Thursday, April 27, 2017

የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን: የፕሮጀክት አጋሮቹን ለምክክር ሊጠራ ነው


ሐራ ዘተዋሕዶ
  • የማኅበረሰብ ተጠያቂነት አጋርነት ማሕቀፍ ትግበራ፣ ከአጋሮች ጋራ ግንኙነቱን አጠናክሮታል
  • በዘላቂ ልማት እና የአገልግሎት ጥራት፣ የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ በተከታታይ ተሸላሚ ኾኗል
  • የበጎ አድራጎት ሕጉ፣ በኮሚሽኑ የውጭ ለጋሽ ድርጅቶች ርዳታ አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል
  • የገቢ ምንጭ መምሪያ በማደራጀት፣ የገንዘብ አቅሙን በሀገር ሀብት ለማጠናከር እየሠራ ይገኛል
  • ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆ ራስን ለመቻል ይረዳናል ያልነውን ጥናት አዘጋጅተናል”/ሊቀ ጳጳሱ/
**
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ
*
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ ከውጭ የርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ የሚያስችለው ሕግና ደንብ ማዘጋጀቱን የገለጸ ሲኾን፤ ከፕሮጀክት አጋሮቹ ጋራ በቀጣይ ስለሚኖረው የሥራ ግንኙነት ለመምከር ማቀዱን አስታወቀ፡፡
የዓለም አቀፍ ለጋሾች ርዳታ፣ ለተወሰነ የሽግግር ጊዜ ከመርዳቱ በቀር በዘላቂነት የሚጠቅም እንዳልኾነ ለሳምንታዊው ሰንደቅ ጋዜጣ የተናገሩት የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ለልማትና ተራድኦ የሚውል ሀብት ከሀገር ውስጥ ለማሰባሰብ የሚያስችል ሕግና ደንብ በኮሚሽኑ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
“ጥናቱ ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆን ራሳችን እንድንችል የሚረዳን ይኾናል፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ሌሎች ምሁራንን በማሳተፍ መዘጋጀቱንና ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ሲጸድቅ በሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡
ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ ለጋሾች ገንዘብ መቀበል እንደማይቻል የሚከለክለው (የ10 በ90) የበጎ አድራጎት ሕጉ፣ የሀገሪቱንና የረጂዎችን ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ባለመኾኑ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንዳለ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ተናግረዋል፡፡
ይህ 10 በ90(10 ከመቶ በላይ ከውጭ ለጋሾች ገንዘብ መቀበል አይቻልም) የሚለው የውጭ ለጋሽ ድርጅቶች ብዙም አልተቀበሉትም። እርሱ ነው ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው። ሕጉ፥ የሀገሪቱንና የረጂዎችን ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም።
ያም ኾኖ፣ ከዓለም የኢኮኖሚ ቀውስና ረጂዎች በዓለም ዙሪያ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ችግሮች በመብዛታቸው የውጭ ርዳታ እየቀነሰ በመምጣቱ፣ ኮሚሽኑ ከውጭ ከሚያገኘው የርዳታ ድጋፍ በተጨማሪ የገቢ አቅሙን የሚያጠናክርበት የተለያዩ ዕቅዶች ማዘጋጀቱን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጠቅሰዋል፤ የኮሚሽኑ የገቢ ምንጭ መምሪያ መደራጀቱንና የተጀመሩ ሥራዎችም እንዳሉ ዘርዝረዋል፡፡
የልማትና ክርስቲያናዊ ኮሚሽኑ፣ በአኹኑ ወቅት ከለጋሽ አካላት ጋራ ስላለውና በቀጣይ ስለሚኖረው ግንኙነት ሰንደቅ የጠየቃቸው ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ፣ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት በመኾኑ በየጊዜው ከለጋሽ ድርጅቶች አዎንታዊ ምላሽ እያገኘ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በተገበራቸውና ዘላቂነታቸው በተረጋገጡ የልማት ተቋማትና ለኅብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት፣ በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት(CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ፣ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በቀዳሚነት አሸናፊ ኾኖ ለመሸለም መብቃቱን በዐብይ አስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡

  • በተለያዩ ክልሎች 27 የማኅበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶች፤
  • ከ10ሺሕ በላይ አሳዳጊ አልባ ሕፃናት ክብካቤ፤
  • በ18 የመጠለያ ካምፖች ከ810ሺሕ በላይ ስደተኞች፤

በተለይ ኮሚሽኑ፣ የማኅበረሰብ ተጠያቂነት አጋርነት(Humanitarian Accountability Partnership) ማሕቀፍ አዘጋጅቶና አጽድቆ በመተግበሩና የሕፃናት ፖሊሲን ቀርፆና አጽድቆ በሥራ ላይ በማዋሉ ከአጋር ድርጅቶች ጋራ ያለው ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሯል።
ከኹሉንም የፕሮጀክት አጋሮች ጋራ ኮሚሽኑ ባለው የጋራ አጀንዳና በቀጣይ ስለሚኖረው የሥራ ግንኙነት በተመለከተ ከተወካዮቻቸው ጋራ በቅርቡ ለመወያየት ዕቅድ መያዙን በምላሻቸው የጠቆሙት ብፁዕነታቸው፣ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
“ዋናው ጉዳይ የታለመለትን ፕሮጀክት በጥራትና ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ በጽናት ማከናወን ነው፤” ያሉት ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ አያይዘው እንደገለጹት፥ የክልል፣ የዞንና የወረዳ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችም፣ ኮሚሽኑ የተገበራቸውን የልማት ሥራዎችና በተጠቃሚው ኅብረተሰብ ላይ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ በመመልከት ምስጋናና ዕውቅና እየቸሩት ይገኛሉ፤ ብለዋል፡፡
ከዛሬ 46 ዓመታት በፊት የተመሠረተውና በእንቅስቃሴውም አብዛኛውን የኢትዮጵያ አካባቢዎች(ክልሎች) በመሸፈን ላቅ ያለ ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የልማትና ክርስቲያናዊ ኮሚሽን፣ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጄንሲ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት፣ በኢትዮጵያዊ ነዋሪዎች በጐ አድራጐት ድርጅትነት በምዝገባ ቁጥር 1560 ተመዝግቦ የማኅበራዊና የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ሰንደቅ ጋዜጣ፣ በትላንት፣ ሚያዝያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. እትሙ ያወጣውና ከኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋራ ያደረገው ቃለ ምልልስ ሙሉ ይዘት የሚከተለው ነው፡፡

በሀገር ውስጥ የሀብት ማሰብሳብ ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ እየሠራ ያለ ተቋም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ ከዛሬ 46 ዓመታት በፊት የተመሠረተና በእንቅስቃሴውም አብዛኛውን የኢትዮጵያ አካባቢዎች(ክልሎች) በመሸፈን ላቅ ያለ ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ነው።
ኮሚሽኑ ከሚያደርጋቸው መጠነ ሰፊ የልማትና የርዳታ ሥራዎች ጋራ በተያያዘ፣ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት (CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ፣ በአገራችን ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል በቀዳሚ አርኣያነት አሸናፊ ኾኖ ለመሸለም በቅቷል። በዚኽና መሰል ጉዳዮች ከኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋራ ባልደረባችን ፍሬው አበበ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሮ ቀርቧል።

ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያለውን አደረጃጀት ቢገልጹልን?
ብፁዕነታቸው፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ በሕግ ክፍል ማስታወቂያ 415/1964 በነጋሪት ጋዜጣ፣ ከታኅሣሥ 26 ቀን 1964 ዓ.ም. ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ራሱን የቻለ መሥሪያ ቤት በመኾን ተቋቁሞ የሚሠራ ሲኾን፤ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ መንግሥት፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጄንሲ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት፣ በኢትዮጵያዊ ነዋሪዎች በጐ አድራጐት ድርጅትነት በምዝገባ ቁጥር 1560 ተመዝግቦ የማኅበራዊና የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ የበጐ አድራጐት ድርጅት ነው። ድርጅቱ፥ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ቦርድና የአመራር አባላት ያሉት ኮሚሽን ነው።
በመኾኑም የልማት ኮሚሽን፣ ቤተ ክርስቲያን፣ የወገን ደራሽነቷን ለማረጋገጥ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የነፍስ አድን ርዳታ በማድረግ ብሎም መልሶ በማቋቋምና በልማት በማገዝ ፈርጀ ብዙ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶአል፤ አኹንም እየሰጠ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- በአኹኑ ሰዓት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዋና ትኩረቶች ምንድን ናቸው?
