Sunday, September 17, 2017

ኢትዮጵያውያን በዘር ፍጅትና በእርስ በእርስ ጦርነት ከመተላለቃችን በፊት ሕወሐት/ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ከስልጣን ይውረድ!!! ( ሰማያዊ ፓርቲ )


ኢትዮጵያውያን በዘር ፍጅትና በእርስ በእርስ ጦርነት ከመተላለቃችን በፊት ሕወሐት/ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ከስልጣን ይውረድ!!!
(ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)

ሕወሐት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከፋፍሎና አዳክሞ ለመግዛት እና ዘላለማዊ ሰላሟን ለማናጋት ቅኝ ገዥዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የዘሩትን የጥላቻ መርዝ እንዳለ በመውረስና የአገዛዙ “ህጋዊነት ማላበሻ” ጨቋኝና ከፋፋይ ህገ መንግስት በማፅደቅ የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች በማጥፋት ልዩነትን እያራገበ ኢትዮጵያን የመበታተን ሂደቱን ህጋዊነት አላብሶ የማፍረስ ተግባሩን ማከናወን ጀምሯል፡፡
በሕወሐት/ኢሕአዴግ ህገ መንግስት የስልጣን ባለቤቶች “ብሔር ብሔረሰብ” የሚባሉት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስልጣን የለውም፡፡ የፌደራል መንግስቱ አባላትም እነዚህ የብሔረሰብ/ጎሳ/ መንግስታት ናቸው፡፡ እነዚህ የጎሳ መንግስታትም እራሳቸውን ያለገደብ የማስተዳደርና ካልፈለጉም የፌደራል መንግስት አባልነታቸውን የመተውና የመገንጠል መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ የህገ መንግስት አስተሳሰብ የሚመነጨው ኢትዮጵያ የብሔረሰቦቸ እስር ቤት እንደነበረችና በሕወሐት/ኢሕአዴግ ህገ መንግስት ብሔረሰቦች ከእስር እንደተፈቱ በማመን ነው፡፡ በሕወሐት/ኢሕአዴግ አስተሳሰብ ቅኝት መሰረት ኢትዮጵያ የምትባለው ሉዓላዊት ሀገር እንደገና ተሰርታ “ብሔር ብሔረሰቦች” ተስማምተው የፈጠሯትና ሲፈልጉ የሚያፈርሷት የጎሳ ስብስብ ሆናለች፡፡
ይህ ከፋፍሎና አዳክሞ የመግዛት ዘይቤ በብዙ ኢትዮጵያውያን ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍና በደል እንዲፈፀም የህግ ሽፋን ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት
1.ከኦሮምያ ብሔራዊ መንግስት ሀገራችሁ አይደለም በሚል አማራዎች ከነነፍሳቸው በገደል ተጥለዋል፣በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ እንዲሁም ከደቡብ “ብሔር ብሔረሰብ” መንግስትና ቤንሻንጉል ጉምዝ መንግስት ሀብት ንብረታቸው ተቀምተው ሀገራቸውን ለቀው ወደ “አማራ ሀገር” እንዲሄዱ ተደርገዋል፡፡
2.በደቡብ ኢትዮጵያ በጌዲዮ “ብሔረሰብ” ዞን ውስጥ “የብሔረሰቡ” አባላት ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን አሰቃቂ ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት ደርሶባቸው ዞኑን ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል፡፡
