፈጸም የኖረ ግዜ አየጠበቀ የሚፈነዳ ቦንብ በሚገዛት ሀገር ያውም በሥልጣን ላይ እያለ መቅበሩ የወያኔን ማንነት የእያንዳንዳቸውንም ወያኔዎች ምንነት የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ የዚህ አይነቱ መሰሪ ስራ ቀማሪና ቆማሪ የነበረው በዚሁ እኩይ ተግባሩ በአጭር የተቀጨውን መለስ ዜናዊ ማንነት በገሀድ የሚያሳይ ነው፡፡
የሚያሳዝነው የሚያስተዛዝበውና ቀን ሲወጣ የሚያፈራርደው ይህን እኩይ ተግባር የፈጸመን ሰው ታላቅ ተግባር የከወነ ኢትዮጵያዊ መሪ እያሉ የሚያሞካሹ ለጋሲውን እናስቀጥላልን እያሉ እሱ ቆላልፎት የሄደውን የሴራ መንገድ በማያቁበትና በማይችሉት መንገድና ሁኔታ አናስኬዳለን እያሉ ሀገር እያወደሙ ህዝብ እየጫረሱ ያሉት ሰዎች ናቸው፡፡ በተለይ ከህውኃት ውጪ ያሉ ሰዎች ቢያንስ በዚህ አንድ አመት የደረሰው ጥፋት እንኳን አይናቸውን ሊገልጠው ያለመቻሉ መለስ እያንዳንዳቸውን ምን አብልቶ አደንዝዟቸው ምን አይነት መርፌ ወግቶ የህሊናቸውን የማስተዋያ ክፍል ቆልፎባቸው ቢሄድ ነው ሚያሰኝ ነው፡፡
ለነገሩ ማስተዋል የጠፋው በወያኔዎቹና አሽከሮቻቸው ሰፈር ብቻ አይደለም፡፡ ተቀዋሚ በሚለው የወል ስም የሚጠራውና ብትንትኑ የወጣው የተቀዋሚው ሰፈርም ቢሆን በሀገርና በወገን ላይ ወያኔ እያደረሰ ካለው ጥፋት አይደለም እያንዳንዱ በድርጅትም ይሁን በግል ከሚያደርሰውና ከሚደርስብትም የሚማር አልሆንም፡፡ ወያኔ አነእድ ነገር ሲያደርስ ወይንም የማስቀየሻ አጀንዳ ሲጥልልን ከየቤታችን ሆነን እንጮሀለን እንጠራራናም በየኤምባሲው ሄደን እናለቅሳለን፣ እስከመኖራቸው የማናውቃቸው ፓርቲዎችም ከየጓደቸው መግለጫ ያዥደጉዳሉ ከአንድ ሳምንት በኋላ ግን ሁሉም ይረሳና ጸጥ ረጭ፡፡ ለወያኔ ይበልጥ የልብ ልብ ይሰጠዋል፡፡ ፡ ወያኔዎች በተለይ አቶ መለስ ኢትዮጵያውያን አንድ መሆን እንኳን ባይችሉ በመካከላቸው ሰላም ፍቅር ካለ፤ መተባበር እንኳን ባይችሉ የሚከባበሩ ከሆነ፣ መግባባቱ ቢሳናቸው ላለመግባባት መግባባት የሚችሉ ከሆነ ለሥልጣናቸው አስጊ መሆኑ የተረዱት፣ ተረድተውም ተጨንቀው ተጠበው ዘዴ የዘየዱት ገና አዲስ አበባን ከመርገጣቸው በፊት ለመሆኑ ማስረጃ መዘርዘር የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም፡፡
ኢትዮጰያ የሚለውን ስም ተጸይፈው ኢትዮጵውያን ብሎ መጥራት በሊማሊሞ የማቆረጥ ያህል ሆኖባቸው ሀገራችን፣ የሀገራችን ህዝቦች ሲሉና ተከታያቸው ሁሉ ይህን ቃል እንዲጠቀም ሲያደርጉና ቀስ በቀስም ሲሆን በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ካልሆነም በወያኔ ተጠርንፎ በተያዘው መካከል መደበኛ ቃል እንዲሆን ለማድረግ ሲሰሩ ምን እየተሰራ አንደሆነ ወደየትስ ሊያመራ እንደሚችል ለማስተዋል የሞከረ ቢኖር ጥቂት ነው፡፡ በመከባበር ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እንገነባለን የሚል በመረዝ የተለወሰ መፈክር እያስተጋቡ ኢትዮጵያዊ ብሎኮአችሁን አውልቁና የጉሳ ነጠላችሁንና