Sunday, September 17, 2017

በምስራቅ ኦሮሚያ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ55ሺህ በላይ ደርሳል-አመራሮቹ የለንበትም አሉ –




By ሳተናውSeptember 17, 2017 17:56






በምስራቃዊው የኢትዮጵያ ክፍል በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይልና በኦሮሞ አርብቶ አደር መካከል በተነሳ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከጂጂጋና አንዳንድ የሶማሌ ከተሞች ተገደው የተፈናቀሉ ኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር ከ55ሺህ በላይ መድረሱን አቶ አዲሱ አረጋ ዛሬ የገለጹ ሲሆን የተገደሉትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር እስከዛሬ ማወቅ እንዳልተቻለም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዜናም በሁለቱ ተጎራባች ህዝብ መካከል ለብዙዎች ህይወት መጥፋትና ለአስር ሺዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ጦርነት ከተነሳ ግዜ ጀምሮ የሁለቱ ክልል ፕሬዚዳንቶች አቶ ለማ መገርሳና አቶ አብዲ ኢሌ ዛሬ ለመጀመሪያ ግዜ በአዲስ አበባ የተገናኙ ሲሆን በጋራ በሰጡት መግለጫም የሁሉትም ክልል ከፍተኛ አመራሮች በግጭቱ ውስጥ እጃቸው የለበትም የሚል እራስህን አድን መግለጫ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችላል።
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ድንበር አከባቢ ከሞያሌ እስከ ባቢሌ ባሉ በርካታ መንደሮች ላይ በሶማሌ ልዩ ፖሊስ ሃይል በተከፈተ ጦርነትና በኦሮሞ አርብቶ አደሮችም በኩል በተወሰደ እራስን የመከላከል አጻፋ እርምጃ ከመቶ በላይ ሰዎች የተገደሉና ከ55ሺህ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች በሚኖሩበት ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ሲሆን በሐረር፣ጭናክሰን፣ ሚኤሶ እና ባቢሌ ከተሞች በድንኳን ተጠልለው እንደሚገኙ አቶ አዲሱ ገልጸው የእርዳታ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሰብዓዊ መብት ተማጋቾችና ምእራባዊያን ዲፕሎማት የኢትዮጵያ መንግስት በምስራቁ እና በሰሜን ምእራብ የሀገሪቱ ክፍል የተነሳውን ጎሳተኮር የድንበር ግጭት መቆጣጠርና መፍትሄ መስጠት አልቻለም በማለት የሚከሱና የሚተቹ ሲሆን ብዙዎችም ከእርሰ በርሱ እሊቂት ጀርባ የራሱ የገዢው ፓርቲ እጅ አለበት ሲሉ በአጽንኦት ይናገራሉ።
የኦሮሚያና ሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር መሪዎች ከዚህ በፊትም በነሃሴ 19ቀን ተገናኝተው ችግራቸውን በሰላም ለመፍታት መፈራረማቸውን የገለጹ ቢሆንም ብዙም ሳይቆዩ ወደ ጦርነት የገቡ ሲሆን በአጠቃላይም ከመጋቢት 2017 ጀምሮ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውና ከ400ሺህ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ከአቶ አዲሱ አረጋ መግለጫ መረዳት ተችላል።

No comments:

Post a Comment