Monday, September 25, 2017

አቶ ለማ መገርሳ የኢሬቻ በዓል እንዳይከበር ማዘዛቸው ተሰማ


 


አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ
የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ የዘንድሮውን ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል እንዳይከበር ውሳኔ መስጠታቸው ታወቀ።
በትናትናው ዜና ዘገባችን የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር በመጪው ጥቅምት 1 ቀን 2017 በቢሾፍቱ ለሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ክልሉ ምንም አይነት መሳሪያ የታጠቀ ወታደርም ሆነ ፖሊስ ሃይል እንዳይኖር አዟል በሚል የዘገብን ሲሆን ዜናውን ከኢትዮጵያ የተከታተሉ ምንጮቻችን እውነተኛው ታሪክ በተዘገበው መልኩ አይደለም በማለት አዲስ መረጃ አቀብለውናል።
እንደምንጮቻችን አገላለጽ አቶ ለማ መገርሳ ባለፈው ነሀሴ ወር በቢሾፍቱ ከተማ የ2016ቱን ኢሬቻ ሰማእታት መታሰቢያ ሀውልት ከመረቁ በኋላ ከኦህዴድ ካድሬና ከኦሮሚያ ዞኖች ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ የዘንድሮውን [የጥቅምት 2017 ማለታቸው ነው] ኢሬቻ በዓል ሁላችንም በየቤታችን በራችንን ዘግተን ባለፈው ዓመት ያለቁብንን ወገኖች በማሰብ የምናከብረው ይሆናል የሚል ውሳኔ እንደወሰኑ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በውሳኔውም ማግስት አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር የ2017ቱን ዓመታዊ ኢሬቻ በዓል ሁሉም የኦሮሞ ተወላጅ እቤቱ ሆኖ ባለፈው ዓመት የሞቱትን ወገኖቹን በመዘከር ለማክበር ስለወሰነ በቢሾፍቱ የሚካሄድ ዝግጅት የለም የሚል ደብዳቤ ለሶስት የፌዴራሉ ጽ/ቤቶች ማስገባቱን በወቅቱ በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የሆኑት ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የአቶ ለማ መገርሳ ደብዳቤ እና ውሳኔ እንዲደርሳቸው የተደረጉት የጠ/ሚ/ር ጽ/ቤት፣ የባህልና ቱሪዝም ም/ር ጽ/ቤት እና የደህንነት ክፍሉ ሲሆኑ ውሳኔውን ቀልባሽ ሌላ ውሳኔ የተሰጠው ከደህንነቱን ጽ/ቤት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአቶ ለማ መገርሳ ሀሳብ አፍላቂነት የኦሮሚያ መስተዳድር የ2017 ኢሬቻ በዓልን በቤት ዘግቶ ለማክበር የተወሰነበት ምክንያት የደህንነትና የጸጥታ ስጋትን መሰረት በማድረግ ሲሆን በሁለተኛነት ደረጃ ደግሞ በ2016ቱ እልቂት አጠቃላይ የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ቢሾፍቱ ላይመጣ ይችላል የሚል መረጃ ስላለ ነው በሚል ለጠ/ሚ/ሩ ቢሮና ለደህንነቱ ጽ/ቤት ማብራሪያ እንደሰጡ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ሆኖም በኦሮሚያ መስተዳድር በኩል የተወሰደው የመፍትሄ ውሳኔ ተቀባይነት ባለመግኘት በአንጻሩም ጠቃሚ ነው ተብሎ የታመነበትን ተግባራትን ያካተተ ውሳኔን ከደህንነት ቢሮ በመሰጠቱ የአቶ ለማ መገርሳ መስታዳድር ውሳኔውን ቀልብሶ የተሰጠውን ትእዛዝ እሱ ከሚመራው መስተዳድር የተሰጠ በማስመሰል እየተገበረ ነው ያለው በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።
በአቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት ጽ/ቤት ከኦሮሚያ መስተዳድር በኩል የቀረበለትን ውሳኔና ምክንያት መሰረት በማድረግ ባወጣው ትእዛዝ ከእያንዳንዱ ኦሮሚያ ዞን በመንግስት [በኦህዴድ ማለት ነው] እየተመለመሉ እንዲመጡ ለዚህም ተግባር የኦሮሚያና የፌዴራል መንግስት በቂ ትራንስፖርት እንዲያዘጋጁ-ከ900 እስከ 1,500 ሲቪል የለበሱ ወታደሮች እንዲሰማሩና የእለቱን ሀይማኖታዊ ፕሮግራም በኦህዴድ አባልነቱና ታማኝነቱ የታወቀን ካድሬ/አባ ገዳ ወይም የሀገር ሽማግሌ ብቻ እንዲመራው ማድረግና መድረኩን በአጠቃላይ ሲቪል በለበሱ ወታደሮች ማስጠበቅ በሚል ትእዛዝ መሰረት ነው ዛሬ የአቶ ለማ መገርሳ ጽ/ቤት የኢሬቻን በዓል በተመለከተ ማንኛውንም መግለጫም ሆነ አዘገጃጀት እያደረገ ያለው ሲሉ አስረድተዋል።
የኢሬቻን በዓል ካለማክበር ይልቅ በእኛ ቁጥጥር ስር አድርገን ማክበሩ ታላቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ አለው የሚል እድምታ ከደህንነትና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንደተያዘ ለማወቅ ተችላል።
በ2016ቱ ዓመታዊ የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ለመሳታፍ በተገኘው ከ3-4 ሚሊዮን ህዝብ ላይ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎችና ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ ቁጥሩ ከ700 በላይ ህዝብ እንዳለቀ የተገለጸ ሲሆን በመንግስት በኩል ዛሬ ድረስ የማቾቹን ቁጥር በ55 ላይ ገድቦ መግለጹ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment