Saturday, September 23, 2017

የህወሃት የስለላ ሃላፊዎች ፖለቲከኞቻቸውን አስጠነቀቁ



  
By ሳተናውSeptember 23, 2017 08:21



ኢሳት – የህወሃት የስለላ ሃላፊዎች ፖለቲከኞቻቸውን አስጠነቀቁ ። የህወሃት የደህንነት ባለስልጣናት (intelligence officers) በአገሪቱ በተለይም በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አደገኛ እና አስፈሪ ነው ሲሉ የድርጅቱን መሪዎች አስጠንቅቀዋል። በሶማሊ ልዩ ሃይል ላይ ያላቸውን ግምገማም አስቀምጠዋል።
ምንጮች እንደገለጹት በምስራቅ ኢትዮጵያ በሶማሊያና በሶማሊላንድ የተደራጁ ታጣቂዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩና ጉልበት እያገኙ መምጣታቸውን የደህንነት አባላቱ ገልጸዋል።
አካባቢውን ያረጋጋል በሚል በመከላከያና በክልሉ መስተዳደር በጥምረት የተቋቋመው የሶማሊ ልዩ ሃይል በማንኛውም ጊዜ ሊከዳና ጠንካራ ውጊያ ከገጠመው በቀላሉ የሚሸሽ በመሆኑ ህወሃት በዚህ ሃይል ላይ የሚያሳየውን መተማመን እንደቀንስ የደህንነት ሃይሎች ለአመራሮች ነግረዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ከደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በፑንትላንድ በኩል የገቡ፣ የኢትዮጵያን ወታደሮች ዩኒፎርም የለበሱ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች በሶማሊ ልዩ ሃይል ላይ በፈጸሙት ጥቃት 36 የልዩ ሃይል አባላት መገደላቸውን የደህንነት ሃላፊዎች ለአመራሮቹ ነግረዋል። እንዲሁም ከሁለት ወራት በፊት 11 የልዩ ሃይል ሃይል አባላት በተመሳሳይ ቦታ ላይ መገደላቸውና አንድ መኪና መቀማታቸው የደህንነት አባላቱ በሶማሊ ልዩ ሃይል ላይ ያላቸው እምነት እንዲቀንስ አድርጎታል።
የህወሃት የደህንነት አባላት ላቀረቡት ግምገማ በባለስልጣናት በኩል አፋጣኝ መልስ አልተሰጠም። ልዩ ሃይሉ ክልሉን በማረጋጋት እና ሰርጎ ገብ ሃይሎች በመከላከል በኩል አወንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የሚገልጹት የህወሃት ባለስልጣናት፣ ለልዩ ሃይሉ የሚሰጡትን ድጋፍ ለመቀነስ ፈቃደኝነታቸውን አላሳዩም።
የሶማሊ ልዩ ሃይልን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች በመልቀቃቸው በአሁኑ ሰአት የመሪነቱን ቦታ የክልሉ ፕሬዚዳንት የአቶ አብዲ ሙሃመድ አማች የሆነው ኮማንደር ከድር እንዲይዘው ተደርጓል። ግለሰቡ በሲቪል ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱ የሶማሊ ልዩ ሃይል የኦፕሬሽን ዋና ሃላፊ አድርገው ከሾማቸው በሁዋላ፣ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የደረሰውን መፈናቀል ጨምሮ ሌሎች ወታደራዊ ኦፐሬሽኖችን መርተዋል።
አቶ አብዲ በሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት ላይ እምነት እያጣ መምጣታቸውም ታውቋል። ከእርሳቸው ጎሳ ውጭ የሆኑ የክልሉ ተወላጆች አብዲ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንዲጋጩ እንዳደረጋቸው በመግለጽ ከስልጣን እንዲወርዱ መጠየቅ መጀመራቸውም ታውቛል። እየተሰማ ያለው ተቃውሞ ፣ የህወሃት ጠንካራ ድጋፍ ያላቸውን ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን ያነሳል ተብሎ አይጠበቅም። አቶ አብዲ ተቃውሞ ማንሳት በጀመሩ የሌሎች ጎሳ አባላት ላይ የከፋ እርምጃ ይወስዳሉ በሚል አንዳንድ የክልሉ ፖለቲከኞች ወደ አዲስ አበባ ሸሽተዋል።

No comments:

Post a Comment