ብፁዕነታቸው፡- የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፥ የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች የሚስፋፉበትን መንገድ መቀየስ፤ በገጠር የሚኖሩ ዜጐች የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ የሚኾኑበትን መንገድ መቀየስና መሥራት፤ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተቀናጀና የተጠናከረ ሥራ መሥራት፤ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የበኩሉን የሥራ ድርሻ ማበርከት፤ በእናቶችና ሕፃናት ሥርዓተ ምግብ ላይ ትርጉም ባለው መንገድ መሳተፍ፤ ስደተኞችን የመቀበልና ማስተናገድ ሥራን አጠናክሮ መቀጠል፤ ችግር ፈቺ የኾኑ የልማት ሥራዎችን በማጥናትና በፕሮጀክት በማካተት ሥራ ዐጥ ወጣቶችንና ችግረኛ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮአቸው የተሻሻለ እንዲኾን ማገዝና የመሳሰሉት ናቸው።
ሰንደቅ፡- በልማት የተለያዩ ዘርፎች በኮሚሽኑ የተከናወኑ ተግባራትና ተጨባጭ ውጤቶች ምን ምንድን ናቸው?
ብፁዕነታቸው፡- ኮሚሽኑ ከበርካታ ሀገር አቀፍና የውጭ በጎ አድራጐት ድርጅቶች ጋራ አጋርነት በመፍጠር፣ በአገሪቷ የተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አያሌ ማኅበረሰቦች ካሉባቸው ችግሮች እንዲላቀቁ በማድረግ ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን በመኾን አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል።
ይኸውም በበርካታ ወረዳዎች የገጠር ልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር፥ በመስኖ፣ በንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን በማዝለቅ፣ በገቢ ምንጭ ተግባራት፣ በአቅም ግንባታ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ በማኅበረሰብ የአደጋ ጊዜ መቋቋሚያና መጠባበቂያ ፈንድ ማኅበራትን በመመሥረትና በማጠናከር፣ በሥርዓተ ምግብ አጠቃቀም፣ በሥነ ተዋልዶ ጤና፣ በፀረ-ኤች.አይ.ቪና በመሳሰሉት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።
በሌላ በኩል፣ በኮሚሽኑ ሥር ባለው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች መምሪያ አማካይነት፣ ከጐረቤት ሀገራት ተሰደው የሚመጡትንና ከስደት ተመላሾችን፣ ኮሚሽኑ ባቋቋመው የስደተኛ ካምፖች በመቀበል አስፈላጊውን ሰብአዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ አድርጓል። ለዚህም፣ ልማት ኮሚሽኑ በተገበራቸው ዘላቂነታቸው በተረጋገጡ የልማት ተቋማትና ለኅብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት፣ በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት(CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ፣ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በቀዳሚነት አሸናፊ ኾኖ ለመሸለም መብቃቱ በዐብይ አስረጅነት ሊጠቀስ ይችላል።
በተጨማሪም በመንግሥት የክልል፣ የዞንና የወረዳ መሥሪያ ቤቶች የልማት ኮሚሽናችን በተገበራቸው የልማት ሥራዎች፣ በተጠቃሚው ኅብረተሰብ ላይ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ በመመልከት ምስጋናና ዕውቅና እየቸሩን ይገኛሉ።
ሰንደቅ፡- በክርስቲያናዊ ተራድኦ ረገድ፣ በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥና ከድርቅ ጋራ በተያያዙ የተፈጥሮ አደጋዎች ኮሚሽኑ የፈጸማቸውን ጉዳዮች ቢዘረዝሩልን?
ብፁዕነታቸው፡- ልማት ኮሚሽኑ፣ በአኹኑ ሰዓት ለዓለም አስጊ ለኾነው የአየር ለውጥ ችግር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፣ የአየር ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን በፕሮጀክት ጥናቶቹ በማካተት ተግባር ላይ እያዋለ ነው። ይኸውም ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች የአየር ለውጥ መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን በማቅረብና በማከፋፈል፤ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት፤ የተፈጥሮ ሀብት ክብካቤና ጥበቃ ሥራን በማጠናከር የጎላ ተግባር እያከናወነ ነው።
ልማት ኮሚሽኑ ለቤተ ክርስቲያን ደን ልማትና ጥበቃ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት በመስጠት፣ የቤተ ክርስቲያን ደን ፕሮጀክት አጥንቶ በአጋርነት የሚሠራ ድርጅት በማግኘቱ፣ በተመረጡ ገዳማት ላይ የደን ጥበቃና ማስፋፋት ሥራን መሠረት በማድረግ፣ የተራቆቱ መሬቶች በደን የሚሸፈኑበትን ኹኔታ ለማስቻል ደረጃ በደረጃ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ፣ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጅና የሶላር መብራት ተከላ፣ በ15 ገዳማት ያከናወነ ሲኾን፣ ለወደፊቱም በሰፊው የሚሠራበት የልማት መስክ ኾኖ የሚቀጥል ይኾናል።
የልማት ኮሚሽኑ፣ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማትን በመገንባትና የመስኖ ልማት በማስፋፋት ወደፊት በድርቅ ሳቢያ የሚከሠቱ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን በአፋር እና በሰሜን ሸዋ የአፋር አዋሳኝ ወረዳዎች እና በሌሎችም ላይ በሰፊው በማከናወን ላይ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች ውስጥ፣ የሕዝቡ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
ብፁዕነታቸው፡- ልማት ኮሚሽኑ ሥራውን እስከ ታች አውርዶ ለመሥራት የሚያስችል የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በክልል እና በዞን ከተሞች ስላሉት በእነርሱ አማካይነት ሥራውን ማኅበረሰቡን መሠረት አድርጎ ለማከናወን ምቹ ኹኔታ ተፈጥሮለታል። በመኾኑም ኮሚሽኑ በሚንቀሳቀስባቸው የፕሮጀክት ወረዳዎችና ቀበሌዎች ሥራውን ለማስተዋወቅም ኾነ ከሕዝብ ጋራ ለመሥራት ምቹ መንገድ በመኖሩና ኮሚሽኑ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስላለው የማኅበረሰቡ የልማት ተሳታፊነት በጣም ከፍተኛ ነው። የልማት ሥራዎቻችን በዘለቄታዊነት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት፣ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ስለታከለበት ነው፤ ይህም በግልጽ የሚታይ እውነት ነው።
ሰንደቅ፡- የስደተኞችንና ከስደት ተመላሾችን፣ መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላትና መልሶ በማቋቋም በኩል በኮሚሽኑ ሥራዎች የተገኙትን ውጤቶች ቢያብራሩልን?
ብፁዕነታቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ ስደተኞችንና ከስደት ተመላሾችን በመቀበልና አስፈላጊውን ርዳታ በማድረግ በሀገሪቱ ቀደምት ታሪክ ያላት ስትኾን ከአምስት ዐሥርት ዓመታት በላይ አገልግሎቱን እየሰጠች ትገኛለች። የሀገሪቱ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለስደተኞችና ከስደት ተመላሾች በተቀናጀ ኹኔታ አገልግሎት መስጠት ሳይጀመሩ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን አገልግሎት በቀዳሚነት መስጠቷን ያሳያል። በነበሩት የድጋፍ ጊዜያትም ለሰው ልጅ ሕይወት አስፈላጊ የኾኑና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ያማከለ ድጋፍና ርዳታ መስጠት ተችሏል።
በሒደትም የቤተ ክርስቲያንዋ የማኅበራዊ ረድኤት ክንፍ የኾነው የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ በ1964 ዓ.ም. በሕግ ሲቋቋም፣ የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ በማካተት በርካታ ተግባራትን ለመፈጸም በቅቷል።የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ መምሪያ፣ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሥር በመኾንና የራሱን አስተዳደር በማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዚኽም መሠረት ኮሚሽኑ፥ ከመንግሥት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችጋ በጋራ በመኾን በዐዲስ አበባና አካባቢዋ ባሉ ከተሞችና በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ በሚገኙ 18 የመጠለያ ጣቢያዎች አማካይነት ቁጥራቸው በየጊዜው የሚለያይ ቢኾንም፣ በአኹኑ ሰዓት ከ801 ሺሕ በላይ ለሚኾኑ የተለያዩ ሀገር ስደተኞች ማለትም፦ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማልያ፣ ከየመን፣ ከኤርትራ፣ ከኮንጎ፣ ከሱዳን፣… ወዘተ ለመጡ ስደተኞች የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።
ኮሚሽኑ ለስደተኞች፥ የመጠለያ፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የገንዘብ፣ የጤና፣ የማኅበራዊና የሥነ ልቡና ምክር፣ የትምህርትና የሞያ ክህሎት ሥልጠና ድጋፍና የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን ይሰጣል። በተጨማሪም ስደተኞች ቤታቸው እንዳሉ ኾነው እንዲሰማቸው ለማድረግ የሚኖሩበት መጠለያና አካባቢው ምቹ እንዲኾን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። የአካባቢ ክብካቤ፣ የአካባቢና የግል ንጽሕና እንዲጠበቅ እንዲኹም የመጡበትን ዐዲስ አካባቢ እንዲላመዱ የማስተማርና የማሳወቅ ሥራዎች በሰፊው ይከናወናሉ።
በመኾኑም ስደተኞች በሚሰጣቸው የትምህርትና የሞያ ክህሎት ድጋፍ የበርካታ ሞያዎች ባለቤት ኾነው የተለያዩ የገቢ ምንጮች የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን በማቋቋም ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ስደተኞችን ከቤተሰብ ጋራ በማገናኘት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ሲኾን፣ ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል።
በአራቱም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ስደተኞች የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ፤ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ድጋፍና ክብካቤ፣ በግጭት አፈታት፣ በፆታ ጥቃት ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም ይሠራል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ከመሰል አገራዊና የውጭ ተቋማት ጋራ ያለው ቅንጅትና መተባበር ምን ይመስላል?
ብፁዕነታቸው፡- የልማት ኮሚሽኑ በሚተገብራቸው የልማት ሥራዎችና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት ከሌሎች ልቆ እስከ መሸለም የበቃው ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋራ ተናቦ፣ ተቀናጅቶና ተባብሮ በመሥራቱ ነው። ዘላቂ ልማትን ማምጣት የሚቻለው ከኹሉም ባለድርሻ አካላት ጋራ ተቀናጅቶና ተባብሮ መሥራት ሲቻል እንደኾነ የታወቀ ነው።
ኮሚሽኑ ይህን መርሖ በዋናነት በመከተል በግልጽነትና በተጠያቂነት በመንቀሳቀስ በአነስተኛ በጀት ታላላቅ የልማት ሥራዎችን በመገንባት እውን እያደረገ ይገኛል። በመኾኑም ኮሚሽኑ የከፈታቸው የልማት የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችም ኾነ የፕሮጀክት ጽ/ቤቶች በሚሠሩባቸው አካባቢዎች፣ ከኹሉም የልማት ባለድርሻ አካላት ጋራ መልካም ግንኙነት ያላቸው ከመኾኑም በተጨማሪ፣ በፕሮጀክት ሥራ መልክአ ምድራቸው አስቸጋሪ በኾኑ ሥፍራዎች ኹሉ የተለያዩ የልማት ተግባራትን በማከናወንና ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የካበተ ልምድ ስላላቸው በየፎረሙም በተምሳሌነት የሚቀርቡ ኾነዋል።
ሰንደቅ፡- የኮሚሽኑ ፕሮጀክቶችና እንቅስቃሴዎች፣ በሀገራዊ ሽፋን ያላቸው ሥርጭት የተመጣጠነ ነው?
ብፁዕነታቸው፡- አዎን! በእኛ በኩል ሙሉ በሙሉ ባይኾን እንኳ ