—
[ የምንከተለው የተለያየ ሐይማኖት፣ የምንናገረው የተለያየ ቋንቋ እንዲሁም የምንኖርበት በዓል፤ የእኛነታችን ጌጥ ሆኖ በአደባባይ የምንሞሸርበት እንጂ! ኢትዮጵያዊነታችንን ነጥቆ ሊከፋፍለን አይገባም!! ]
—ለረዥም አመት ታስቦበት የተቀበረው የህወሃት/ኢህአዴግ አደገኛ “የብሔር/የጎሳ”ፖለቲካ ፈንጂ እዚህም እዚያ እየፈነዳ ነው። አሁን ላይ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በባሰ እጅግ በጣም አሳዛኝ እና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየገባች ነው። ለዚህም የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የወያኔ አገዛዝ ሥርዓት መሆኑ ለወዳጅ እንዲሁም ለጠላት
ፍንትው ብሎ የሚታይ ሃቅ መሆኑን ለማንም ግልጽ ነው።ሆኖም ግን ሌሎች ግለሰቦች እና ስብስቦች ወይም ድርጅቶች በማወቅ ይሁን ባለማወቅ ለሃገር እና ለወገን የማይበጀውን የጎሳ ፖለቲካ በማራመድ ከዚያም ከፍ ብሎ አንዱን “ብሔር” ከሌላው” ብሔር” በመለየት እራስን በማተለቅ ሌላውን በማንኮሰስ ፣ “የእኔ ይበልጣል” አይነት አፍራሽ ወይም ገንቢ ያልሆነ “የብሔር” ፖለቲካ ፍላጎታቸውን እንዴት አድርገው ያቀነቅኑ እንደነበረ የትላንት ብቻ ሣይሆን ዛሬም የምናየው ተግባር ጭምር ነው ።ይህ ማለት ግን ዐማራ በዐማራነቱ ፣ ኦሮሞ በኦሮሞነቱ፣ ጉራጌ በጉራጌነቱ፣ ሶማሌው በሶማሌነቱ … ሌላውም እንደዛው፤ ማንነቱን መሰረተ ያደረገ ጥቃትን አጥብቄ እንደምቃወም ሁሉ ፣ማንነት መነሻ በማድረግ የሚደርስ የትኛውንም አይነት ጥቃት መከላከል እደግፋለው ማለት እንደሆነ ጭምር ታሳቢ ይደረግልኝ።
—
ከዚህ ቀደም የጎሳ ፖለቲካ አይበጀንም ፣ ሃገርን የሚበታትን ለዜጎች የማይጠቅም አደገኛ ነገር ነው ። ከዚህ ይልቅ በአንድነት ቆመን የሚከፋፍለንን ሥርዓት በማስወገድ ፤ “ኢትዮጵያ ለሁሉም ፣ሁሉም ለኢትዮጵያ “ዘብ በመቆም እኛ ኢትዮጵያውያን የምንከተለው የተለያየ ሐይማኖት፣የምንናገረው የተለያየ ቋንቋ እንዲሁም የምንኖርበት በዓል፤ የእኛነታችን ጌጥ ሆኖ በአደባባይ የምንሞሸርበት እንጂ ! ኢትዮጵያዊነታችንን ነጥቆ ሊከፋፍለን አይገባም!! በማለት ቀን ከለሊት ልመና ቀረሽ ጉትጎታ ሲካሄድ ይስጥ የነበረዉ ምላሽ ምን እንደነበር የሚታወስ ነው። አሁን ላይ በአንድ ሃገር ውስጥ ስለ ሦስት ሃገር በሚመስል ደረጃ የምናወራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል “ሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ኢትዮጵያ !”ነገ ደግሞ ስንት ሃገር እንሆን ይሆን ?! ለእንዲህ አይነቱ ጥያቄ የሌላውን ባላውቅም ለእኔ ግን ፤የኔታ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም “ያስፈራል ግን ኢትዮጵያ አትፈርስም” በማለት ከዚህ ቀደም የፃፉት ጽሁፍ መጽናኛ ብቻ ሣይሆን ብርታትም ጭምር ይሆነኛል።
—
አሁን ግን በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክፍለ ሃገር የሚሰማው እና የሚታየው ነገር እጅግ በጣም አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል!! በሶማሌ ክፍለ ሃገር በመንግሥት ባለሥልጣናት “የኦሮሞ ተወላጆች” በመታወቂያ እየተለዩ ለእንግልት እና ለእስር ከዚያም ከፍ ሲል ለሞት የሚዳረግበት አስከፊ ደረጃ ተደርሷል ። ምን ይሄ ብቻ የኦሮሞ ተወላጆች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጭምር እየተደረጉ እንደሆን በሰፊው እየተነገር ነው። ከምንም በላይ ደግሞ “የሶማሌ ፖሊሲ ልዩ ሃይሎች” የወሰን ቦታዎች አልፈው በጦር መሣርያ ጥቃት ማድረሳቸው ሌላው አሳሳቢ ችግር ነው። በተመሳሳይ መንገድ የሶማሌ ተወላጆች ላይ በአወዳይ ከተማ በንጹሀን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ የደረሰው አስከፊ ጉዳት እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው። እንዲህ ያለው ነገር ከአካባቢው አልፎ በአገር ደረጃ የሚያደርሰው ቀውስ ቀላል የሚባል አይደለም ።እርግጥ ነው በሥልጣን ላይ ያለው የአገዛዝ ሥርዓት የዘራውን የጎሳ ፖለቲ የሚያጭድበት ወርቃማ ጊዜ እንደሆነለት እሁን ቢሆንም፤ ለሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እጅግ በጣም የሚያስቆጣ አደገኛ ተግባር ነው።
—
ከሁለት ቀን በፊት የኦሮሚያ “ክልል” ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እና አቶ እድሪስ ኢስማኤል የሶማሌ “ክልል” ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ እንደ-ባላሥልጣናቱ አነጋገር እና እየወሰዱት እንዳለው እርምጃ በአግባቡ በማጤን፤ ከግጭቱ ጀርባ ያለው አደገኛ ሴራ መገንዘብ ያስፈልጋል። ቪኦኤ ካነጋገራቸው የሁለቱ “ክልል” አፈ ቀላጤዎች በተጨማሪ የኦነግ ከፍተኛ አመራር በተጨማሪ አቶ ጀዋር መሀመድ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ታሳቢ በማድረግ ፤በሁለቱ ክፍለ ሃገሮች የተከሰተው ችግር እንዲሁ በቀላሉ የማይታይ ከመሆኑ ባሻገር፣ አንዱን ትክክል ሌላውን የተሳሳተ በማድረግ፤ በአንድ ሃገር ግዛት ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮያዊያን መካከል የተለየ ግዛት በመፍጠር ሶማሊያ እና ኦሮሚያ በማለት እንዲሁ በቀላሉ ዘው ብለው የጥፋት ወጥመድ ውስጥ መግባት ቀጥሎ ይዞ የሚመጣው ነገር እጅግ አደገኛ እንደሆነ ለመገመት ብዙም የማያስቸግር ነው።ነገር ግን በመረጃ እና በማስረጃ በተደገፈ ጉዳዩን በአግባቡ በመመርመር ትክክል የሥራውን ማበረታታት ፣ ያጠፋውን መውቀስ እና ከስህተት እንዲመለስ ማድረግ ተገቢነቱ አሻሚ አይደለም ።
—
ህወሃት እንደሚፈልገው አበጅቶ የሰራቸው “የሁለቱም ክልል” ባለስልጣናት በአካባቢው የተከሰተውን ችግር አስመልክተው የሚሰጡት ማብራሪያ እና እየወሰዱት ያለው በወታደር የተደገፈ እርምጃ፤ በአግባቡ የተመረመረ እንደሆነ ከጀርባው ከባድ ነገር አለ።ከዚህም በተጨማሪ የሁለቱ “ክልሎች” ባለስልጣናት አንዱ ሌላውን ሲከስ እና ለቀረበበት ክስ ምላሽ ሲሰጡ በአንድ ሃገር ግዛት ውስጥ ፈጽሞ ያሉ አይመስልም ፤ የፌደራል መንግሥት ነኝ የሚለው’ም አካል በበላይነት በሚያስተዳድረው ግዛት ውስጥ የተፈጠረ ችግር እንዳለ ሣይሆን፤ በሁለት ሃገሮች መካከል ሦስተኛ ጣልቃ ገብ ሃገር ሆኖ ነው ምላሽ እየሰጠ ያለ ነው የሚመስለው ። እነዚህን እና መሰል ነገሮችን በአግባቡ በመረዳት በሁለቱ ክፍለ ሃገሮች መካከል የተፈጠረው ችግር በአግባቡ የሚፈታበት ፣በዜጎች መካከል እልቂት እንዳይከሰት እንዲሁም የሃገር አንድነት እንዳይናጋ ፤ ከአደራ ጭምር ጉዳዮን በአግባቡ በመያዝ ሁላችንም የዜግነት ግዴታችንን በተገቢው መንገድ ልንወጣ ይገባል ብዬ በጽኑ አምናለሁ ።በዚህ ግጭት ህይወታቸውን ላጡ በሙሉ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ይስጥልን ። ለዚህ ሁሉ የዳረገን የአገዛዝ ሥርዓት በመለወጥ ፤ ከህዝብ ለህዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖረን በምናደርገው ጥረት ፈጣሪ ይርዳን፤አሜን!!!
—
(ይድነቃቸው ከበደ)
—
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
No comments:
Post a Comment