Friday, April 28, 2017

ኢሳያስ እና ሻቢያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የችግር ወይስ የመፍትሔ አካል? (በወረታው ዋሴ)

    
ኢሳያስ እና ሻቢያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የችግር ወይስ የመፍትሔ አካል?  (በወረታው ዋሴ)
«ኦኤምኤን» የተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሻቢያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩት፡፡ ከኢሳያስ ዲስኩር ምንም አዲስ ነገር አላገኘሁም፡፡ ሰውየው የኢትዮጵያን ፖለቲካ እያማሰለ መኖር ዋናው የህይወት መርሁ መሆኑን በግልፅ አሳይቷል፡፡ እርሱ የተነሳበትንና ማን እንደነበር አሁን ያለው እብሪቱ ጨርሶ ከጭንቅላቱ አጥፍቶበታል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለውን የአማሳይነትና የበጥባጭነት ሚና ለማሳካት ለተለያዩ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በሚያደርገው ድጋፍ ልቡ ምን ያህል በእብሪት ማበጡንና ለሌሎች ድጋፍ ማድረግ የድጋፍ አድራጊውን ታላቅነትና የድጋፍ ተቀባዩን ትንሽነት ለማሳየት ከመመሪያ ሰጭነትና ከአስተማሪ ነኝ ባይ ድስኩሩ ተረድቻለሁ፡፡
ኢሳያስ ድጋፍን ከሌሎች መቀበል ታናሽነትን የሚያሳይ መሆኑን ሲነግረን ከሁሉ አስቀድሞ የመጀመሪያው ታናሽ ራሱ መሆኑን ግን ፈፅሞ ረስቶታል፡፡ ኢሳያስ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የጀመረውን ደባ ለማሳካት ኢትዮጵያን ለመበታተንና ለማዳከም ከሚፈልጉ ሀገሮች ማለትም ሶማሊያ፣ሶሪያ፣አልጀሪያ፣ግብፅ፣ኳታር እና ኢራቅ ፓስፖርት ተዘጋጅቶለት በየቤታቸው እየዞረ በተረጅነት ሲቀላውጥ የኖረ ታናሽ ሰው ነው፡፡ ዛሬ ያ ተረጅነቱ በግርዶሽ ወደተሞላው ጭንቅላቱ ወርዶ መናገርና ማስመሰል የሚፈልገው ድጋፍ አድራጊነቱን ብቻ ሆኗል፡፡
ሻቢያና ኢሳያስ ወደስልጣን ከመውጣታቸው በፊትም ሆነ አሁን በስልጣን ባሉበት ዘመን በርዕየተ አላማቸውና ስለኢትዪጵያ አራምባና ቆቦ የሆነ አመለካካት ያላቸውን ድርጅቶችን እንደ ኢህአፓ፣ ኦነግ፣ ወያኔ፣መኢሶን እና ሌሎችም በተመሳሳይና በተለያዬ ጊዜ ሲደግፍና ሲያስታጥቅ ቆይቷል፡፡ ሻቢያ የተለያየ አቋም ያላቸውን ድርጅቶች የሚደግፋቸው ድርጅቶቹ በሚያደርጉት ትግል ምክንያት ኢትዮጵያን በማዳከም እንደየወቅቱ ሁኔታ ሊያሳካ የሚፈልገውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ቀላል እንዲሆንለት በማሰብ ነው፡፡
ኢሳያስ እና የሚመራው ድርጅት ሻቢያ እያደረጉ ያሉት ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመበታተን ከሚፈልጉ ሀገሮች የተቀበለውን ኢትዪጵያን እስከመጨረሻው የማፍረስ የቤት ስራ ለመጨረስ እንጅ መቸውንም ቢሆን ለተሻለች ኢትዮጵያ ቅንጣት አስተዋፅዖ ለማድረግ አይደለም፡፡ ዛሬ በከፋፍለህ ግዛው ብሂል በተዳከመችዋ ኢትዮጵያ በድንበር ይገባኛልና በሌሎች ባልተሳኩ የደባ ጥቅሞች ምክንያት በውዝግብ ውስጥ የገባው ኢሳያስ ጠንካራዋ ኢትዮጵያ መቸም ቢሆን እረፍትና መረጋጋት እንደማትሰጠው ስጋቱና የቀን ቅዠቱ እንደምትሆንበት ይረሳል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው፡፡ በአንፃሩ ይህንን እውነታ በሚገባ እየተረዱ ሃቁን ሸፍኖ ከሻቢያ ጋር በማበር ለኢትዮጵያ የተሸለ ነገር እናመጣለን በማለት የሚደረገው ነገር ሁሉ አንድም የፖለቲካ አድርባይነት ነው ወይም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚደረገው የቤት ሥራ የበኩላቸውን ድንጋይ ለመወርወር የሚሯሯጡ ወገኖች የደባ ስራ ነው፡፡
በመግቢያዬ አካባቢ እንደገለፅኩት ሻቢያና ኢሳያስ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እጅግ የተራራቀ አመለካከት ያላቸውን ድርጅቶች እንደ ኢህአፓ፣ ኦነግ፣ ወያኔ፣መኢሶን፣ግንቦት ሰባት እና ሌሎችም ነፃ አውጭ ነን የሚሉ ድርጅቶችን ሲደግፍ እንደነበረና አሁንም እየደገፈ እንደሆነ ኢሳያስ በቃለ ምልልሱ ነግሮናል፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር በአመለካከታቸው እጅግ የተራራቁና እርስ በእርስ በጠላትነት የሚፈላለጉ ድርጅቶችን አንዱ ሻቢያ ድጋፍ ሲያደረግላቸው የተነሱለት ዓላማ እንዳይሳካ እየሰራባቸው መሆኑን አለመረዳት የእነዚህ ድርጅቶች የፖለቲካ አስተሳሰብ አርጧል ወይም በአድርባይነት የሚፈልጉትን ነገር በአቋራጭ ለማግኘት ከመሮጥ ያለፈ ራዕይ የሌላቸው ናቸው፡፡
እጅግ የሚያስገርመው እስካዛሬ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመበታተን በሚፈልጉ ሀገሮችና በሻቢያ የተሰራብንን ደባ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ በማለፍ ከሻቢያና ከኢሳያስ በሚደረግ ድጋፍ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ መንግስት እንመሰርታለን በማለት የሰውን ልጅ ክቡር ሕይወት በከንቱ የሚያስቀጥፉና የብዙ ለሐገራቸው ቀና አመለካከት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጊዜና ገንዘብ እያባከኑ አካሔዳቸው ስህተት እንዳለበት ሲነገራቸው እንደ አበደ ውሻ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ሰዎችን ስመለከት የፖለቲካ አድርባይነትና የግል ፍላጎት ያወረውን የእነዚህን ድርጅቶች የፖለቲካ አስተሳሰብ ለማረቅ ፈታኝ ትግል እንደሚጠይቅ ተገንዝቢያለሁ፡፡
ለማጠቃለል በታሪክ እንደምንገነዘበውና አሁንም በቃለ ምልልሱ እንደተረዳሁት በኢሳያስና በሻቢያ ድጋፍ ለኢትዮጵያ መልካም ነገር እናመጣለን ማለት ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደመጠበቅ ነው፡፡ስለሆነም የኢትዮጵያ ሃቀኛ የፖለቲካ ሃይሎች ይህንን አውዳሚ ተግባር በይፋ ልንታገለው ይገባል፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment