Wednesday, April 5, 2017

የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንም ፈረሰ | የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ፥ ቀኖናን ጥሷል፤ ምስጢራትን ደፍሯል፤ ንዋያተ ቅድሳትን መዝብሯል



  • የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ፥ ቀኖናን ጥሷል፤ ምስጢራትን ደፍሯል፤ ንዋያተ ቅድሳትን መዝብሯል
  • ደብሩ፣ በወረዳው ሥራ አስፈጻሚ እና በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ሓላፊዎች ላይ ክሥ መሠረተ
  • ተመሳጥሮ በማፍረሱ፥ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው የተባለው፣ ‘አባ’ ኃይለ ሚካኤል ካሳ ታገደ
  • ጸሎቱ እና ትምህርቱ አልተቋረጠም፤ ኹሉም እንደ ልቅሶ ደራሽ እንባውን አፍስሶ ይሔዳል
***
  • ሮሮው ተባብሶ አቅጣጫ ሳይለውጥ ፍትሕ ርትዕ የተሞላበት ዳኝነት ይታይ”/ፓትርያርኩ/
  • ይዞታ፣ በስጦታ ተገኘ፤ በሚል ብቻ ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ አይችልም”/የከንቲባው /ቤት/
  • “የይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱን የእግድ ትእዛዝ እያሳየናቸው ማፍረሳቸው ሕጉን መናቅ ነው”/ደብሩ/
  • “ታቦቱ ባለበት በንብረቱ ላይ ተራምደው ከነጫማቸው ገቡ፤ መንበሩንም ጭነው ወሰዱ/ምእመኑ/
***
(ሰንደቅ፤ ፲፪ኛ ዓመት ቁጥር ፮፻፬፤ መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)


በአዲስ አበባ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12፣ አባዶ ቁጥር 1 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተሠራችው፣ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን፥ ድፍረት በተመላበት ኃይልና ሥልጣን፣ በወረዳው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤትእንደፈረሰች ፓትርያርኩ የጠቀሱ ሲኾን፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚያሰማው ሮሮ ተባብሶ አቅጣጫውን ከመለወጡ በፊት፦ ፍትሕ ርትዕ የተሞላበት ዳኝነት ታይቶ፣ የፈረሰው ተጠግኖ፣ የጎደለው ተሟልቶ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል አመራር ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍ ከንቲባ ድሪባ ኩማን አሳሰቡ፡፡
የደብሩ ይዞታና ግንባታ፣ ሕገ ወጥ ነው፤ በሚል ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትፈርስ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ፣ የይግባኝ ቅሬታ ቀርቦበት እንዳይፈጸም ታግዶና በቀጠሮ ላይ እያለ፣ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በሚያሳዝን ኹኔታ፣ ታቦተ ሕጉ ያለበት መቃኞ ቤተ ክርስቲያን በመፍረሱ፥ ንዋያተ ቅድሳቱ ተመዝብሯል፤ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንም የድፍረት ሥራ ተፈጽሞባቸዋል፤” ብለዋል ፓትርያርኩ፣ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ ለከንቲባው በጻፉት ደብዳቤ፡፡

የከተማው አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ ሳይታወቅና ጉዳዩ በቀጠሮ ላይ እያለ፣ በወረዳው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሠራተኞች የተፈጸመው ድርጊት፣ አፍራሽ ተልእኮ ያለውና ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት መኾኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ “ለሕግ የበላይነት ትኩረት አለመስጠትን ያመለክታል፤” ሲሉም ተችተዋል፡፡
ምእመናን ከመንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይርቁ፣ በየአቅራቢያቸው ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበት ቤተ ክርስቲያን እያቋቋሙ፣ ከርቀት ጉዞ በመታደግ የሥራ ተነሣሽነት እንዲኖራቸው ማስቻል፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሀገራዊ ልማት ባላት አስተዋፅኦ ኅብረተሰቡን የምትደግፈበት አገልግሎትዋ እንደኾነ ፓትርያርኩ አስገንዝበዋል፡፡
ይኹንና መንግሥት ለዜጎች ባመቻቸው የየካ አባዶ ቁ.1 ኮንዶሚኒየም አካባቢ፣ ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች በተሰጠ ቦታ ላይ ተሠርታ ላለፉት አራት ወራት አገልግሎት ስትሰጥ የቆየችው የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን፣ ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል በመፍረሷ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚያሰማው ሮሮ ተባብሶ አቅጣጫውን ከመለወጡ በፊት ፍትሕ ርትዕ የተሞላበት ዳኝነት እንዲታይ፣ ፓትርያርኩ በደብዳቤአቸው ጠይቀዋል፡፡ “የፈረሰው ተጠግኖ፣ የጎደለው ተሟልቶ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል አመራር” ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍላቸውም ከንቲባውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም አሳስበዋል፡፡
(የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ)
ፓትርያርኩ ለጻፉት ማሳሰቢያ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ በከንቲባው ጽ/ቤት በኩል ምላሽ እንደተሰጣቸው የጠቀሱት የደብሩ ካህናትና ምእመናን፦ የቤተ ክርስቲያኒቱ ግንባታ ሕገ ወጥ እንደኾነና ቤተ ክርስቲያን ሊባል እንደማይችል፤ ይዞታው ከግለሰቦች የተላለፈበት የስጦታ ውልም፣ በውልና ማስረጃ ያልተረጋገጠ በመኾኑ ተቀባይነት እንደሌለው በሓላፊው በኩል እንደተነገራቸው አስታውቀዋል፡፡
አክለውም፣ የፈረሰችውን የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በወረዳው በቅርቡ ከተሠሩ ስምንት አብያተ ክርስቲያናት ጋራ በተያያዘ፣ በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ አዘጋጅነት በቅርቡ የተካሔደው የሽልማት መርሐ ግብር፣ ተገቢ እንዳልነበረ ሓላፊው መተቸታቸውንና “በዚኽ ጉዳይ የሚጠየቅ አካል ይጠየቃል፤” ማለታቸውን ተናግረዋል፤ የይዞታ መብት በስጦታ ተገኘበሚል ብቻ ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ እንደማይችልና የከተማውን ማስተር ፕላን በጠበቀ መልኩ ከሚመለከተው የከተማው አስተዳደር አካል ጋራ በመነጋገር የግንባታ ፈቃድ አስቀድሞ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተገልጾልናል፤ ብለዋል፡፡
ነገር ግን፣ ማሳሰቢያው የተጻፈው በቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ እንደመኾኑና ባለአድራሻውም የከተማው ከንቲባ እንደመኾናቸው ጉዳዩ ደረጃውን ጠብቆ ምላሽ ሊሰጠው ይገባ እንደነበር ቅሬታቸው የገለጹት ካህናቱና ምእመናኑ፣ በጽ/ቤቱ የተስተናገዱበት ኹኔታ “ክብረ ነክ ነው፤” ሲሉ አማርረዋል፤ “እናንተን ማስተናገድ አይገባኝም፤ እንዲያውም ውጡ” መባላቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ከይዞታና ከግንባታ ሕጋዊነት ጋራ በተያያዘ፣ ባለፈው ሳምንት ሰኞ፣ መጋቢት 18 ቀን ጠዋት የፈረሰችው የየካ አባዶ ደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፥ ለይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የእግድ ትእዛዝ አለመከበር ተጠያቂዎች ናቸው ባላቸው፦ የወረዳ 12 የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ዳዊት ሙሉጌታ፤ የአስተዳደሩ ሥራ አስፈጻሚ ሓላፊ አቶ ደመላሽ ጎሣ እና በሌላ የመዝገብ ቤት ሠራተኛ ላይ ክሥ መሥርቷል፡፡
“ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትፈርስ በሥር ፍ/ቤት በተላለፈው ውሳኔ ላይ፣ በደብሩ የቀረበው የይግባኝ ቅሬታ ተመርመሮ ትእዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ተፈጻሚ እንዳይኾን የታዘዘበትን እግድ እያሳየናቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ማፍረሳቸው፥ የሕግ የበላይነትን አለማረጋገጥና ሕጉን መናቅ ነው፤” ይላሉ፣ የደብሩ ካህናትና ምእመናን፡፡ ችሎቱ፣ የተከሣሾችን መልስ ለመስማት፣ ለሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. መቅጠሩ ተገልጿል፡፡

በዚያው በየካ አባዶ፣ ቁጥር 13 የሚገኘው፣ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን፣
 ከትላንት በስቲያ፣ መጋቢት 25 ቀን ረፋድ ላይ፣ በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ግብረ ኃይል መፍረሱ ታውቋል፡፡ ጽላቱ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ዋሻ መዛወሩ ተገልጧል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ የቆርቆሮ ክዳንም የተነሣ ሲኾን፣ ንዋያተ ቅድሳቱ እዚያው ሜዳ ላይ ተቀምጦ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ኹኔታው፣ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሪፖርት ቢደረግም፣ እዚኽ ግባ የሚባል እንቅስቃሴ አለመኖሩ ተጠቁሟል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከፈረሰችው የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቀጥሎ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን፣ በአካባቢው በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ የፈረሰ ኹለተኛው ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የየካ አባዶ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንም፣ እንዲፈርስ በሥር ፍርድ ቤት ቢወሰንም፣ የይግባኝ ቅሬታ በመቅረቡ፣ ውሳኔው ከመፈጸም ታግዶ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ይገኛል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የአሠራር ክፍተቱንና ከወረዳው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ጋራ የተፈጠረውን ውዝግብ በመጠቀም፣ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እንድትፈርስ፣ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው፤ የተባለው፣ ‘አባ’ ኃይለ ሚካኤል ካሳ፣በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት፣ ከሥራና ከደመወዝ መታገዱ ታውቋል፡፡

‘አባ’ ኃይለ ሚካኤል፣ በአቅራቢያው የምትገኘው የጽርሐ አርያም ቅድስት ማርያም “ጥብቅ አስተዳዳሪ” ሲኾን፣ በተሰጠው ሓላፊነት፣ ቤተ ክርስቲያን እንድትስፋፋና እንድትጠናከር መደገፍና መርዳት ሲገባው፣ በተቃራኒ መልኩ፣ “ከሃይማኖታችን ውጭ ከኾኑ አካላት ጋራ በመመሳጠር የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እንድትፈርስ” ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ሙሴ ዘነበ ተፈርሞ፣ በቁጥር 403/35/09፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በወጣው እግድ እንደሰፈረው፥ ‘አባ’ ኃይለ ሚካኤል ካሳ፣ በአስገዳጅ ኹኔታዎች ሳቢያ፣ በሰበካው በዐዲስ መልክ የሚቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናትን፣ “እንደ ሙዳይ ምጽዋት ወደረኛ/ተቀናቃኝ” ነው የሚያያቸው፡፡
በአንዳንድ ምንጮች መረጃ፣ በአካባቢው የተለያዩ ሳይቶች፣ በዐዲስ መልክ ለማቋቋም የተሞከሩ ከአምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንዲፈርሱ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል፤ የተወሰኑት ጽላት ከሚመራው ደብር ጋራ ሲደርቡ፣ ጠፍተው የቀሩ መኖራቸውም ተጠቅሷል፡፡ በዚኽ መነሻ፣ ‘አባ’ ኃይለ ሚካኤል፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተደጋጋሚ ምክር ቢሰጠውም ሊታረም እንዳልቻለ፣ በእግድ ውሳኔው ተመልክቷል፡፡
በቤተ ክርስቲያን መዋቅር መሠረት ለክፍለ ከተማው እንደማይታዘዝና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው፣ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ አስታውሶ፣ ነገር ግን ሊስተካከል ባለመቻሉ፣ ከመጋቢት 22 ቀን ጀምሮ፣ ከጽርሐ አርያም ቅድስት ማርያም ጥብቅ አስተዳዳሪነት መወገዱንና ከደመወዝ መታገዱን አስታውቋል፤ ጉዳዩንም በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እንዲከታተል አሳስቦታል፡፡
‘አባ’ ኃይለ ሚካኤል፣ ዐዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይቋቋሙ ብቻ ሳይኾን፣ በሓላፊነት የተቀመጠበትንም ደብር አስተዳደርና አገልግሎት በአግባቡ እንደማያስፈጽም፣ የአጥቢያው ምእመናን በምሬት ይናገራሉ፡፡ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ባስፈረሰ ቁጥር፣ በሚመራው ደብር ባልነበረና ባልተሠራ ሥርዓት፥ “ንግሥ” እያለ ታቦት ያወጣል፤ በያዝነው ዐብይ ጾም ውስጥ ብቻ፣ “ቅዳሴ ቤቱ” ብሎ የካቲት 19 ቀን፤ “ንግሥ” ብሎ የደብረ ዘይት እሑድ፣ የቅዱስ ገብርኤልንና የእመቤታችንን ታቦታት አውጥቷል፡፡ በጥምቀት በዓል፣ ከሌሎች ታቦታት ጋራ ወደ ባሕረ ጥምቀት ላለመውረድ፣ ቦታ እስከመቀየር ሙከራ አድርጎ የተከለከለው በጸጥታ ኃይሎች ነበር፡፡
ዐውደ ምሕረት ላይ በወጣ ቁጥር፣ የኾኑ አርቲስቶችን ሳያስከትል አይወጣም፤ ታቦቱን አቁሞ ነገር ዘርቅ ያወራል፤ ያስወራል፤ ጨረታ እያለ ብር ከሰበሰበ በኋላ እብስ ይላል፤ ያልተፈቀዱና ሕጸጽ ያለባቸውን መዝሙር ተብዬዎች ይከፍታል፤ የዙሪያውን አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና ካህናት፥ “አወናባጆችና ሥራ ፈቶች” እያለ ያጥላላል፤ ይዘልፋል፤ ከስብሐተ እግዚአብሔሩም ኾነ ከትምህርተ ወንጌሉ የለበትም፡፡
በግል ሕይወቱም፣ ለሥርዓተ ምንኵስና የታዘዘውን በመፃረር፣ እንደ ባለትዳር ነው የሚኖር ሲኾን፣ የልጅም አባት ነው፡፡ ብዙዎች በተጨባጭ እንዳረጋገጡት፣ ቆብና ቀሚሱን እንደለበሰ የምሽት ክበቦችን የሚያዘወትር ዋልጌ ነው፡፡ ይኸው አነዋወሩ፣ ገና በሺንሺንቾ ወረዳ ቤተ ክህነት ሳለ፣ ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ የሚታወቅና በቀኖናዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች ለማስተካከል ቢሞከርም የሚያርመው አልኾነም፤ ይህም ኾኖ፣ በቅርቡ ለደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት፣ በቋሚ ሲኖዶስ ከተመደቡትና ለጉዞ ከተዘጋጁት ልኡካን አንዱ መኾኑ በርካታ ወገኖችን አሳዝኗል፡፡
በወረዳ ቤተ ክህነት ደረጃ፣ ለቤተ ክርስቲያን መስፋፋትና መጠናከር ጠንቅ ነው ተብሎ ርምጃ የተወሰደበትን ብቃቱ ይኹን ሕይወቱ የሌለውን ግለሰብ፣ ይባሳችኹ ብሎ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በብዙ ተስፋ ወደሚጠብቋትና የላቀ ሐዋርያዊ አገልግሎት ወደሚሹ ወገኖቻችን መላክ፣ ትልቅ ምፀት ነው፤ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ላይም ከመሣለቅ ተለይቶ አይታይም!!
የ‘አባ’ ኃይለ ሚካኤል ምደባ ዳግመኛ ሊጤንና በጥብቅ ሊታሰብበት የሚገባ ኾኖ፣ ቤተ ክርስቲያናቸው የፈረሰባቸው የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሮሮም፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳሉት፣ ፍትሕ ርትዕ የተሞላበት ዳኝነት በአፋጣኝ ሊታይበት ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment