Monday, April 24, 2017

“የሀገሬ ሀገሯ የት ነው?” (ከዳግላስ ጴጥሮስ)

    


“መሃረቤን አያችሁ ወይ?…..አላየንም!” የሚለው የልጅነት ዘመኔን ጨዋታ ዜማውን ተውሼ፣ ዛሬም በጉልምስና ዘመኔ፤ “ሀገሬን አያችሁ ወይ?” እያልኩ ከብዙኃን ጋር የለሆሳስ ዜማ የማንጎራጉረው በግራ መጋባት ባሕር ውስጥ እንደሰመጥኩ ነው፡፡
የልጅነት ዘመናችን “የመሃረብ ድብብቆሽ ጨዋታ” የሚከወነው ዓይናችንን በእራፊ ጨርቅ አስረንና ክብ ሠርተን እየተሽከረከርን ሲሆን የጉልምስና ዘመኔ፤ “ሀገሬን አያችሁ ወይ?” የግራ መጋባት ብሔራዊ የብሶት እንጉርጉሮ የሚዜመው ደግሞ ህሊናዬና ህሊናችን  በይሉኝታ አልባ አዳፋ ግለኝነት ታብቶና ተጠፍሮ፣ እውነትን በአደባባይ አቁስለን እያፌዝንና በዙሪያዋ እየተሽከረከርን “……አላየንም! አልሰማንም!” እያልን በመጮህ ይመስለኛል፡፡
ሀገሬ ሀገር አልባ፣ ወገኔም ወገን አልባ እየመሰሉኝ የውስጥ ባዶነት አገርሽቶብኝ፣ ታማሚ ከሆንኩ ውሎ አድሯል፡፡ “የአየሩ ክብደት ሲሰነፍጠኝ”፣ የምድሪቱ ሞገስ ሲፈዝብኝ፣ ጥላዬ ተገፎ በጥርጣሬ እርምጃ እየተጓዝኩ፣ ያፈጠጠውን እውነታ ለመሸሽ “የሕልም ሩጫ” እንዲሉ፣  በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ እያበራ ገበያ ለገበያ እንደተንከራተተው እንደ ፈላስፋው ዲዮጋን፣  “የሀገሬ ሀገሯ ሀገሯ የት ነው” በማለት በሃሳብ እየናወዝኩ፣ በውስጤ የተንከራታችነት ስሜት ይሰማኛል፡፡
ስለ እውነት “የሀገሬ ሀገሯ የት ነው?” የጂኣግራፊ ካርታ ዘርግቶ በዚህን ያህል ኬክሮስ፣ በእንደዚያ ያህል ኬንትሮስ፣ ከምድር ሰቅ  ከፍ ብሎ ወይንም ዝቅ ብሎ፣ ከሠሃራ በታች ወዘተ. የሚለው የአራተኛ ክፍል ትምህርት እንዲደገምልኝ በፍፁም አልሻም፡፡
የኬክሮሱና የኬንትሮሱ የዲግሪ መላ ምት ፍቺ የሚኖረው፣ የሀገር ዳር ድንበር ጥርት ብሎ ሲከለል፣ ጎረቤቶቻችን የነቀሉት ወይንም ሊነቅሉት የነቀነቁት ብሔራዊ የሉዓላዊነታችን መገለጫ፣ የይዞታችን ችካል በአግባቡ ሲከበርና ፀንቶ ሲተከል ብቻ ነው፡፡
ረጋ ብዬ ውስጤን ሳዳምጠው፣ የሀገሬ ደመና የሕዝብን የብሶት እንባ አቁሮ በእጅጉ የከበደ ይመስለኛል፡፡ ያረገዘው ደመና ምን አይነት የአሲድ ዝናብ ያዘንብ ይሆን እያልኩም ልቤን የፍርሃት ምች ያንዘፈዝፈዋል፣ የዜማ ቅኝቱ ባይስተካከልም፤
“አይሽ አይሽና ይመጣል ዕንባዬ፣
አንቺም ወይ ዕድልሽ እኔም ወይ ዕጣዬ”
በማለት ሣግ በሚተናነቀው ጎርናና ድምጽ አንጎራጉር፣ አንጎራጉር ይለኛል – አለቦታው የሕዝብ ዜማ ተውሼ፡፡
“ሀገሬ ኢትዮጵያ” የሚለው የኩራት መመኪያ ከብዙዎቻችን አንደበት እየሟሸሸ በመዝገብ ቃላት ውስጥ ብቻ ተሸሽጎ፣ በነበር ሊያሸልብ አንድ ሃሙስ ብቻ የቀረው ይመስለኛል ወይንም በዘፈን አልበም ውስጥ ብቻ ታሽጎ ሊሻግት ዳር ዳር የሚል እየመሰለኝ እተክዛለሁ፡፡
“ሀገሬን ሀገሬን የምትል ወፍ አለች፣
እኔን እኔን መስላ ታሳዝነኛለች፡፡”
የሚለው የራሮት እንጉርጉሮም የዕለት መተከዣዬ ሆኗል፡፡ ብሶቱ ሲያይልም “የምን ሀገር…..” ወደሚል ክፉ ቅኝት እንዳይለወጥም ራሴን በራሴ ፈርቼዋለሁ፡፡ ድብልቅልቅ ስሜት ይሏል ይሄ ነው፡፡
“ሀገር ማለት ሰው ነው!” የሚለው የሲቪክስ ትምህር አስኳል ሃሳብና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቲያትረኞች የሰበኩልን ዘመንኛ ፍልስፍናም “አይቅርብን” ለማለት የተዜመ ወቅት አድማቂ መዝሙር እየመሠለኝ በውስጤ ጥርጥር ከገባ ሰነባብቷል፡፡
“ሀገር ማለት ሰው ከሆነ” ሰውን ያውም የራሳችንን ወገን፣ ከእምዬ ልጅ ጋር እርስ በእርስ እንድንጠራጠር፣ አዚም የላከብን ወይንም ክፋት የዘራብን ማን ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ቢያንስ እኔ መልስ አላገኘሁለትም፡፡ ጠይቄም በአግባቡ ሊያስረዳኝ የሚችል ሰው አላገኘሁም፡፡ እውን መልሱ ለአንተ ጠፍቶህ ነው? ብለው ለሚጠይቁኝ ሞጋቾችም መልስ የለኝም፡፡
በመሃላ የተበረከተልን ሕገ መንግሥት እንደደነገገልን፣ በሀገሬ ምድር፤ “እውን ዜጎች ሁሉ እኩል ናቸው?” ማን ይሙት በሀገሬ ምድር ዛሬ፣ አሁን ከክልል ክልል፣ ከወረዳ ወረዳ፣ ከቀበሌ ቀበሌ እየተዘዋወርኩ “ኢትዮጵያ ሀገሬ” እያልኩ ለመዘመር፣ እንደ ፈቃዴ “በምድሬ ላይ” በወርዷና በስፋቷ ልክ እየተንቀሳቀስኩ በላቤና በወዜ እየደከምኩ የዕለት እንጀራዬን ልበላ እችላለሁ፡፡ ሙያዬን ብቻ ዋቢ እያቆምኩስ በነፃነት ሠርቼ መግባት እችላለሁ፡፡ የትናንቱ ዘመነ ምንትስ “በይለፍ” ደብዳቤ በሀገሬ ውስጥ እንድንቀሳቀስ በልጓም የሸበበኝ ወቅት እንኳ እንዲህ እንዳስብ አላደረገኝም፡፡
ትንሽ የሃሳቤን ገመድ ሳብ ላድርገውና፤ “በሕግ አምላክ” እያልኩስ ርትዕ እንዲሰፍን በሀገሬ የትኛውም ክልል፣ በቋንቋዬና “በኢትዮጵያዊነቴ” ተመክቼና ሕገ መንግሥቱን ከፊቴ አስቀድሜ፣ ሕጉን በሕግ መሞገት እችላለሁ? ቸር አምላክ ጥብቅና ቆሞልኝ ወይንም ለሕሊናቸው ያደሩ መልካም ፍትህ አስከባሪዎች ፈርደውልኝስ ቢሆን በሹም ቃል፣ በሥልጣን ድምፀት ፍርዴ አይገለበጥብኝም? “ማን ነክቶህ! ምን ችግር አለና!” ባይ ተሟጋች ካለ እሰየው፣ ምን ገዶኝ “ይሁንልኝ” እልል በቅምጤ እያልኩ እንደ ልጅነቴ በደስታ እያጨበጨብኩ እቦርቃለሁ፡፡ ይህ ስጋት የእኔ ሃሳብ ብቻ የመሰለው ካለ፣ ሕዝቡን በነቂስ ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ይልቅስ የልጅነቴን ትዝታ ስጎረጉር አንድ ገጠመኝ ትዝ ብሎኝ ፈገግ አሰኘኝ፡፡ አበባ ዜማን በማስታወስ። በሣቂታዋ ኮልፌ ሠፈር ተወልደው ዕትብታቸው የተቀበረ፣ ወይንም በጨቅላ ዕድሜያቸው የኮልፌን ቀይ አፈር እያቦነኑ ያደጉ ዘመነ አቻዎቼ ዝነኛውን አበባ ዜማን ይረሷቸው ይሆን ብዬ በፍፁም አልጠራጠርም፡፡
አበባ ዜማ የእቴጌ መነን ጫካ ባለ አደራ ጠባቂ ነበሩ፡፡ ዛሬ ኮልፌ አስራ ስምንት ማዞሪያ የሚባለው አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ ታሪኩ የተፈፀመበትን ትክክለኛ ቦታ ለማረጋገጥ ለሚፈልጉ ደግሞ ዕውቀቴ ወገኔ ት/ቤት ያለበትን ግቢ ሄደው ቢጎበኙ ቀጥዬ የምተርከው ታሪክ ዛሬም ድረስ አሻራው እንዳልጠፋ መገንዘብ ይችላሉ፡፡
አበባ ዜማ ከቆቅ የነቁ፣ ከሚዳቆ የፈጠኑ፣ ቆፍጣና የደኑ ጠባቂ ነበሩ፡፡ በተለይ በተለይ የኮክ ደኑን የሚጠብቁት በልዩ ጥንቃቄና ንቃት ነበር። ለእኔና ለቢጢዎቼ ደግሞ ቆቅነታቸውንም ሆነ ሚዳቆነታቸውን ለመፈታተን ጥበቡ አልጠፋንም። በልዩ ልዩ ፈጣን የልጅነት ዘዴ አበባ ዜማን እያታለልን፣ የኮክ ደኑን ኬላ ሰብረን የምንገባው የኮክ ፍሬዎችን ለመስረቅ ብቻ ሳይሆን በኮኩ ደን ውስጥ የምትንጎማለለውን አንዳች  የምታህል ዕድሜ ጠገብ ዔሊ ቀርበን ለማየት ጭምር ነበር፡፡
ከዛፍ ላይ ያረገፍነውን የኮክ ፍሬ እየተገላመጥን በመግመጥ፣ በዚያች አማላይ ዔሊ ዙሪያ ተሰባስበን የምንከውነውን የልጅነት ትርዒትና የምንፈላሰፍበትን ርዕሰ ጉዳይ አስገራሚነት ሳስታውስ ፈገግ ማለቴ አይቀርም፡፡
ከመካከላችን አንዱ ወጠጤ ጓደኛችን፣ ዔሊዋን በጀርባዋ እየገለበጣት ተፈጥሯዊ ፆታዋን እንድንለይ፤ “ይህ/ይህቺ ዔሊ ወንድ ነው፣ ሴት ነች?” እያለ በጥያቄ ያጣድፈን ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ዔሊ ባየሁ ቁጥር ይህ የፆታ ጥያቄ በአእምሮዬ እየመጣ መሰንቀሩ አልቀረም፡፡
