Friday, September 15, 2017

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ድሬዳዋ ገቡ


Filed under: News Feature,የዕለቱ ዜናዎች |


 


በሰሞነኛው ግጭት የተነሳ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ድሬዳዋ መግባታቸው ታወቀ፡፡ ዛሬ ተጓጉዘው ወደ ድሬዳዋ የገቡት የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በእርግጠኝነት ባይታወቅም፣ በርከት ያሉ እንደሆኑ ግን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከስፍራው የተገኙ መረጃዎች እንደጠቆሙት፣ በዛሬው እለት በአስር የጭነት መኪኖች ተፈናቃዮቹን ወደ ድሬዳዋ ማስገባት ተችሏል፡፡ በድሬዳዋም ህብረተሰቡ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገላቸው እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ውጥረት አሁንም አለመብረዱ እየተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ በድንበር አዋሳኝ በሆኑ ቦታዎች ላይ ያለው ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግጭት በተከሰተባቸው አካባበዎች ሰፍረዋል ቢባልም፣ ሁኔታው ግን አሁንም መረጋጋት እየታየበት እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስከ ዛሬ ምሽት ድረስም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ መጠነኛ ግጭት እንደነበር ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ግጭቱን ሆን ብለው የሚፈጥሩትም የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊሶች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩል፤ ሰሞነኛውን ግጭት ተከትሎ የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ባለስልጣናት እየወነጃጀሉ ይገኛሉ፡፡ ግጭቱን ተከትሎ ከሁለቱም ወገን የሰዎች ህይወት የተቀጠፈ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል አወዳይ ከተማ የሞቱ የሶማሌ ክልል ተወላጆች አስከሬን ለሶማሌ ክልል ተላልፎ መሰጠቱን የገለጸው የኦሮሚያ ክልል፣ ሆኖም በሶማሌ ክልል የሞቱ ተወላጆቹ አስከሬን ግን እስካሁን ድረስ ለኦሮሚያ ተላልፎ አለመሰጠቱን ገልጿል፡፡ በዚህም የተነሳ የኦሮሚያ ክልል የሶማሌ ክልልን እየወነጀለ ሲሆን፣ የኦሮሞ ተወላጆች አስከሬንም በአስቸኳይ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

 

No comments:

Post a Comment