Thursday, September 14, 2017

በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሊ ክልል መውጣታቸውን እንደቀጠሉ ነው

ዜና 1
(ኢሳት ዜና መስከረም 04/2010 ዓም) በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሊ ክልል መውጣታቸውን እንደቀጠሉ ነው
በሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ትዕዛዝ የታፈሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሶማሊ ክልል የተለያዩ ከተሞች እየተፈናቀሉ ሃረር ከተማ የገቡ ሲሆን፣ ብዙዎች በልዩ ሃይል አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ካለፉት 3 ቀናት ጀምሮ መታወቂያቸው እየታዬ የታፈሱት የኦሮሞ ተወላጆች፣ ብዙዎቹ ሃረር ከተማ ከገቡ በሁዋላ ወደ ዘመዶቻቸው እንዲሄዱ የኦህዴድ ባለስልጣናት ሲያግባቡ ውለዋል።
በእየለቱ ወደ ሃረር የሚገቡ የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ የአጋዚ ወታደሮች ጥይት በመተኮስ ሰልፈኛውን በትነዋል። እስካሁን ባለው መረጃ አንድ ሰው በወታደሮች ተገድሏል። የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ጸጥ ረጭ ብላ ውላለች።
በሁለቱም ወገን የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉ ታውቋል።
በጅጅጋ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ በክልሉ የሚፈጸመው ነገር እንዳስፈራቸው ይናገራሉ። አሁን የተጀመረው ጥቃት በሁሉም ብሄሮች ላይ ይፈጸማል በሚል የከተማዋ ነዋሪዎች ፍርሃታቸውን ይገልጻሉ። ( )
በአጠቃላይ እስከ 12 ሺ የሚደረሱ የኦሮሞ ተወላጆች ይፈናቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ የኦህዴድ ባለስልጣን ለክልሉ ዘጋቢያችን ገልጸዋል። የተፈናቀሉና የሚፈናቀሉ ዜጎችን መኖሪያ ቤቶች መዘረፋቸውንም ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ( )
ከጅጅጋ ውጭ ባሉ የጠረፍ ከተሞች የልዩ ሃይል አባላት ዜጎችን እየገደሉ መሆኑም ታውቋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግድያውንና መፈናቀሉን ለማስቆም ምንም የሚወስዱት እርምጃ እንደሌለ የአይን እማኞች ይናገራሉ። በአወዳይ ዛሬ ሌሊት ወታደሮች የከተማዋን ወጣቶች ለመያዝ በተንቀሳቀሱበት ወቀት ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል የምስራቅ እዝ የመከላከያ አባላት በምስራቅ ሃረርጌ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆችን እየሰበሰቡ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ያስገቡ ሲሆን፣ ዛሬ በእዙ ዋና መምሪያ አዳራሽ ሲያነጋግሩዋቸው ውለዋል።
ወደ አዲስ አበባ ፣ ጅጅጋና ሌሎችም ቦታዎች የሚደረገው የትራንስፖር አገልግሎት ከተቋረጠ 3ኛ ቀኑን ይዟል።
በሌላ በኩል በሶማሊ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮና በኦሮምያ ኮሚኒኬሽን መካከል የተጀመረው የቃላት ጦርነት ቀጥሎአል።
የሶማሊ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በአወዳይ ከተማ ከ50 በላይ የሆኑ የሶማሊ ተወላጆች እስከዛሬ ድረስ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ ፣ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ መገደላቸውን ገልጿል። ከ300 በላይ የሚሆኑ ደግሞ በመከላከያ ሰራዊት ሀይል ህይወታቸውን በማትረፍ ወደ ሀረር እንዲገቡ መደረጉን እስከ ትናንት ድረስ 30 የሚሆኑ የዜጎች የተቆራረጠና የተቃጠለ ሬሳ የመጣ ሲሆን በዛሬው እለት በክብር ግብአተ ግብራቸው እንደሚፈጸም የሶማሊ ክልል መግለጫ ያትታል።
የሶማሊ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ “ የኦሮምያ ክልል መንግስትና የአሸባሪው ኦነግ አንድ አቋም በመይዝ በግልጽ ጆሀር መሀመድና እና የኦሮሞ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አዲሱ አረጋ ተመሳሳይ አቋም ያሳዩበትና ፣አዲሱ አረጋም በግልጽ የኦነግ አባልነቱን ያረጋገጠ ሆኖ ተግኝቷል:፡” በማለት ለግጭቱ እነዚህን አካላት በተጠያቂነት ካቀረበ በሁዋላ፣ ይህ መንገድ አልሳካ ብሎ ሲቀር ፊቱን በክልሉ ነዋሪ በሆኑ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የዘረኝነት ጭፍጨፋውን ጀምሯል በማለት የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት በዘር ጨፍጨፋ ወንጀል ከሷል።
“የኦሮሞ መንግስትና የጸጥታ ሀይሉ በኦሮሞ ክልል ላይ ከ20 አመት በላይ የኖሩ ከክልሉ ማህበረሰብ ጋር በደም የተዛመዱ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የወሰደው እርምጃ የክልሉን ህዝብና መንግስት በእጅጉ ያስቆጣና ይህንንም በሀገራችን ህግና ደንብ መሰረት ጉዳት አድራሾቹ ለህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ የክልሉ መንግስት አጥብቆ ይሰራል” የሚለው መግለጫው ፣ የክልሉ መንግስት የተቆጣውን የክልሉ ህዝብ በማረጋጋት በክልሉ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆችን በማሰባሰብ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከለላ በመስጠት ምግብና መኝታን በመስጠት ህዝባዊነቱን፣ ሰላም ወዳድነቱንና ወገን አክባሪነቱን አሳይቷል ሲል ደምድሟል።
የኦሮምያ ክልል ኮምኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የክልል መንግስታቸውን ምላሽ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን፣ የሶማሊ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃገርን ከሚያስተዳድር መንግስት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ይሰጣል ተብሎ የማይጠበቅ አሳፋሪ መግለጫ አውጥቷል ሲሉ ገልጸዋል።
“ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተጣለበትን ህዝባዊ እና መንግስታዊ ሃላፊነት ከመሸከም አንጻር ያለበትን ደካማ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ፡፡” የሚለው የኦሮምያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ፣ የሶማሊ ክልል መንግስት ልዩ ሃይል አደራጅቶ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን፣ በኦሮሞነታቸው ብቻ ቀያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ማድረጉን ገልጿል።
የሶማሊ ክልል የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናትን በኦነግነትና በአሸባሪነት መክሰሱም ትክክል አይደለም የሚለው፣ የኦሮምያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ መግለጫ፣ “የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አመራሮች በኢትዮጵያ አንድነት እና በህዝቦች ወንድማማችነት ላይ የማያወላዉል ጽኑ አቋም እንዳለን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክራችን ነዉ፡፡ ኦሮሚያ እና የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ አንድነት ምሶሶዎች ናቸዉ፡፡ የክልሉ አመራሮችም ለፌዴራላዊ ስርዓታችን ማበብና መጎልበት የህዝቦች ወንድማማችነት እና እኩል ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ እየታገሉ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ዉድ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች እንጂ በአሸባሪነት እና በኦነግነት የሚፈረጁ አይደሉም፡፡ ከዚህ ባለፈ የኦሮሞ ተወላጆችን እና የክልሉን አመራሮች በኦነግነት ሌብል ማድረግ ለማሸማቀቅ መሞከር ከበርካታ አመታት በፊት ሲደረግ የነበረ አሁን ጊዜዉ ያለፈበት ተራ ሌብሊንግ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡” ሲል ተከራክሯል።
የሶማሊ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ያወጣው መግለጫ ግጭትን የሚያባብሱ አደገኛ ቃላት እና በተጋነኑ ዉሸቶች የተሞላ ነው ሲል የሚኮንነው የኦሮምያ ክልል መግለጫ፣ ሰሞኑን በተፈጠረው ግጭት ስለደረሰው ጉዳት በክልሉ መንግስት በኩል ያለውን መረጃ አካፍሏል። |”መስከረም 1/2010 ከጉርሱም ወደ ወደ ሀረር እየተጓዙ ያሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆችን የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አካላት ቦምባስ ከተማ ኬላ ላይ ይዘዉ ማሰራቸውን፣ እነዚህ ታሳሪዎች አቶ ሰላማ መሀመድ (የጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበረ)፣ አቶ ታጁዲን ጀማል እና ሌሎች ሁለት ሰዎች፣ በነጋታዉ በደረሰባቸዉ ድብደባ መሞታቸዉን፣ ይህ ግድያ የምስራቅ ሀረርጌ ነዋሪዎችን በማስቆጣቱ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን አወዳይ፣ ደደር፣ ቆቦ እና መልካ ራፉ ከተሞች ያልተጠበቀ የህዝብ ቁጣ እና ሰልፍ ማስከተሉን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ገልጿል። በተለይ አወዳይ የነበረዉ ሰልፍ ወደ ግርግር ተሸጋግሮ በተፈጠረዉ ግርግርም የ18 ሰዎች ህይወት ሊያልፍ መቻሉን፣ በዚህ ግርግር ዉስጥ ህይታቸዉ ካጡ 18 ሰዎች 12 የሶማሌ ተወላጅ ፣ 6ቱ ደግሞ የጃርሶ ጎሳ ተወላጅ ኦሮሞዎች መሆናቸውን አክሎ ገልጿል። “ እዉነታዉ ይህ ሆኖ ሳለ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ይህን ጉዳይ ግጭትን በሚያባብሱ ስሜታዊ ቃላት እና ዉሸትን ጨምሮ አጋኖ ማቅረብ ግጭቱን ከማባባስ ያለፈ ምንም ጠቀሜታ አይኖረዉም፡፡” በማለት ወቀሳ አቅርቦ፣ ከዚህ በፊት ከዚህ ግጭት ጀርባ ያሉ አካላት ተጣርተዉ ወደ ህግ እንደሚቀርቡና የስራቸዉን ዋጋ እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለንም፡ ሲል መግለጫውን ደምድሟል።

No comments:

Post a Comment