Monday, April 24, 2017

ያሽቆለቆለው የትምህርት ጥራት የት ያደርሰን ይሆን? ( ያለው አክሊሉ )

    


ከእግዚአብሔር በታች ሰውን ዳግም የሚፈጥር ኃይል ቢኖር ትምህርት ብቻ ነው፡፡ ስለ ትምህርት ጠቀሜታ በዘርፉ የተራቀቁ ሊቃውንት ያሰፈሯቸውን አያሌ ፍሬ ሀሳቦች በዋቢነት እያነሱ ማጣቀስ ይቻላል፡፡ ትኩረቴ ግን ለውጤታማ የትምህርት ሥርዐት በግብዐትነት የሚታሰቡ ፍሬ ነገሮች በሚያስከትሉት አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ግብ ላይ ብቻ ማተኮር ነው፡፡
የመደበኛ ሥርዐተ – ትምህርት ይዘት መነሻ የመንግሥት ፖሊሲ ነው፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎች መንደርደሪያ ሕገ-መንግሥት ሲሆን የእሱ ምንጭ ደግሞ የሕዝብ ፍላጎት ነው፡፡ መቸውንም ቢሆን ሕዝብ ከራሱ ጥቅም ህልውና ጋር የሚጋጭ ምርጫ ይከተላል ተብሎ አይታመንም፡፡ ሆኖም በእኔ አውቅልሃለሁ ዕብሪት ጥቂቶች የባበሩን መሪ አንቀው በተበላሸ ሃዲድ ማሽከርከር ሲጀምሩ አንዱ ጎድቤል ገብተው እስኪገለበጡ ድረስ የእውነቱም የውሸቱም ብቸኛ ሊቅና ልሂቅ ይሆኑና፣ ሕዝብ አውራነቱ ቀርቶ በተከታይነት እየተፈረጀ፣ አዕላፍ ጥቅሞቹን ያጣል፣ ለከፋ አደጋም ይጋለጣል፡፡
ዛሬ በሀገራችን ለሚታየው የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆልና የዚህ ውጤት ለሆኑት ምግባረ ብልሹነት ራስ ወዳድነት፣ ለሀገር ፍቅር ስሜት ደንታ ቢስነት፣ ለሕዝብ መብትና ልዕልና ያለመጨነቅ፣ የጥሎ ማለፍ ዘይቤ ሰለባነትና ጎጠኝነት ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? ተዘውትሮ እንደሚነገረው፣ ከሁሉም በፊት የመልካም ወይም የመጥፎ ባህርያት መገኛ ሥፍራ ት/ቤቶች ናቸው፡፡ ት/ቤቶች የሚመሩበት አቅጣጫ ተነድፎ የሚላከው እንዲሁም ለተማሪዎች በሚሰጡት የትምህርት ገበታ የሚሰናዳው የአዕምሮ ምግብ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው በበላዮች ነው፡፡ ታዲያ ት/ቤቶች የሚወቀሱት በምን አግባብ ነው?
