Friday, September 15, 2017

ዛሬ በኦሮሞ ተጀምሯል፣ ነገ በአማራውና በጉራጌው ላይ ይቀጥላል።” የሚሉ አስተያየቶችንም ሰጥተዋል።

ኢሳት ዜና መስከረም 5 ቀን 2010 ዓም) ከሶማሊ ክልል የሚባረሩ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር እየጨመረ ነው
ከተለያዩ የሶማሊ አካባቢ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር እየጨመረ መሄዱንና አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደሚፈናቀሉ የኦህዴድ ባለስልጣናት እየተናገሩ ነው። ዛሬ አርብ በመቶወች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሃረርና ድሬዳዋ የገቡ ሲሆን፣ ህዝቡም ከፍተኛ አቀባባል አድርጎላቸዋል። ጭናክሰን ላይ እስከ ትናንት ምሽት 13 ሺ 98 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ጭናክሰን ትምህር ቤት ተጠልለው የነበረ ሲሆን፣ ቁጥሩ ዛሬ ወደ 20 ሺ ከፍ ማለቱን ዘጋቢያችን ገልጿል። ለእነዚህ ተፈናቃዮች ህዝቡ ምግብና ውሃ እያቀረበ ሲሆን፣ የሃረር መምህራንም ዛሬ ስብሰባ አድርገው ገንዘብ ለግሰዋል።
የሚፈናቀሉት ዜጎች በልዩ ሃይል አባላት በግድ እንዲለቁ መደረጋቸውን እንዲሁም ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እየገለጹ ነው። በጅጅጋ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደገለፁት በከተማዋ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ሙሉ በሙሉ ከከተማዋ የወጡ ሲሆን፣ የቀሩ ሰዎች ይኖራል በሚል ጥርጣሬ የልዩ ሃይል አባላት ዛሬ ቤት ለቤት እየዞሩ መታወቂያ ሲጠይቁ ውለዋል። የእነዚህ ዜጎች ቤት የሰቪል ልብስ በለበሱ የልዩ ሃይል አባላት ሲዘረፍ መዋሉንም የአይን እማኞች ገልጸዋል። በንግድ ስራ የሚተዳደሩና ሃብት አላቸው የተባሉ የኦሮሞ ተወላጆች መታሰራቸውም ታውቋል። ( )
አወዳይ ውስጥ የተገደሉ የሶማሊ ተወላጆች በጅጅጋ ዛሬ የቀብር ስነስርዓታቸው ተፈጽሟል። ስነስርዓቱ በሰላም የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላትና ባለስልጣናት ፣ ከኦሮምያ በተለይም ከአወዳይ የሚመጣውን ጫትና ብርቱካን ህዝቡ እንዳይጠቀም ሲቀሰቅሱ ውለዋል። የሶማሊ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ፣ ከአወዳይ የሚመጣው ጫት ከሩስያ በተሰራ መርዝ በመመረዙ ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም ሲል አስገራሚ መግለጫ አውጥቷል። ይህንን መግለጫ የሚያጠናክር ቅስቀሳ በከተማው እየተካሄደ መሆኑን፣ ነዋሪዎች ይናገራሉ( )
የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ ዛሬ በነበረው የቀብር ስነስርዓት ላይ፣ “መስከረም 2 - 2010 አ.ም በእወዳይ ከተማ ምንም ባለጠፉ እና የሶማሌ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በሀገራችን በየትኛውም ቦታ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተጨፍጭፈው” ተገድለዋል ብለዋል። አቶ አብዲ ለዚህ ድርጊት ፣
ኦህዴድ ጉዳዩን ማራገብ ባለመምረጥ ይመስላል፣ የክልሉ ጫት መመረዙን በመግለጽ የሶማሊ ክልል ላወጣው መግለጫ መልስ አልሰጠም። ያም ሆኖ ግን የክልሉ ተወላጆች ድብደባ እየተፈጸመባቸው ከሶማሊ ክልል ሲባረሩ ምንም ለማድረግ አለመቻሉ በደጋፊዎቹ ዘንድ እንዲተች አድርጎታል።
ዛሬ የክልሉን ምክትል ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሌሎች የኦህዴድ ከፍተኛ ባላስልጣናት ከምስራቅ ሃረርጌ ከተውጣጡ አባገዳዎች ጋር በኦሮምያ ምስራቅ ሃረርጌ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ አሁን ያለው ሁኔታ ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስ አለበት በማለት ለህዝቡ ንግግር አድርገዋል። አባገዳዎች በበኩላቸው፣ “የኦሮሞ ህዝብ ጥፋቱ ምንድነው? ይህን ያክል ህዝብ የተፈናቀለበት ምክንያት ምንድነው?” ደግሞስ ሌሎችን አገር እዳኛለሁ እያለ የሚናገር መንግስት ፣ የራሱን አገር ህዝብ መዳኘት እንዴት አልቻለም?የሌሎችን አገር ሰላም አስጠብቃለሁ በሚል ሰራዊቱን የሚልክ መንግስት የራሱን ህዝብ ሰላም መጠበቅ እንዴት አይችልም ” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
አባገዳዎች፣ “ የሶማሊ መሪዎች እቅድ፣ ኢትዮጵያውያንን ማስወጣት ነው፣ ዛሬ በኦሮሞ ተጀምሯል፣ ነገ በአማራውና በጉራጌው ላይ ይቀጥላል።” የሚሉ አስተያየቶችንም ሰጥተዋል። የኦህዴድ ባለስልጣናት በበኩላቸው ሁኔታዎችን እንደሚያስተካክሉ ቃል ቢገቡም፣ አባ ጋዳዎች ግን፣ “አሁንማ ብዙ ጉዳት ከደረሰ በሁዋላ ስራ እንሰራለን ማለት የሚቻል አይደለም። በፊትም አቶ ለማ መገርሳ ጭናክሰን ላይ ‘ ከእንግዲህ አንድም ኦሮሞ አይገደለም ብሎ ተናግሮ ነበር፣ ነገር ግን ግድያው ተባብሶ ቀጠለ እንጅ አለቆመም በማለት” ባለስልጣናቱን እንደማያምኑዋቸው ገልጸዋል።
በጅጅጋ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ይህን ያክል ወንጀል ሲፈጸም፣ በከተማው አንድም የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አለመኖሩ ብዙዎችን ግራ አጋብቷቸዋል። ከተማዋ በአቶ አብዲ ሙሃመድ በሚመራው እና በሚፈጽማቸው ጭፍጨፋዎች በሚታወቀው ልዩ ሃይል አባላት እየተመራች መሆኑ ፣ ከዚህ ደርጊት ጀርባ የወታደራዊ አዛዦች እጅ አለበት ብለው እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው የጅጅጋ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
አቶ አብዲ “የክልሉ ና የአከባቢው ጸጥታ ሀይልና አመራሮች ዝምታና ተሳታፊነት የሌሎቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው “ እንዲያልፍ አድርገዋል በማለት የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናትን ወንጅለዋል። ከዚህ በሁዋላ የሶማሊ ተወላጆች በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይፈጽሙባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል በአወዳይ ለንግድ ስራ የሄዱ የሶማሊላንድ ተወላጆች ተገድለዋል በሚል የተነሳሱ የሶማሊላንድ ወጣቶች የበቀል እርምጃ እንወስዳለን በማለታቸው እስከ 800 የሚደርሱ የኦሮሞ ተወላጆች በሶስት አካባቢዎች እንዲጠለሉ ተደርጓል። እስከሁን ድረስ የሞተ ሰው ባይኖርም ትናንት በነበረው ግጭት አንድ ሰው መጎዳቱ ታውቛል። የሶማሊላንድ መንግስትና አገር ሽማግሌዎች ወጣቶች በኦሮሞ ተወላጆች እርምጃ እንዳይወስዱ ወጣቶችን ሲያግባቡ ውለዋል። በመጠለያ ቦታዎች ላሉትም ምግብ እና ውሃ እንዳቀረቡላቸው በስፍራው የሚገኙ ኦሮሞ ተወላጆች ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment