የጉድ ሐገር !!!!
(ከአቶ ግርማ ሰይፉ ገፅ የተገኘ አሳዛኝ መረጃ)
ዛሬ ጠዋት ከቤቴ ወጥቼ ልጆች ትምህርት ቤት ካደረሰኩ በኋላ የተገኘሁት ቦሌ ክፍለ ከተማ ዐቃቢ ህግ ቢሮ ነበር፡፡ አብሮኝ የሸዋስ አሰፋ ነበር፡፡ ያጎደልኩት ካለ ይጨምርበታል፡፡ የተጋነነ የለውም፡፡ የሄድንበት ምክንያት ወደጆቻችን ኤሊያስ ገብሩ እና ዳንኤል ሸበሺ ለረጅም ጊዜ በእስር በመቆየታቸው ፋይላቸው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጉዳያቸውን እየተመለከተው ይገኛል ከሚባለው ዐቃቢ ህግ ሃላፊ ጋር ለመነጋገር ነበር፡፡ ሃላፊው አቶ ዘለቀ ይባላል፡፡ ጠዋት ከቢሮ ብንገኝም አቶ ዘለቀ ለአራት አስር ጉዳይ ሲል ወደ ቢሮ ገቡ፡፡ ማርፈዳቸው ቢገባቸው ብዬ ይቅርታ ገና ከመግባቶ የመጣነው ውጭ ትንሽ ሽለቆየን ነው በማለት ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ማርፈዳቸው ምንም ግድ አልሰጣቸውም፡፡ ያለምንም ቢሮክራሲ ቢሮ ገብተን ማናገር ጀመርን፡፡ ምንም ቢሮክራሲ የማያውቁት አቶ ዘለቀ ላቀረብንላቸው ጥያቄዎችም አንድም የሲቪል ሰርቪል ደንብና ህግ፣ የአገልጋይነ መንፈስ የለባቸውም፡፡ ዐቃቢ ህግ የሚለው ነገር ትርጉም ካልተቀየረ በስተቀር ለህግ ልዕልና የሚቆም ባለሞያ የሚሰጠው ስለ ሰው ልጅ ስብዓዊ መብት ግድ የሚሰጣቸው ሆኖ አላገኘኋቸውም፡፡ ዝርዝሩን ልነግራችሁ አልችልም ብዙ ነው፡፡ ለማሳያ ያክል ላካፍላችሁ፡፡
ለአቶ ዘለቀ የመጣንብተን ጉዳይ አስረዳናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች በእስር ስድስት ወር ሊሞላቸው ነው፡፡ ወይ ፍርድ ቤት አልቀረቡም፤ ወይም እንደሌሎች ስልጠና ወስደው አልተለቀቁ እና ጉዳያቸው ምን እንደደረሰ ለማወቅ እና አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ እንዲያግዙን ነው፡፡ አልኳቸው፡፡ የአቶ ዘለቀ መልስ “ለምን ይፈጥናል እነዚህ እኮ ሀገር ሊያፈርሱ የነበሩ ናቸው፡፡” ብለው በግል ጠብ ያላቸው የሚያስመስል ነገር ነገሩኝ፡፡ እነርሱ ባስነሱት ጦስ “ሀገር ልትፈርስ ለጥቂት ነው የዳነችው” ብለውኝ አረፉት፡፡ አለቆቻቸው የሲኒ ማዕበል ነው ሲሉ እርሳቸው ደግሞ ሀገር ልትፈርስ ለጥቂት መዳኗን፣ የዳነችውም እነ ኤሊያስ ገብሩ በመታሰራቸው እንደሆነ እና አገር የሚፈርሰው እነዚህ ልጆ በፌስ ቡክ ላይ በሚለጥፉት ፅሁፍ መሆኑ ገረመኝ፡፡ አቶ ዘለቀን አግባብቶ ወደ ቁም ነገሩ ለመውሰድ ብዬ፡፡ መቼም ይህ የሚነግሩኝ ጉዳይ ለጫወታ ሊሆን ይችላል፤ እነዚህ ልጆች ጥፋተኛ ከሆኑም ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጥ ፋይላቸው ፍርድ ቤት መቼ እንደሚቀርብ ማወቅ ፈልገን ነው የመጣነው አልናቸው፡፡ “ምን ያሰቸኩላል እያጣራን ነው ስንጨርስ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡” አሉን፡፡ በዚህ መሃክል ቤተሰብ ይፈርሳል፣ ጥፋተኛ ካልሆኑ ደግሞ ፍትህ ይዛባል ሰለዚህ እንዲፋጠን የፈለግ ነው ለዚህ ነው ብለን ሃሳባችንን ሳንጨርስ፤ “ይፍረሳ (ቤተሰቡ ማለታቸው ነው)፤ እነርሱ አኮ ሀገር ለማፍረስ እንጨት ይዘው ሲጎረጉሩ ነበር፡፡” በማለት ሀገር የሰጋቱራ ክምር ይመስል በእንጨት ጉርጎራ የምትፈረስ አደረጉና ግራ አጋቡን፡፡ አቶ ዘለቀ ሀገር እኮ የቤተሰብ ድምር ነው ብዬ ጣልቃ ስገባ፤ “እሱን አላጣሁትም፣ አገር ከሚፈርስ ግን አንድ ቤተሰብ ቢፈርስ ችግር የለውም ነው የምልህ፡፡” ብለው አስረግጠው ደገሙልኝ፡፡
ተመሳሳይ መልሶችን ለሌሎችም እንደሰጡ ተረድቻለሁ፡፡ እነዚህ ልጆች በጣቢያ በእስር ቤት ውስጥ ሆነው ሁሉ የሚሰሩትን እንደሚያውቁ፤ በኢሣት እና በቪኦኤ በፌስ ቡክ ስለነሱ ብቻ እንደሚወራ እንደሚያውቁ፤ መግለጫ ሰጡን፡፡ ይህን ፅሁፍ የፃፍኩትም አንባቢ ከእነ ኤሊያስ እና ከአቶ ዘለቀ አገር የሚያፈርስ ማን ነው? ብዬ ለመጠየቅ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ በመንግሰት መስሪያ ቤት አገልግያለሁ፣ በዚህ ደረጃ ለተገልጋይ መልስ የሚሰጥ በኃላፊነት ደረጃ ያለ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በዚህ ደረጃ ሃላፊነት ያለበት ሰው የተጠየቀውን ጥያቄ የግል ሰሜቱን ዋጥ አድርጎ የስራ ሂደቱን በመንገር መረጃ ከመስጠት ሃልፎ አንድን ቤተሰብ ቢፈርስ ግድ እንደማይሰጠው ሲነግረኝ መስማት ያሳምማል፡፡ አንድ መስሪያ ቤት የያዘውን ጉዳይ መቼ ጀምሮ መቼ እንደሚጨርስ የሚቀመጥ ጊዜ በመኖሩ ይህ ጊዜ ካልተቻለ ደግሞ ምክንያቶች መግለፅ እንደሚቻል ማንም ያውቃል፡፡
ለማነኛውም በእኔ እምነት ይህች አገር የምትፈረሰው ኤልያስና ዳንኤል ፅፈው በሚለጥፉት መልዕክት ክፋትና መጥፎነት ሳይሆን የመንግሰት የሃላፊነት ቦታዎች በተለይ ደግሞ በህግ ሊመሩ የሚገባቸው ዓቃቢ ህጎች ዓቃቢ ፖለቲካ ከሞያቸው ይልቅ ካድሬነታቸው ሲያመዝን ነው፡፡ እነ ዘለቀ የጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ከሆኑ፣ የወረድንበትን ዝቅጠት ጥልቅነት ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሠጣጥ እዚህ ደረጃ መውረዱ ያሳዝናል፡፡ በፌስ ቡክ ስለ እነ ኤሊያስ ብቻ ይወራል ያሉት አቶ ዘለቀ ደስ ይበላቸው ይኽው ስለ እርሳቸውም አወራን፡፡
No comments:
Post a Comment