ሌላው ቃንቄ ጓደኛችን ደግሞ፤ “አሁን ይህ/ቺ ዔሊ ዕድሜው/ዋ ስንት ይሆናል?” እያለ ያመራምረናል፡፡ ወላጆቻችን የዔሊ ዕድሜ ረጅም ነው ሲሉ ስለምንሰማም፣ አንዳንዶቻችን ፈጥነን የዔሊዋን ዕድሜ በሺህ ዓመት እንገምታለን፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በመቶ ዓመት እድሜ ይከራከራሉ። ምክንያታዊ ነን የሚሉ ሚጢጢዎቹ ጓደኞቻችን ደግሞ ሃያ ዓመት፣ ሃያ አምስት ዓመት እየተባባልን፣ የአበባ ዜማን ዔሊ ዕድሜ ከሺህ ዓመታት ወደ ሃያ ዓመታት ቁልቁል በማምዘግዘግ እንከራከር ነበር፡፡ ከአባባ ዜማ የዱላ ቅዝምዝም ራሳችንን እየጠበቅን፡፡
በዛሬው የጉልምስና እድሜዬ ትልቋን ሀገሬን፣ ውድና የከበረ ታሪክ ያላትን “ይህቺን ጉደኛ ሀገሬን” እንደ አበባ ዜማ ዔሊ፣ ገናና ታሪኳንና በተከበሩ ልጆቿ ደምና አጥንት የተከለለውን የታሪኳን ኬላ እንዳሻን ጥሰን እያለፍንና በአልባሌ ሁኔታ ገበናዋን እያራቆትን፣ በዕድሜዋ ርዝመት ላይ እንከራከራለን። ግማሹ ሀገሬን በሺህ ዓመታት ሲያገዝፋት፣ አወቅሁ ባዩ በመቶ ዓመት ሲያሰላት፣ የባሰበት ደፋሩ የሃያ አምስት ዓመት አድሜ እየቆረጠላት፣ “አዲሲቷ ኢትዮጵያ” በማለት የጨቅላ ጥብቆ ሲያለብሳትና ሲያሟሟት “እውን የሀገሬ ታሪክ ይህ ነው? የሀገሬ ሀገሯስ የት ነው” እያልኩ በውስጤ እከስላለሁ። ምሬት ባጠለሸው ህሊናም ራሴን በራሴ ተጠይፌ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ፡፡ የዘመኔን ምሁራን “ዝም አይነቅዝም” ፍልስፍናም በእጅጉ ውስጤን ሲያነቅዘኝ ይሰማኛል፡፡
እጅግ በርካታ ያፈጠጠ ዕውነት ሲደፈጠጥ፣ ፀሐይ የሞቀው ሀገራዊ ጉዳይ ሲድበሰበስ ሳስተውልም፤ ”እውነትን ስቀሏት” ያለው ገጣሚ ትዝብት እውን ሆኖ ይሆንን እያልኩ በሙያ ባልደረባዬ “ጥቁር ምላስ” (ጥቁር ብዕር ማለትም ይቻላል) ንግር እወሰዳለሁ፡፡
ሀገሬ ሀገር አልባ ሆና ተፋራጅ በማጣት ከግዛቷ ተነቅላ፣ በአውሎ ነፋስ የምትንገላታ እየመሰለኝም “ወይ ነዶ” እያልኩ እብሰለሰላለሁ፡፡ ብሶቴን ላጋራው ጠጋ የምለውም ብዙ ሰው እንደኔው ጨሶና ከስሎ ኖሮ፣ በወላፈን ትንፋሹ ግለት መልሶ ያግለኛል፡፡
ማንም ዜጋ በቋንቋው፣ በባህሉና በማንነቱ መኩራቱና መመካቱ ማንም ሊሽረውና ሊገሰው የማይችለው ሰብዓዊና ተፈጥሮአዊ መብቱ እንደሆነ ደመ ነፍሴ ይነግረኛል፤ ሕገ መንግሥቱም እውነት ነው ብሎ መስክሮልኛል፡፡ ይህንን እውነታ መካድ በፈጣሪም ዘንድ ሆነ በትልቁ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሠረት፣ ይግባኝ የማይባልበት ፍርድ እንደሚያስፈርድ የተቆረጠ ጉዳይ ነው፡፡ እኔውም ብሆን የዜግነት ስልጣኔን ተመክቼ፣ የአንድን ዜጋ ሰብአዊ ክብር መዳፈር በፍፁም አግባብ እንዳይደለ ማመን ብቻ ሳይሆን የአቅሜን ያህል ለማስከበርም ወደ ኋላ አላፈገፍግም፡፡ ለወገኔ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ክብር መጠበቅም አጥብቄ እሟገታለሁ፡፡ የብዙ ወገኖቼ እምነትም ይኼው ይመስለኛል፡፡ ፖለቲካው እንደ ድርቆሽ ያጠነዛውን ዲሞክራሲ ሳይሆን የምሩንና ለምለሙን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በእጅጉ እናፍቃለሁ፡፡
ይህንን የተከበረ እውነታ በብርሃን ፍጥነት ማን፣ መቼ እንደሸረሸረው ቆም ብዬ ሳስብ በእጅጉ ግራ እጋባለሁ፡፡ የወቅታዊው ግራ መጋባቴ መንስዔ እነሆ፡፡ አንድ ወገኔ የሀገር ዜጋ በመንገድ ላይም ይሁን በትራንስፖርት ውስጥ በቋንቋው እያወራና እየተጨዋወተ ሲሄድ ወይንም የስልክ ግንኙነት ሲያደርግ ማንነቱን ለማጣራት ዞር ዞር እያሉ መጎሸማመጡ ከተጀማመረ ውሎ አድሯል፡፡ ለምን፣ እንዴት፣ በምን ምክንያት፣ ማን ጀምሮት ወዘተ. ይህ ጉዳይ እያደገ ከሄደ ምን ላይ ያሳርፈን ይሆን እያልኩ የመላ ምቱን ፍፃሜ ሳስበው፣ ልቤን ፍርሃት ፍርሃት እያለው ማማተብ እጀምራለሁ፡፡ “ምን እንዳይመጣ ከቶስ ምን እንዳይፈጠር ሰጋህ!!!” ባይ አፅናኝ ጀግና ካለም፣ እንደ ልብህ ሳይሆን እንዳፍህ ይሁንልን እያልኩ፣ በአደፋፋሪነቱ እመርቀዋለሁ፡፡
ወገኔን እንደ መጤ ዜጋ በማንነቱ ላይ መጠራጠርና መፍረድ በሕዝቦች ሥር የሰደደ የደም ትስስር ላይ ክፉ ካንሰር ሊያሰራጭ የሚችል ደዌ እንዳይሆንም ስጋቴ የገዘፈ ነው፡፡ በአጭሩ ካልተፈወሰ በስተቀር፡፡
በሁሉን ቻይ ፈጣሪ መልካም ፈቃድ፣ ከተወላጁ ዕውቅናና ፍላጎት ውጭ ተፈጥሮ በወደደችው መልኩ ብቻ የተፈጠረውና የተገነባው የስብዕና ማንነታችን ዛሬ ድንበር እየተከለለለት የየትኛው ብሔርና ቋንቋ ውልድ ነህ እየተባለ በዋዛም በምርም ሲነገርና ሲደሰኮር ስሰማ፣ “ዕድሜ ደጉ ለዚህ አበቃን” እያልኩ በመተከዝ፣ “ዕውን ሀገሬ ራሷ ሀገር አላት?” እያልኩ ለባተሌዋ ሀገሬ ዕንባዬን ወደ ውስጥ አፈሳለሁ፡፡ ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት ማንኛው መምህሬ ነበሩ ይህንን ግጥማቸውን ያነበቡልን፡፡ የእድሜ አቻዎቼ አስታውሱኝ፡፡
ግጥሙንም ስላወላከፍኩት አርሙልኝ፤ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ባሟላኋቸው ስንኞችም ይቅር በሉኝ። የግጥሙ ባለቤት ዶ/ር . . . እባክዎን ሙሉውን ግጥም ያስነብቡን፤
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት የልጅ ሞት ያጠቃት፤
ከል ያስለበሳት፣ [ዕንባ ያሰከራት]፣
ለካ እርሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡
“ተሸክሜው የምዞረውን መታወቂያዬን እየረገምሁ” እንደው ለጉዱ እኔው ራሴ የተሸመንኩበት የማንነቴ ሸማ ቀለሙ ምን ይመስል ይሆን ብዬ ጉጉት አድሮብኝ፣ “ወጥቶ አደሩ” አባቴ ከእጁ ከማይለያት የውሎ መመዝገቢያ ደብተሩ ላይ በልጅነቴ የገለበጥኩትን ማስታወሻ አቧራውን እያራገፍኩ ያነበብኩት፣ እያቆረዘዘ ካስቸገረኝ እንባዬ ጋር እየታገልሁ ነበር፡፡ የወገኔ ሁሉ ታሪክ ይህንን እንደሚመስል እስከ መሃላ ድረስም ቢሆን ገፍቼ እከራከራለሁ፡፡ እነሆ የተፃፈልኝን አንብቡልኝና ፍርዱን እናንተው ስጡ፡፡ የተሸመንኩበት ቀለሙ ማማሩን፡፡
ከሰሜን ሸዋ አፈር በመፈጠር ማህፀኗን ያዋሰችኝ እናቴና የአብራኩ ክፋይ ያደረገኝ አባቴ፤ እኔና እህቶቼን አፍርተው በሚሊዮኖች የሕዝብ ቁጥር ላይ ስለደመሩን አመሰግናለሁ፡፡ እኔ እያየሁ ያለሁትን የዘመኔን ጉድ ሳያዩ በማለፋቸውም ዕድለኞች መሆናቸው ይሰማኛል፡፡ ልቀጥል ታሪኩን. .  .
ወለዬዋ የአባቴ እናት ሴት አያቴና ይፋቴው የአባቴ አባት ወንድ አያቴ ወልደው ከከበዱ በኋላ እህል ውሃቸው በማለቁ ተለያይተው፣ እማማ ትልቋ ወደ ዛሬው የኦሮሚያ ክልል፣ ትልቁ አባባ ወደ ሐረርጌ በመጓዝ፣ ለሁለቱም ዕድል ቋንቷቸው ኖሮ ኑሯቸው ስለሰመረላቸው እማማም ከሁለት ሌሎች የኦሮሞ አባቶች፣ አባባም ከሱማሌና ከሐረሪ ክልሎች ከተገኙ እናቶች በልጆችና በሀብት በረከት ተጥለቀለቁ፡፡ እኔም በርካታ የኦሮሞ መልካም አጎቶችና አክስቶች፣ አልፎም ተርፎ በበርካታ የልጅ ልጆች ቤተሰቡ የተባረከ ሲሆን፣  ከሱማሌና ከሐረሪ ተወላጆች ደጋግ አክስቶችና አጎቶችም ለማግኘት ታድያለሁ፡፡
ወላጅ አባቴም በወታደራዊ የሥራ ባህሪው ረጅሙን ዘመን በሱማሌ ክልል ስላሳለፈ በቋንቋውም ሆነ በባህሉ፤ “ከእኔ ወዲያ ሱማሌ ለአሣር!” እያለ እስከ መፎከር ደረሰ፡፡ ሴት ልጅ ስትወለድለትም በሐረር ወርቅ የሰየማት ሲሆን እርሷም በተራዋ ከኦሮሞ ባለቤቷ በሰባት ልጆችና በበርካታ የልጅ ልጆች ተባርካለች፡፡ ሌላዋ ታላቅ እህት፣ አንድ የጋሞ ጀግና አግብታ፣ ከወደ ደቡብም የትስስሩ ጅረት ፈሶ ነበር፡፡ ይህ የጋሞ መልካም ሰው ገና በማለዳው ቀና የሕይወት መስመሬን እንዳሰምር ትልቁ ባለድርሻ ስለነበር፣ እነሆ ለክብሩ ባርኔጣዬን አንስቼ ዕድሜ ይስጥልኝ እላለሁ፡፡
የወላጅ አባቴ ወታደራዊ ግዳጅ ሕይወቱን መስዋዕትነት ካስከፈለው በኋላም ምስኪኗ እናታችን የባሏን ሰባት ካወጣች በኋላ ከአንድ የትግራይ ተወላጅ ጋር እህልና ውሃ አገናኝቷቸው፣ አንድ ደግና ርህሩህ እህት አፍታርታልናለች፡፡ ከሌላ የኦሮሞ ባልም ተወዳጅ እህት ወልዳልናለች፡፡ እኔም ብሆን ከኦሮሞ አባት ከተገኘችው ውብና ሽቁጥቁጥ ባለቤቴ ጋር በደስታ እየኖርኩ አይደል፡፡
እራሴን አብነት አድርጌ እንዳጋለጥሁት ይህን መሰል ቅይጥነት፣ ውህደትና ትሥሥር የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የጋራ መገለጫ በሆነበት ሀገሬ፤ ዛሬ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ማኀበረሰባዊ የመፈራራትና እርስ በእርስ የመጠራጠር ተስቦ እንዴት ሊስፋፋና መተማመን ሊነሳን እንደቻለ ማሰቡ ያሳምማል። የሚለበልበው የፖለቲካ ትኩሳትም ያሳስበኛል፡፡ ከየትኛው ብሔርና የየትኛው ቋንቋ ተናጋሪ ነህ ብሎ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ልዩነቱን ለማስፋት መሞከር፣ ሲኖሩት ብቻ ሳይሆን ሲያስቡትም ይኮሰኩሳል፡፡ ለምሳሌ የእኔን መሰል ታሪክ ያላቸውን ወገኖቼን፣ የዘር ደማችሁን አጥልላችሁ አሳዩን ቢባል፣ የትኛው  ወንፊት አንጥሮ ያወጣዋል፡፡
ቶሎ ነቅተን ትስስራችንና አብሮነታችንን ማጥበቅ ካልቻልን በስተቀር የልዩነቱ ስፋት እርስ በእርስ ሊያሻግረን የማይችል ገደል ፈጥሮ ማዶ ለማዶ እንዳያስቀረንም አጥብቀን ልንሠጋ ይገባል፡፡
ለዘመናት “ዋይ ዋይ” እያልን ከጥላሁን ገሠሠ ጋር የዘመርንለት ርሃብስ ቢሆን የወደደነው መስሎት እንደ አልቅት ተጣብቆንና አዳፋ  ቡቱቱውን ከደጃፋችን ላይ አንጥፎ ቤተኛ ከሆነ ዘመናት አሸብቷል፡፡ ዛሬም ቅኝቱ ይለያይ እንጂ ለርሃብ እየዘመርንለት ነው፡፡ አዬ ጉድ! ጉዳያችንና ጉዳችን ብዙ ነው፡፡ የጋዜጣው አርብ ደግሞ ጠባብ፡፡ ባይሆን ለዳግም ቅኝት ቀጠሮ ቋጥረን እየተሰነባበትን፣ እስከዚያው ድረስ “የሀገራችን ሀገር” የት እንደሆነ በውይይትና በምክክር ኮምፓስ አቅጣጫውን በደቦ እንፈልግ፡፡ ሰላም!!

No comments:

Post a Comment