ለአንድ ነፍስ በውል ላላወቀ ህፃን በዓለም ላይ ብርቱ፣ አዋቂ፣ ረጅም፣ ወፍራም ወይም በጣም ተወዳጅ ሰው አባቱ ወይም እናቱ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጭ ስላለው ምንም አያውቅም፡፡ ቢያይና ቢሰማም ለእርሱ ትርጉም የላቸውም፡፡ ህፃናት ከቤተሰብ በላቀ ለመምህራንም ከዚህ የበለጠ ግምት ይሰጣሉ፡፡ መምህራን የሚያስተምሯቸው እውነት፣ የሚያሳዩት ድርጊት ተገቢ ነው ብለው ስለሚቀበሉ ለሰብዕናቸው አርአያ ያደርጓቸዋል፡፡ ት/ቤቶችና ቤተሰብ ለአንድ ህፃን መፃኢ ህይወት ቁልፍ ናቸው። የቤተሰብና የሕብረተሰብ ማንነት በራሱ የሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ነፀብራቅ እንደሆነ ይታመናል፡፡
አንድ ወላጅ ሕፃን ልጁ የታረመና የበቃ እንዲሆንለት በቤት ውስጥ ቢያንጸውም ወደ ት/ቤት ሲሄድ ይህ መልካም እሴት እዚያ ከሌለ፣ ሕፃኑ ውዥንብር ውስጥ እንደሚገባ አያጠራጥርም። የተሻለ በተባለ ት/ቤት የሚማር ሕፃን፣ ቤተሰቡ በጥራዝ ነጠቅ ብልሹ ልማድ የታጀለ ከሆነ፣ በት/ቤት የተገነባ አመለካከቱ እቤቱ ሲደርስ እየተናደበት  ግራ መጋባቱ አይቀሬ ነው፡፡ የሥነ ምግባር ልቀት፣ የትምህርት ጥራትና የወጣቶች መፃኢ ህይወት ኅብረተሰባዊ መሰረት ካልያዘ፣ ለብቻ ደሴት ፈጥሮ ከተፅዕኖ ለማምለጥ መሞከር የዋህነት ነው፡፡
ሀገራዊው የሶሺዬ-ኢኮኖሚክ ሥርዐት በጠንካራ ሕዝባዊ ባህል ላይ ከተገነባ የአመለካከት አንድነትና የዐላማ ውህደት ስለሚጋባ፣ የአንዱ ልጅ የሁሉም ልጅ ሆኖ ተኮትኩቶ የሚያድግበት መልካም ዕድል ሊሰፋ ይችላል፡፡ ይህ ምኞት አይደለም፡፡ የሀብት ወይም የሥልጣን መበላለጥ ሳይገድባቸው ሕፃናት ስለ ወገናቸው፤ ስለ ሀገራቸውም ሆነ ስለ ራሳቸው  ዕጣ ያልተነጣጠለ አቋም የሚይዙበትን ሥርዐት መፍጠር ከባድ ሥራ አይደለም፡፡ ይህ ቁም ነገር በፊውዶ ቡርዥዋው በቀዳማዊ ዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ሰርፆ፣ ስንቶች በሀገር ፍቅር ስሜት እየነደዱ፣ ከፊት የሚቀራቸውን ሳይሆን እስከደረሱበት ዕለት የቀሰሟትን ትምህርት እያሰቡ ወገንን ለማገልገል ወደ ሀገራቸው  እየተጣደፉ ይመለሱ እንደነበረ ማስታወሱ የጠንካራ ሕዝባዊ ባህልና ጠቀሜታን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ያ ድንቅ የሀገር ፍቅር ስሜት የመነጨው ከብዙ ግብዐት ነበር፡፡ የሥርዓተ ትምህርቱ ጥራትና ሁሉን አቀፍነት፣ የመምህራን የአሰለጣጠን ብቃት፣ የቤተሰብ ቁጥጥር፣ የህብረተሰቡ ሥነ ልቦናዊ ቅርርብ፣ የመንግሥት እገዛና ልዩ የማበረታቻ ሥርዐት፣ የሀይማኖት ተቋማት ሥነ-ምግባራዊና ሞራላዊ ድጋፍ፣ የሀገር ፍቅርንና መስዋዕትነትን የሚሰብኩ ገድሎች በተጠና መልክ መካተታቸው፣ የማኅበራዊ ሳይንሱ የትምህርት  ዘርፍ በጎላ መልኩ በሀገራቱ ታሪክ ላይ መመስረቱ… እና ሌሎች