Tuesday, September 5, 2017

በህግ እና በእኩልነት ሳይሆን በበቀል ሀገርን የሚያስተዳድር መንግሥት



      |

 




ከሀ.ህሩይ:  ሴብቴምበር, 2017
      የኢህአዴግ መራሹ መንግሥት የበቀል እርምጃ ስውር መሆኑ ቀርቶ ህጋዊ ከሆነ ውሎ አድሯል።  በኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ እና የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጥቅም እና ህልውና የሚያሰጉ ነገሮችን/ጉዳዮችን ለመከላከል  ለሀገር እና ለህዝብ የታሰበ በማስመሰል በርካታ ህጎች፣ ደንቦች፣ ፓሊሲዎች እና መመሪያዎች እየወጡ  ህዝቡ መብቱን እንዳይጠይቅ፣ ሠርቶ እንዳይበላ እና በሀገሩ ጉዳይ እና ሀብት ክፍፍል ላይ እኩል መብት እንዳይኖረው ተደርጓል።

በመሆኑም ይህንን በህዝብ እና በሀገር ላይ የሚፈፀም እኩይ ተግባር በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በህጋዊ መንገድ የተደራጁ ፓርቲዎች እና አባሎቻቸው ለበቀል ማስፈፀሚያነት በወጡ ህጎች ሽፋን ይከሰሳሉ ይገደላሉ ወይም ይታፈናሉ።
 በዚህም መሠረት በዚህ መንግሥት በተደጋሚ ለእስራት የተዳረጉ በርካቶች ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ ባሳለፍነው እና በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ግዜ እና ከዛም በላይ ታስረው በክርክር ላይ ያሉትን (የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ በቀለ ገርባን፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረን እና  የሰማያዊ ፓርቲ  ሊቀመንበርን  አቶ የሺዋስ አሰፋን) መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ዜጎች በአዲስ አበባና በክልል እስር ቤቶች የታጎሩት እና በተንጓተተ የክርክር ሂደት በእስር ቤት የሚሰቃዩት አሸባሪ ሆነው ወይም በአመፅ መንግሥትን ለማስወገድ ተንቀሳቅሰው ሳይሆን የበቀለኛው መንግሥት ሰለባ ሆነው ነው።
         በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በፓለቲካ አመለካከታቸው ወይም የዜግነት መብቸው እንዲከበር በመጠየቃቸው ምክንያት የተከሰሱና የታሰሩ ሰዎች በፓሊስ እና በደህንነት ኃይሎች ከሚደርስባቸው ቶርቸር እና ኢሰብአዊ አያያዝ በተጨማሪ ጉዳያቸውን በሚያየው ፍ/ቤትም ለምርመራ እየተባለ በተደጋጋሚ ለፓሊስ በሚሰጥ ተጨማሪ ግዜ፣ ጉዳዩን በያዘው ፍ/ቤት እና በከሳሽ ዓቃቤ ህግ በሚቀርቡ የማይረባ ምክንያቶች በሚለወጥ ቀጠሮ ተከሳሾቹ ያለ ፍርድ እየተሰቃዩ ለአመታት እንዲታሰሩ የሚደረገው ሌላው የመበቀያ መንገድ ነው።
 ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ህግና ደንብን  ከለላ አድርጎ ከሚወስደው የበቀል እርምጃ አልፎ በትላንትናው ቀን መርዛማ የበቀል በትሩን  በመሰንዘር ብዙ በደል ያደረሰበትን  አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)  አልበሙን እንዳያስመርቅ አሰናክሎበታል።  ይህ አሳፋሪና አምባገነናዊ እርምጃ የሚያረጋግጠው ገዥው ፓርቲ ምን ያህል በቀለኛ እና ከህግ በላይ መሆኑን ነው።
ስለዚህ ሀገራችን አንድነቷን ጠብቃ ዜጎች በእኩልነት፣ በነፃነት፣ በሰላም እና በፍቅር እንዲኖሩ ከተፈለገ መከፋፈልን አስወግደን የህግ የበላይነት የሚሰፍንባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት በአንድ ላይ መቆም አለብን።
መጭው አዲስ ዓመትም ይህንን የምናይበት ይሁንልን።

No comments:

Post a Comment