Friday, September 8, 2017

በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ የድንበር ውል አደረግን ሲሉህ ተቀምጠህ ለምትመለከት ትውልድ – ሞትህ ዛሬ መሆኑን ብታውቀው መፈጠርህን ትጠላ ነበር



          


ጉዳያችን / Gudayachn
ጳጉሜን 3፣2009 ዓም (ሴፕቴምበር 8፣2017)
ኢትዮጵያ በህወሓት እና ግብረ አበሮቹ ትናንሽ አዕምሮ ፈርሳ አብቅታለች።ምድሯን በጎሳ ከፋፍለው ድንበር ያሉትን ሰረተው፣ የፈለክበት ተንቀሳቅሰህ እንዳትሰራ መታወቂያህ ላይ የጎሳ ስም ለጥፈውልህ በሕይወት አለሁ ካልክ ተሳስተሃል።ገዢዎች ዙርያህን ምን እየሰሩ እንዳሉ አልታየህም እንጂ መቃብርህን በግሬደር እየቆፈሩልህ ነው።ጥንርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ እያሳዩህ የትኛው መቃብር ላንተ እንደሚስማማህ በእጃቸው ሲያማርጡህ ትንሽ የመደንገጥ ምልክት አታይባቸውም።ከእነርሱ ይልቅ ያንተ መደንዘዝ ያስደነግጣል።ከእነርሱ መደናበር እና አረመኔነት ይልቅ ያንተ በእራስህ እና በልጆችህ ላይ የተደገሰውን የጎሰኞች ድግስ ከቁሌቱ ትንሽ ለአፍንጫህ እንዴት እንዳልሸተተህ በቁም ያስበረግጋል።
ትናንት ጳጉሜን 2፣2009 ዓም የዐማራ ክልልን እወክላለሁ ያሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ትግራይን እንደሰም አቅልጨ እንደገል ቀጥቅጨ የምገዛ ነኝ የሚሉት አቶ አባይ ወልዱ በዐማራ እና ትግራይ መካከል ታሪካዊ የድንበር ውል ተደረገ ብለው እንደ ሁለት የተለያየ ሀገሮች ውል እያስጨበጨቡ እና በሰበር ዜናነት በመገናኛ ብዙሃን ለቀው ምሽቱን የድራማ ምሽት አድረገውት አምሽተዋል። ” ውሃ ሲወስድ አሳስቆ’ እንዲሉ ሁሉም የውሉን አደገኛ ጥላ ከመመልከት ይልቅ ተስማሙ አልተስማሙም እያለ ማውራቱን ቀጥሏል። ከእዚህ ሁሉ ይልቅ ግን ህወሓት እና አጫፋሪው ብአዴን የህዝቡ ተወካይ ናቸው? ሕዝቡ የድንበር ግጭት ነበረበት? ግጭቱን እንደላብራቶሪ ፈጥረው እና አሳድገው የህዝብ ደም እንዲፈስ ያደረጉ የችግሩ መንስኤዎች እራሳቸው አይደሉም? ለመሆኑ የጎሳ ፈድራሊዝም ኢትዮጵያን ወደ እልቂት እየመራት መሆኑን ከበቂ በላይ ማስረጃ የለም? የትግራይም ሆነ የዐማራ ሕዝብ ለሺህ ዓመታት ሲኖር  ተከባብሮ ሲጣላ እየታረቀ የኖረ ሕዝብ አይደለም? በየትኛው የድንበር ውል ነው ለሺህ ዓመታት የሁለቱ ህዝቦች የኖሩት? የትኛው የውል ስምምነት ነው  የወልቃይት ሕዝብ ሽሬ ገበያ  ገብቶ ከብቱን እየሸጠ  የሽሬም ነጋዴ ወርቅ ለጎንደር ገበያ እየሸጠ እንዲኖር ያደረገው? በጣም በሕዝብ ላይ የተደረገ ሸፍጥ ነው።
በትግራይ እና ዐማራ ሕዝብ መካከል ልዩነት ሲፈጥር አይደለም በ1967 ዓም ማኔፈስቶው (እስካሁን ይህ ማነፈስቶ ተሽሯል የሚል ከህወሓት በኩል አልተሰማም ) የዐማራ ሕዝብን ” ጠላት” በሚል ቃል በቃል ያስቀመጠ ህወሓት ኢትዮጵያን በጎሳ ሸንሽኖ የድንበር ውሎች ተደረጉ እያለ ቆይቶ የሚፈነዳ ቦንብ ሲያስቀምጥልህ ተቀምጠህ ለምትመለከት አንተ ትውልድ የመከራ ዘመንህን እያረዘምከው መሆኑን ማወቅ አለብህ። ህወሓት የድንበር ውል እያለ ሲያሳየን በዐማራ እና ትግራይ መካከል የመጀመርያ አይደለም።ከሳምንታት በፊት በኦሮሞ እና ሱማሌ መካከል የድንበር ውል ተደረገ የሚል  ዜና መልቀቁ አይዘነጋም።ሆኖም ከእዚህ ውል ተደረገ በተባለ ማግስት ጀምሮ በሁለት አካባቢ ነዋሪዎች መካከል የለየለት ጦርነት እስከአሁኑ ሰዓት ድረስ እየተደረገ ሲሆን የህወሓት ወታደሮች አድሏዊ በሆነ መልክ የሚጫወቱት አደገኛ ጫወታ ህዝብን ያሳዘነ ጉዳይ ነው።በእዚህ ግጭት ውስጥ ተራ የህዝብ ለሕዝብ መጨራረስ በቀል የታየ ሲሆን በትናንትናው እለትም በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሜኢሶን  ከተማ ትምህርት ቤት ተመዝግበው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ተማሪዎች ላይ በተጣለ ቦንብ አሰቃቂ አደጋ በተማሪዎች ላይ መድረሱ ይታወቃል።ይህ እንግዲህ የጎሳ ፖለቲካው አንዱ እና የቅርቡ ውጤት ነው። በዐማራ እና ትግራይ መካከል ውል ተፈረመ በተባለ በሰዓታት ውስጥ ሁለቱም ክልሎች የመገናኛ ብዙሃን በእየራሳቸው የሚጣረስ ዜና ይዘው ከመውጣታቸው በላይ ሁለቱም ተመሳሳይ ቦታዎች ወደ እኔ ተጠቃለሉ የሚል ዘገባ ይዘው ወጥተዋል። ይህ በእራሱ እንደ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነት እና አንድነት ተምሳሌ ለሆነች ሀገር የመጨረሻ የውርደት ደረጃ ነው። ለነገሩ ሀገሪቱ ሳትሆን የውርደት ሸማው በእዚህ ዘመን ላለን ትውልዶች ነው።በገዛ ሀገራችን ድንበር ሲከለል ድንበር አንፈልግም አንለያይም ብለን የጎሰኞችን ድንበር ማፍረስ ያልቻልን ደካሞች! በገዛ ሀገራችን ያልወከልናቸው ጉግ ማንጉጎች ድንበር ተካለልን፣ተፈራረምን ብለው በሰበር ዜና ሲያሳዩን እናንተ ማን ናችሁ? በስሜ በድንበር ከወንድሜ የዐማራ ሕዝብ ከወንድሜ የትግራይ ሕዝብ ከወንድሜ የኦሮሞ እና ሱማሌ ሕዝብ እንድታካልሉኝ ስልጣን ቀድሞነገር መቼ ሰጠሁኝ? ብለን የማንጠይቅ ከንቱዎች። እኛ ነን የሞት ሞት  የሞትን። እኛ ነን መከራ የሚያንሰን። እኛ ነን ምን እያደረጉ እንደሆነ እና ነገ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጅ በልጆቻችን አንገት ላይ እያሰሩ እንደሆነ ያልገባን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓት እና ግብረ አበሮቹን የክልል ማካለል እና ኃላፊነት የጎደለው እጅግ የተለጠጠ የጎሳ ፖለቲካ እንክትክቱን ካላወጣ እና እራሱ በራሱ ተመካክሮ አኗኗሩን ካልወሰነ በኦሮምያ እና ሱማሌ በጉጄ እና ቦረና ቤንሻንጉል እና ዐማራ እና ሌሎችም ቦታችዎች በማራገብ ብዛት በተቆሰቆሱ የጎሳ ጠቦች ሕዝብ እንዳለቀ ነገ ይሄው ግጭት ወደ ከተሞች ተዛምቶ ኢትዮጵያ ልትወጣው ወደ ማትችለው ማቅ ህወሓት እና አጋሮቹ እንደሚከቷት መረዳት አለብን።እኛ ያልወከልናቸው በስማችን ድንበር ሲከልሉ ቆሞ ማየት ከወንጀሉ ጋር ከመተባበር እኩል ነው።ማን ወከላችሁ? እኛ መቼ ተጣላን? ጥሉም የድንበር ክልሉም ያለውናንተው አእምሮ ውስጥ ነው አታፋጁን! በአንድ ሀገር ውስጥ ድንበር የለም! ይህ ሃገርን የመክዳት እና የመከፋፈል ከባድ ወንጀል ነው! ብለን ልንቃወም ይገባል።የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት እንደሚኖር የሚያውቀው እራሱ ነው።በመሬት ድንበርተኝነት ገበሬው በሚገጥመው ክርክር ሁሉ እንዴት እንደሚፈታ የእራሱ ብሂል እና ዘይቤ አለው።እነኝህ ጥበቦች ናቸው ለሺህ ዓመታት የኖረች ሀገር ፈጥረው ለአፍሪካ በጭንቅ እና የጨለማ የቅኝ ግዛት ዘመን እረዳት እንድትሆን የረዳት። አሁን ወቅቱ ህወሓት የድንበር ውል አደረኩ እያለ በስማችን ሲነግድ በቴሌቭዥን መስኮት እየተመለከትን ከንፈር የምንመጥበት ሳይሆን አንተ ያሰመርከው የጎሰኞችን ድንበር አንቀበልም።በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ የድንበር አጥር ሊኖር አይገባም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቱ ሊጠበቅ ይገባል ብለን በፅናት የምንነሳበት ወቅት ነው።ከእዚህ በተለየ ግን በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ  የድንበር ውል አደረግን ሲሉህ ተቀምጠህ ለምትመለከት ትውልድ – ሞትህ ዛሬ መሆኑን ብታውቀው መፈጠርህን ትጠላ ነበር።

No comments:

Post a Comment