የመንደር አንገት ልብሳችሁን እየለበሳችሁ ተሰለፉ ሲባል አረ ይሄ ነገር ምንድን ነው፣ ምን ታስቦ ነው ብሎ ለአፍታ ከማሰብ ይልቅ በእድሜም በቀለም ትምህርቱም አንቱ የተባሉት ሳይቀሩ በየጎሳቸው ተደራጅተው እጅ ለመንሳት ቀናት አይደለም ሰአታት አልፈጀባቸውም፡፡ አይበጅም አደጋ አለው ያሉት ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ እናም የቦንቡ አዘጋጅ አቶ መለስ ቢሆንም ቀባሪና አቃባሪ በመሆን የተሰለፈው ግን ከሁሉም ሰፈር ብዙ እጅግ ብዙ ነው፡፡ በወያኔ በተለይም በአቶ መለስ ተዘጋጅቶ ግዜ እየጠበቀ አንዲፈነዳ በሁሉም የሀገረቱ አካባቢ የተቀበረው ቦንብ አገልግሉቱ የሥልጣን እድሜ ማረዘም ብቻ ሳይሆን በምንም ይሁን በምን ወያኔ ከምንይልክ ቤተ መንግሥት ከወጣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አንዳትቀጥል ማድረግ ለመሆኑ ያለምንም ሀፍረትና ፍርሀት በድፍረት ነግረውናል፡፡ ደግሞስ ማንን ሰው ብለው ያፍራሉ ይፈራሉ፡፡ የወያኔንና የቀኝ ገዢዎችን ቦንብ የሚያመሳስላቸውም ይሄ ነው፡፡
ምንም ወታደራዊ እውቀት ሳያስፈልግ ተቀባሪ ቦንብ በራሱ የማይፈነዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡እንዲፈነዳ የሚያደርጉት እንደ ቦንቡ አይነትና እንደ አጠማመዱ የሚለያዩ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ማንም ሰው ከፊልም አይቶ እንደሚገነዘበው በርቀት መቆጣጠሪያ፣ በሰአት፣ በመጫን፣ ክብደት በማላላት ወዘተ ተጠማጅ ቦንቦች ይፈነዳሉ፡፡ በሰአትና በርቀት መቆጣጠሪያ የሚፈነዱት በቀጥታ በአጥማጁ የሚፈጸሙ ሲሆን ቀሪዎቹ አደጋው አንዲደርስበት ታልሞ በተጠመደለት የሚፈነዱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹንም ቢሆን አጥማጁ ያሰበውን አደጋ ሳያደርሱ በባለሙያ ማምከን ይቻላል፡፡ እኛ ግን በተለይም ዘርፈ ብዙውና አይነተ ዝንጉርጉሩ ተቀዋሚ ተብየው ለማፈንዳት ነው እገዛ የምናደርገው፡፡ በእኛ ትብብርና እገዛ አንዳንዴም ቀጥተኛ ተዋናይነት የወያኔው ቦንቡ ፈንድቶ ጉዳት ሲያደርስ የአዞ አንባ ለማንባት ግን የሚቀድመን የለም፡፡

የወያኔን ንቀት የብዙዎቻችንን፣ አይረቤነት የሆድ አደሩም ብዛት ወዘተ የታየበት ሌላው ሰሞነኛ ድርጊት የጎንደሩ ህዝበ ውሳኔ ነው፡፡ ከአስር አመት በፊት በኦሮምያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ መፍትሄ ማስገኘቱ ቀርቶ ግዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ መሆኑ በተግባር በታየበት በዚህ ወቅት ሌላ ቦንብ ጎንደር ላይ ሲቀበር እያየንና እየሰማን ከለመድነውና አንዳችም ረብ ከሌለው ተራ ዋይታ መውጣት አልቻልንም፡፡ ለአንድ አላማ በአንድ የጋራ መርህ ስር መሰለፉ ቢቀር ሁሉም ሊላቀቀው የማይፈልገውንና ለመተባበር ዋና ችግር የሆነውን የድርጅት ሊቀመንበርነት እንደያዘ አንተም በመንገድህ እኔም በመንገዴ ተባብሉ አንዱ የሌላኛው እንቅፋት ከመሆን ታቅቦ የሁሉም ትኩረት ወያኔ ላይ እንዲሆን የሚያስገድዱ ብዙ ግዚያቶች በአንድ ሰሞን ዋይታና በጓዳ መግለጫ ታልፈው እንደ ዋዛ አምልጠዋል፡፡
ይህ ሰሞነኛ ድርጊትም በሀገራችን በየስፍራው የተጠመዱ ቦንቦችን አደገኛነት በግልጽ ያሳየ ተጨማሪ ማስረጃ ይመስለኛል፤ እኛ ከሌለን ትበታተናላችሁ የሚለው መፈክር ተራ ፉከራና ማስፈራሪያ ሳይሆን በደንብ የተሰራበትና ወያኔዎች የትም የትም ሆነው በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ገቢራዊ ሊያደርጉት የሚችሉት መሆኑን ያልተረዳ ኢትዮጵያዊ ይኖር ይሆን፡፡ ወያኔዎቹ ግን ዛሬም አላረፉም ተጨማሪ ቦንብ እያጠመዱልን ነው፡፡ እኛ አዲስ እንዳይጠመድ መከላከል የተጠመደውንም በመርገጥም ሆነ በማላላት እንዳይፈነዳ ማድረግ በርቀት መቆጣጠሪያም ሆነ በሰአት የሚፈነዳውንም ማምከን ሲቻለን ይባስ ብለን የሚፈነዳበትን ሁኔታ ነው የምናመቻቸው፡፡ ይህም ተቃውሞአችን የውሸት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚለው ዋይታችን የገንዘብ ማግኛ ብቻ መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ከሀገር ህልውና የሚቀድም፣ ከህዝብ እልቂት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ኖሮ ተቀዋሚዎች ዛሬም እንደትናንትናው በየጎጆአቸው ባልታዩ ነበር፡፡ ከነ ግል ፍላታቸውና ልዩነታቸው በሀገር ህልውና ላይ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ለመምከር የሚያስገድድ ከዚህ የባሰ ምን ግዜ ሊመጣ ነው? በቅርቡ እንኳን በጠመንጃ የተገታው የኦሮምያውና የአማራው የህዝብ እንቢተኝነት የእሬቻው ፍጅት የጋምቤላው ጭፍጨፋ አረ ስንቱ ይህ ሁሉ ፖለቲከኞቻችን የየግል ዘውዳቸውን አልጋቸው ስር አስቀምጠው ለጋራ ሀገር በጋራ እንዲመከሩ ሊያስገድዳቸው አልቻለም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ በህዝቡ ደም ሊነግዱ ሲዳዳቸው ነው ያስተዋልነው፡፡ ባላዋሉበት ሲፎክሩ በማያውቁት ነገር ሲደሰኩሩ የሰማናቸውም አሉ፡፡ፖለቲከኞቹ ዓላማ ብለው የያዙት የፖለቲካ ንግድ ወይንም ቁማር አለና ከያዙት መንገድ ሊወጡ እንደማይችሉ ተግባራቸው አሳይቶናል፡፡ የሚገርመው የጀሌው መብዛት ነው፡፡ ህሊና ያለው ሰው የሚያየውንና የሚሰማውን እራሱ መዝኖና አመዛዝኖ ማድረግ ያለበትን መወሰን ሲገባው የሌሎች ተከታይ ሲከፋም አምላኪ በመሆን ምንነቱን ባልተረዳው ጉዳይ የጥፋት ተባባሪ መሆኑ የችግራችን አንዱና አብዩ ችግር እንደሆነ አለ፡፡ ፖለቲከኞቹ ጀሌ ተከታይና አጨብጫቢ ደጋፊ ባይኖራቸው በፖለቲካው እየቆመሩ በጥፋት ተግባራቸው የወያኔን ያህል እድሜ ባላስቆጠሩ ነበር፡፡
ዛሬ እየሆነ ላለውም ሆነ በዚሁ ቀጥሎ ወደፊት ሊሆን ቢሚችለው ነገር ሁሉ ተጠያቂው ወያኔ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው መጠኑ ይበላለጥ ካልሆነ በስተቀር ድርሻ አለው፡፡ አጥፊው የመጀመሪያ ተጠያቂ ቢሆንም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በእምነትም ይሁን በጥቅም ተባባሪ የሆነ አንዲሁም ጥፋቱ እንዳይደርስ ማስቀረት፣ ያ ካልተቻለም ጥፋቱ የከፋ ጉዳት እንዳያከትል መከላከል እየቻለ ይህን ያልፈጸመ ሁሉ በየደረጃው ከተጠያቂነት ነጻ ሊሆን አለመቻሉ አነጋጋሪ አይመስለኝም፡፡
ድርድር እያሉ ለወያኔ የዴሞክራሲያዊነት ካባ የሚያላብሱት ስመ ተቀዋሚዎችም ከወያኔ ጋር በአንድ ጠረጴዛ መቀመጣቸው ፍጅትን ማስቀረት ካልቻለ በህዝብ ደም ላይ ቆመው ፖለቲካ እየቆመሩ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡አሁን በኦሮምያና በሶማሌ ክልሎች መካከል እየደረሰ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ከወያኔ እውቅና ውጪ የሚካሄድ ነው ብሎ በማስረጃ ሊከራከር የሚችል ሰው የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ይህ ነገር የተከሰተው የሶማሌው ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ከርመው ከተመለሱና የኦብነግን አንድ አመራር አሳልፈው ከሰጡ ለዚህ ምላሽም በወያኔ አጅ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶማሊ እስረኞች እንደሚፈቱ በተገለጸበት ወቅት መሆኑ በተጨማሪም ጥቃቱ ከደረሰበት አካባቢ ነዋሪዎች ሲናገር እንደተሰማው በሶማሌ ልዩ ፖለስ የተደበደቡትን ፌዴራል ፖሊስ መልሶ እነርሱን መብደቡ ብሎም ከሁለቱ ክልሎች ቃለ አቀባዮች የሚሰጡ መግለጫዎች ተደማምረው ሲመዘኑ ከበስተጀርባ የወያኔ እጅ መኖሩን በግልጽ ያያሉ፡፡ ዘለቅ ብለን እናስብ እንስታወስ ካልንም ወያኔ የሶማሊያን ወረራ ህጋዊ ብሎ ደግፎ ደርግን ያወግዝ እንደነበረ አንዝነጋውምና ይህም ማለት ታላቋ ሶማሊያን ይቀበላል ማለት ነውና በወረራ መያዝ ያልቻሉትን መሬት በእጅ አዙር ሊያስረክባቸው ቢሆንስ ብሎ መጠርጠር አይከፋም፡፡ ለዚህ ደግሞ ወያኔ ለፖለቲካ ፍላጎቱ ሲል መሬት አንደ ቅርጫ ሥጋ የሚሰጥ መሆኑን በሰሜን በኩል አይተናልና ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ መክረም ማግስት ከሶማሊያ ተነስቶ ድንበር ተሻግሮ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ጥቃት እያደረሰ ያለ ኃይል መኖሩ መስማቱ ለጥርጣሬው ተጨማሪ ግብአት ይሆናል፡፡ ስለሆነም ሶማሌና ኦሮሞን የሚመለከተው ተብሎ ቸል ሳይባል ከተለመደው ተራ ዋይታ፣ ተቃውሞ፣ ውገዘትና ፕሮፓጋንዳ ወጣ ብሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳዩን በስፋትና በጥልቀት ሊያየው ሊነጋገርበት ብሎም መላ ሊመታበት ይገባል፡፡ የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል የሚለው ብሂል እዚህ ጋር ይሰራ ይሆን!!

No comments:

Post a Comment