የኢትዮጵያዊነትን ዋጋ ከምንም በላይ አጉልተው የሚያሳዩ የዜግነት ግዴታዎች በሳይንሳዊ ዘዴ በመካተታቸው፣ ዘመን ያፈራው ትውልድ በትምህርት ጥራት ተደናቂ እንደነበረ መካድ አይቻልም፡፡ ደርግ ባሽመደመደው ሶሻሊስታዊ ሥርዐተ- ትምህርት ምን እንደተፈጠረ ያለፍንበት ስለሆነ ወቀሳ ከመተርተር ባለፈ ለአሁኑ ርዕስ ጥቅም ስለሌለው ማለፉ አይከፋም፡፡ (የመሠረተ ትምህርት እመርታ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡)
ዛሬ ቴክኖሎጂው መጥቆ ትምህርት በት/ቤት ብቻ ሳይሆን በሞባይሎችና ላብቶፖች ውስጥም ይገኛል፡፡ ዓለምን በኪስ ይዞ ስለ ዓለም ያለ ማወቅ አለመታደል እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ሣር ቅጠሉ አጋዥ በሆነበት ዘመን፣ ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎች ውሎ አድሮ ምጡቅ ሳይንቲስቶች የማይሆኑበት ምን ምክንያት አለ? “ቶክ ኤንድ ቾክ” ተብዬው ኋላቀር የማስተማር ዘዴ ቀርቶ፣ “ስፑን ፊዲንግ” የሚለው ስንኩል አካሄድ ተወግዶ፣ የመምህሩ ሚና ከአስተማሪነት ወደ አቅጣጫ ጠቋሚነት ብቻ ዝቅ ባለበት ሥልጡን ዘመን፣ ደካማ ተማሪ ከበዛ ችግሩ የተማሪው ሳይሆን የትምህርት ሥርዐቱና የህብረተሰቡ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ገና በለጋነታቸው ሊያውቁ ከሚገባቸው ጣራ በላይ እየተምዘገዘጉ፣ ሊታመን በማይችል የትምህርት ብቃትና ሙያ ክህሎት ውጤት ሲያስመዘግቡ በርካታ ወጣቶችን አይተን ተደንቀናል፡፡ በአንፃሩ ከዩኒቨርስቲዎች ቢመረቁም (ተመረቁ ነው የሚባለው?) ፊደል ካልቆጠረው ወገናችን ተርታ ሊመደቡ የሚዳዳቸው አያሌዎች እየተመለከትን ግራ ተጋብተናል፡፡ ችግሩ ምንድን ነው? ለዚህ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ሥመ ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ ፀበል በየአቅጣጫው እየረጨን “መጥተናል – ደርሰናል” እየተባባልን፣ ብንሸዋወድ ጉዳዩ ከፖለቲካ ጨዋታነት አልፎ የአካዳሚክ ጥራት ጥያቄን ይመልሳል ተብሎ የሚገመት አይመስለኝም። ከሺህ  ወንጋራ አንድ ጠንካራ እንዲሉ፣ ሥርዐተ-ትምህርቱን እያጠራን፣ ያሉንን ብናበቃቸው ከነዚሁ የሚፈልቁት ሊቃውንት ባላነሱን ነበር፡፡ ሰው አልባ መንኮራኩር እንጂ ሰው አልባ ህንፃ ምን ጥቅም አለው?
በት/ቤት ውስጥ ታላቁ ኃይል መምህሩ ነው ይባል የነበረው ቀርቶ፣ ወላጅና ተማሪው ተጣምረው ካልዘመቱበት አይረባም ተብሎ ቅንጅታዊ አመራር ተፈጥሯል፡፡ (መቆራኘቱ ባልከፋ) እንዲያ ከሆነ ደግሞ ለትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆል ተጠያቂዎቹ ሦስቱ አካላት ናቸው ማለት ነው? መንግስት በየትኛው አካል ሊወከል ነው? በት/ቤት በኩል?
ከላይ እንደጠቀስሁት ማንም ተቀነሰ ወይም ተጨመረ የሥርዐተ ትምህርት ጌታ፣ ፖሊሲው ነው፡፡ ሌላው ተከታይና አስፈፃሚ ከመሆን የዘለለ አቅም የለውም፡፡ በዘመነ ደርግ የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት የተናደው ምሁራኑ ከእነ ተማሪዎቻቸው ሙልጭ ብለው በኢ.ሕ.አ.ፓ መዋቅር ሲሰባሰቡ ነበር፡፡ ያኔ ት/ቤቶች ኦና በቀሩበት ወቅት ስማቸውን መጥቀስ ባያስፈልግም አንድ ባለስልጣን፤ ‹‹…. አስተማሪነት እኮ ማንም ገብቶ የሚሰራው ሞያ ነው..›› ብለው  የድጎማ ፕሮጀክትን ካስፋፉበት ጊዜ ጀምሮ፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹… የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ ወሰደሽ አሉ አስተማሪ…›› መባል ከነክብሩ ወድቆ ቀረ፡፡ የትውልዱ በሳል ወጣት (ክሬም የሚባለው) በጥይትም በስደትም ተወግዶ፣ ‹‹ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ›› እንደተባለው፣ ጊዜው በራሱ ሰዎች ዘልቆ፣ መንግስት ሄዶ መንግስት ተተካ፡፡
እያንዳንዱ መንግስት የየራሱን ፖሊሲ መትከሉ አይቀሬ ስለሆነ የዛሬው ሥርዐተ-ትምህርት ቅርፅና ይዘት በራሱ ጎዳና መጓዝ ከጀመረ ሩብ  ምዕተ አመት ሞላው፡፡ ሲጀምር ፖሊሲው ከባድ ተቃውሞ ቢያጋጥመውም የሚመለከታቸው አካላት መክረው አፅድቀውታል ተብሎ ሥር ተከለ፡፡ ከአመታት በኋላ በት/ቤቶች ግንባታና ማስፋፊያ ረገድ በርካታ ሥራ ተሰራ፣ ዩኒቨርስቲዎች ከ30 ያላነሱ ሆነዋል፤ የተማሪዎችና የመምህራን አሀዝ የትናየት አድጓል፣ የፈረቃ ትምህርት ቀርቷል፡፡ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ ስለማሽቆልቆሉ በየጊዜው እሮሮ ይሰማል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ተደራሽነትን በማስፋፋት የጥራቱን ጉዳይ ቀስ በቀስ ማስተካከል ይቻላል ባይ ነው፡፡ እስከዚያ በለብ ለብ የወጣ የህክምና ባለሞያ፣ ሰው ሊያበላሽ፣ ከከፋም ሊገድል ነው?
በምህንድስና የተመረቀ ሕንፃ ሊንድ ወይም ድልድይ ሊያፈርስ ነው? ሕግን  ጠንቅቆ ያላወቀ ዳኛ፣ አላግባብ የሞት ፍርድ ሊወስን ወይም ያንዱን ንብረት  ለሌላው ሊሰጥ ? የኢኮኖሚክስ ምሩቁ፣ በቅድሚያ የራሴን የኢኮኖሚ አቅም ሳልገነባ ምን በወጣኝና ነው ለአካባቢያዊ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የምጨነቀው እያለ ሊመነትፍ ነው? ከእነዚህ አብነታዊ የአሉታ ተግባራት የከፋ ብዙ ተሞክሮዎችን አላየንም አልሰማንም?
ሀገርና ሕዝብ ለመለማመጃ ላቦራቶሪነት ከታሰቡ፣ የዛሬው ፖሊሲ ተጠቃሚ ስላለመሆናችን ብንጠራጠር ያስከፋብናል? በየመ/ቤቱ፤ በየአገልግሎት ሰጭ ተቋማቱ፣ በየከተማ አስተዳደሩ የሚስተጋባው የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና አንዱ ምንጭ፣ ይሄ መሆኑን ልብ ብለነዋል? ከችሎታው ችሎታ፣ ከሥነ ምግባሩ ሥነ ምግባር የሌላቸውና ሞባይላቸውን እየነካኩ ከመቆነን በቀር ሰው የማይከብዳቸው ሰራተኞች ቁጥር የዋዛ ነው!? ለግሉ ዘርፍ በተፈቀደው  ዕድል ማንም መንገደኛ የቡና ቤት ንግዱ አላዋጣ ሲለው፤ ‹‹… ባክህ የሆኑ አስተማሪዎች  ቀጥረን ይሄን ቤት ኮሌጅ እናድርገው…›› እሚባባልበት ምዕራፍ ላይ አልደረስን ይሆን? ሌላው ህመም ያነሰን ይመስል በጠባቦች ወይም ትምክህተኞች ባለቤትነት የሚመሩ ሥመ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለመሰሎቻቸው ዲግሪና ዲፕሎማ የሚያስታቅፉበትን ሹክሹክታ አልሰማንም አላየንም ይሆን?
ከዚህ ባሻገር ለመምህርነት የሚመረጡ ሰዎች (በተለይ በከፍተኛ ተቋማት) በተቻለ መጠን በዚህ ሥርዓት ተቀርፀው የወጡ እንዲሆኑ የሚፈለግበት ምክንያት የሚያመራምር ባይሆንም አካሄዱ በዚህ ከቀጠለ አደጋውም አብሮ እንደሚያዘግም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እጅግ በሰለጠኑት ሀገራት ምሁራን ወደ ምርምር ሞያ የበለጠ ዘልቀው ለትውልድና ለዓለም የሚተርፍ ግኝት የሚያበረክቱት በልምድና በእድሜ ከገፉ በኋላ ስለሆነ ልዩ ክብካቤ ይደረግላቸዋል። እኛ ዘንድ የበሳል ሰው ፍቅርና ክብር “ፎቢያ” የሆነብን ይመስላል፡፡ ችግሩ መድኃኒት ያሻዋል – የጥልቅ ተሃድሶ መድኃኒት! የተማሪው እድሜ 18፣ የአስተማሪው እድሜ 22 ከሆነበት ጓዳ፣ ምን ውጤት ይጠበቃል?
ለወጣቱ በቂ የሥራ ዕድል መፍጠሩ በጎ ሆኖ፣ በዚህ ሽፋን በሳል ሊቃውንት ከትምህርቱ ዓለም ሲፈናጠሩ ማየት ጠያቂ ሳይሆን ተጠቂ ትውልድ መፍጠር እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ሥርዐተ-ትምህርቱ አካዳሚያዊ ጉዳዮችን ከነጠረ ፖለቲካ ጋር አጣምሮ ቃኝቶታል፡፡ ይህም በትምህርቱ ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ሲባል ቆይቷል፡፡ የታሪክ ትምህርትን ያህል ክቡር ዘርፍ የጎሪጥ ሲታይ ኖሮ ማምሻውን ለይቶለት ጥግ ላይ ተወሽቆ “እንተያያለን!” ይለናል። ለህፃናቱ በተዘጋጁ የመማሪያ መጽሐፍት የሚነበቡ አንዳንድ አዘናጊና አናቋሪ ድርሰቶች ምንጫቸው ጤነኛ አይደለም፡፡
የሀገሩን እውነተኛ ታሪክ ያላወቀ ወይም ተንሸዋሮ የተፃፈ ሲመገብ ያደገ ተማሪ፤ አንድ ቀን “ጠላት መጣ ተነስ” ሲባል፣ “በየት አቅጣጫ ነው የመጣው? በእኔ ክልል በኩል ካልሆነ ምን ቸገረኝ” ብሎ ሊያንገራግር እንደሚችል ያለመገመት የዋህነት እንዳልሆነ እንተንብይ! የጋራ ጉዳዮቻችንን በእውነትና በፍቅር እንድንቀበል የሚያንፅ ሥርዓተ-ትምህርት መኖሩ ማንንም አይጎዳም፡፡ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንጅ ክልል ተረካቢ ትውልድ እንዳይበቅል አርቀን እናስብ። በዚህ ረገድ አንድ አቋም የሚያስይዝ አንድ ቋንቋ ይኑረን፡፡ ይህ ብዝሀነታችንን የሚተናኮል ወይም የበላይነትና የበታችነት ምልክት ተደርጎ የሚታይ አይደለም፡፡ ክፉ ቀን ቢመጣ ለመግባባት ተስኖን ከቃላት ይልቅ በምልክት የምንጠቃቀስ እንዳንሆን ይሰውረን!  አንዳንዱ መምህር ከተማሪው ጋር ሺሻና ጫት ቤት የማይውልበት፣ በሥነ ምግባሩ አርአያ ሆኖ የሚከበርበት፣ በልጃገረድ ፍቅር ሳቢያ ከተማሪው ጋር የማይናቆርበት፣ በትምህርት አሰጣጡ “ግሩም” ተብሎ የሚደነቅበት፣ ስለ መነጣጠልና ጥላቻ ሳይሆን ስለ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚሰብክበት ቀን ህልም እንዳይሆንብን እንትጋ፡፡ ለአገር ለትውልድ የሚበጅ ሥርዓተ ትምህርት እንቅረጽ – ለማንም ብለን ሳይሆን ለራሳችን ብለን፡፡ የነገ ሰው ይበለን!

No comments:

Post a Comment