3.በአሁኑ ሰዓትም በኢትዮጵያ ሶማሌ “ብሔረሰብ” መንግስት ውስጥ የኦሮሞ “ብሔረሰብ” ተወላጆች አሰቃቂ ግድያ እና የንብረት ውድመት ከደረሰባቸው በኋላ ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል፡፡ በዚህ በሁለቱ “ብሔረሰቦች” ግጭት ምክንያት በኦሮምያ ክልል የሚገኙ የሶማሌ “ብሔረሰብ” ተወላጆች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በእኛ ዕምነት ከላይ የጠቀስናቸው ችግሮች የተፈጠሩት ለብሔረሰቦች የተሰጠውን ህገ መንግስታዊ ስልጣን ወደ ተግባር ለመለወጥ በሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ነው፡፡ ግዛቱን ለማስፋትና ኢትዮጵያን ለመቀራመት በሚደረገው ትግል የትግሬው ብሔረሰብ መንግስት ግዛቱን ለማስፋፋት በሚወስደው እርምጃ “ወልቃይት የትግሬ ነው” ሲል ወልቃይቶች ደግሞ “አማራ ነን በህገ መንግስታችን መሰረት የአማራ መንግስት አካል መሆን እንፈልጋለን” በማለታቸው ምክንያት ብዙ የወልቃይት ተወላጆች ተገድለዋል፣ንብረታቸው ወድሟል፣ለእስርም ተዳርገዋል፡፡ የኦሮምያ መንግስትም ኢትዮጵያን በመቀራመቱ ሂደት ውስጥ ድርሻውን ለማስፋትና አዲስ አበባን ለመዋጥ የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የህግ ረቂቅ ልኮ በፓርላማ ለማፀደቅ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌም ይህንኑ መብቱን ለማስከበር ከኦሮምያ ክልል ጋር በሚያዋስኑት አካባቢዎች ግዛቱን ለማስፋት በሚያደርገው ጥረት ከሁለቱም ወገን የብዙ ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል፣በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡ ለብዙ ዘመናት አብረው በመኖር ልዩነታቸው እስኪጠፋቸው ድረስ በብዙ መስተጋብር ተሳስረው የኖሩ ዜጎችን “በቅማንትነት” እና “በአማራነት” ልዩነት በማሰለፍ በሚፈጠረው ልዩነት ሥልጣንና ኃብትን ለማጋበስ የቋመጡ ግለሰቦችና ቡድኖች በፈጠሩት ትርምስ ለትውልድ የሚተርፍ ቂምና ጥላቻ እየዘሩልን ይገኛሉ፡፡
ከላይ ለጠቀስናቸው የሀገራችን ውስብስብ ችግሮችና በህግ ሽፋን ተሠጥቶት ላንዣበበብን የዘር ፍጅት ባለቤቱና አስፈፃሚው ሕወሐት/ኢሕአዴግና ህገ መንግስቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ችግሩ በተፈጠረበት አስተሳሰብ ላይ ሆኖ ለችግሩ መፍትሔ ማምጣት ስለማይቻል ሕወሀት/ኢሕአዴግ ራሱ የፈጠረውን ችግር ሊፈታ የተፈጥሮ ባህሪው አይፈቅድለትም፡፡ይልቁንም ይህንን በሀገር ደረጃ ያንዣበበ ትልቅ አደጋ አቃሎ እንደ ረቂቅ ፍልስፍናና ልዩ እውቀት የጎሰኝነት ተፈጥሯዊ ባህሪ የሆነውን መናናቅና መፈራረጅን “ጠባብነትና ትምክህት” በሚሉ ቃላት አቃሎ ሲያቀርብ ይስተዋላል፡፡
በመሆኑም ይህንን የሀገራችንን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ እንዲቻል ሕወሐት/ኢሕአዴግን ከስልጣን ማውረድ እና ህገ መንግስቱን መቀየር ቀዳሚውና ጊዜ የማይሰጠው የኢትዮጵያውያን አብይ ተግባር መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአገዛዙም ሆነ ልዩነትን ከሚያባብሱና በዘረኝነት ከስልጣን የሚገኘውን ጥቅም በማስላት አድብቶ ከሚጠባበቁ የጎሳ ልሂቃን ምንም ሳይጠብቅ አንድነታችንን በማጠናከርና ልዩነታችንን በማክበር በዜግነት ላይ የተመሰረተች ዴሚክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ከተደቀነብን አደጋ በተለመደው ብልህነትና አስተዋይነት በአሸናፊነት እንድንወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
መስከረም 07 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment