Thursday, September 28, 2017

የአለም ባንክ እውነትና ኩሸት – ኤርሚያስ ለገሰ



  
By ሳተናውSeptember 27, 2017 23:53


ኤርሚያስ ለገሰ
ኤርሚያስ ለገሰ
ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የአለም ባንክ ሪፓርት ብዙ የሚነግረን ቁምነገሮች አሉ። በአንድ በኩል የሕውሐት አገዛዝ የገባበትን ማጥ ያሳየናል ። ይህም አገዛዙ ጊዜውን ጠብቆ ተፈጥሮአዊ ሞቱን ሊሞት መቃረቡን ሐገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚያሳዩበት ነው። በሌላ በኩል አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ምእራባውያን በሚያካሂዱት ስውር ደባ ስርአቱን ለማስቀጠል የሚያደርጉትን አገም ጠቀም እንመለከታለን ። እነዚህ የውጭ ሐይሎች እውነትና ውሸት እየመጋገቡ የሚያቀርቡት በዚህ ምክንያት ነው። የሰሞኑ የአለም ባንክ ሪፖርት ለዚህ አባባል ጥሩ ምሳሌ አድርጌ ወስጀዋለሁ። ለዚህ ብዙ ማስረጃዎች ከሪፖርቱ ውስጥ መጥቀስ ይቻላል። ለዛሬው አንድ ኩሸት እና እውነት እንውሰድ።
ኩሸት አንድ: ” ዳታ ማጣጣም!”
በሕውኃት/ ኢሕአዴግ ውስጥ ” ዳታ ማጣጣም” ልምድ የተወሰደው ከአለም ባንክ ነው። የአለም ባንክ እስከ ጐጥ የዘለቀ መዋቅር ስለሌለው የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያቀርብለትን የእድገት አሃዝ መቀበል ይጀምራል። ይሄ ባለሁለት አሃዝ ( በአብዛኛው 11%) የተጋነነ መሆን እና እዛው ቁጥር ላይ ሙጭጭ ማለት እንዲሁም በኢትዮጵያ መሬት ላይ የተነጠፈው እውነት መረጃው ውሸት መሆኑን ይገነዘባል። በዚህ ምክንያት አለም ባንክ እስከ አስር የሚጠጉ ሠራተኞቹን ወደ መዲናችን አዲስአባ በመላክ በቁጥሮቹ ላይ ይደራደራል። አብዛኛውን ጊዜ አለም ባንክ ከ5 እስከ 8 % እድገት ይገልጣል። በነገራችን ላይ የአለም ባንክ ሰዎች ተጨማሪ ፈንድ ለማግኘትና ለግላቸው ጥቅም ሲሉ እድገት መጥቷል ማለታቸው የሚጠበቅ ነው። ህውሓት በበኩሉ የ11% እድገት ይዞ ይቀርባል። በድርድር የፀደቁት( በአብዛኛው አማካይ) ቁጥሮች የአለም ባንክ ዳታ ሆነው ይቀርባሉ። በዚህ አሃዝ አለም ባንክም ፈንዱን ያገኛል፣ ህውሓትም የፕሮፐጋንዳ ማድመቂያውን ያገኛል። አቶ በረከት “አለም የሰጠነውን ስለሚቀበል ጨማምራችሁ ከመስጠት አትቆጠቡ!” የሚለው ይሄንን ስለሚያውቅ ነው።
የአለም ባንክን ዳታ ማጣጣም ውሸት በአንድ ምሳሌ አስደግፈን እንመልከተው ። ሪፖርቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሶስተኛው (33 ሚሊዬን) የሚጠጋው ከፍፅም ድህነት ወለል በታች በቀን ከ1•9 ዶላር በታች ገቢ ያገኛሉ ይላል። ከሁለት ዶላር በታች የሚለውን ስሌት ከሄድን “የጠቅላይ ሚኒስትሩን” (HD) ቤተሰብ ጀምሮ በድህነት ወለል ውስጥ እንከታቸዋል። ነብስ ይማርና “ከድርጅት ተቆራርጦ የሚቀረን አራት ሺህ ብር ነው!” የተባለላቸው የአቶ መለስ ቤተሰቦች ደግሞ በፍፅም ድህነት ውስጥ ኖረው የሞቱ ይሆናሉ። እንደውም ከዛሬ ጀምሮ ” ምጡቁ”፣ ” ዘመን ተሻጋሪ!”፣ ” የክፍለ ዘመን ክስተት!” እየተባለ መንፈሳቸው ከሚጨነቅ ” የደሃ ደሃ” ብንላቸው እረፍት የሚያገኙ ይመስለኛል። ሴትየዋ ጉልት ለመነገድ ያቀረበችው ሓሳብ በሕወሓት ደጃፍ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል ። ጉልት ሸጦ የማክበር ሓሳብ! እስቲ እንሞክረው!
እስቲ ደግሞ አንድ መሬት የወረደ ተጨባጭ ምሳሌ እናንሳ። ሁለት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህራን የሆኑ ባልና ሚስት አሉ እንበል። እነዚህ ባለትዳሮች አራት ተማሪ የሆኑ ልጆች አሏቸው እንበል። እነዚህ ጥንዶች የወር ደሞዛቸው በድምሩ 10ሺህ ብር ይሁን። እንግዲህ በአለም ባንክና አለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ይሄ ቤተሰብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው። እስቲ እግዜር ይታያችሁ እነዚህ የዪንቨርስቲ መምህራን ቤተሰቦች ከድህነት ጠለል በታች የሚኖሩ ከሆነ እንዴት 33 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ በፍጹም ድህነት ይኖራል? ፈፅሞ ውሸት ነው!!
በነገራችን ላይ ይሄ አለም ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው ” ዳታ የማጣጣም ” ተሞክሮ ዛሬ በቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል ፣ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ማእከላዊ ስታስቲክስ ባለሥልጣን መደበኛ አሰራር ሆኗል። ቶጐ ጫሌ የሚገኘው የቀበሌ ሊቀመንበር እና አብርሃ አጽብሃ የሚገኘው የሕውሓት ካድሬዎች የሚያቀርቡት የኢኮኖሚ እድገት ቁጥር አንድ አይነት ነው። አንድ አይነት። 11 በመቶ። በጣም ያሳዝናል።
እውነት አንድ :- ” እኩል ተጠቃሚነት የለም!”
ሪፖርቱ “የኢኮኖሚ እድገቱ በክልሎች እና በሕዝቦች መካከል እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አላረጋገጠም” ይላል። እኛስ ከዚህ ውጭ ምን አልን? ምን ወጣን? የሕውኃት አገዛዝ በዘር ላይ የተሞረከዘ በመሆኑ መቼም ቢሆን በእኩልነት ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል እድል መፍጠር እንደማይችል በተደጋጋሚ ገልጸናል ።
እርግጥም በማበላለጥ ፣ በጥላቻና በጠላትነት የተመሰረተው የአገዛዝ ስርአት ውጤቱ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም ። ጎጠኝነትና ጠባብነት የተከለው የመርዝ ዛፍ ፍሬውም መርዛም መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ አንዱን ክልል ከሌሎች ለይቶ የማበልፀግና ሌላውን የማቆርቆዝ አድሎአዊ አሰራር በትውልዶች መካከል ከቶውንም ሊረሳ የማይችል የቂም በቀል ቋጠሮ የሚያኖር ነው። አንዱ አካባቢ እንደ የቁማሯ ከተማ ላስቬጋስ በምሽት ፀሐይ ተንቆጥቁጦ ሌላው በድቅድቅ ጨለማ ሲዋጥ የሚያመላክተን ነገር የአገዛዙን አድሎአዊነት እና ሸውራራ አመለካከት ነው። የዘረኝነት ፓሊሲ የወለደው ጐሰኝነት ነው።
አንዳንዶች ጐሰኝነትን ቀባብተው ብሔርተኝነት ቢሉትም በየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ ለፓለቲካ መሳሪያ እስከተጠቀምንበት ድረስ ሁለቱም የዘረኝነት ፓሊሲ ነው። ለራስ ብሔረሰብ ሰው ድጋፍና ጥቅም የመስጠት አድሎአዊ አካሄድ ነው ። ለአጠቃላይ የአገር እድገት ሳይሆን በራስ ክልል ለሚካሄድ ልማት ቅድሚያ መስጠት ነው። አለም ባንክ አፋን ሞልቶ የአድሎው ምንጭ ጐሠኝነት የወለደው አትበል እንጂ መብራቱና መንገዱ በልዩ ትኩረት የት እየተሰራ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ አመላክቷል። የባንኩ ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ማይክል ጊገር የአገሪቱ እድገት ሁሉም አካባቢዎችና ዜጎች ማካተት እንደሚገባው፣ የኢኮኖሚ ርቀቱ መጥበብ እንዳለበትና መሠረተ ልማቶች ያለ አድሎ መስፋፋት እንደሚገባው በትኩረት ተናግረዋል ። የፈረንጁ ምክር ” የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትንገር” ቢሆንም ከምክሩ ባሻገር ያለውን እዉነታ አሻግሮ ማየት የሚቻል ይመስለኛል። ማየታችንን ካልከለከሉን በስተቀር!!

No comments:

Post a Comment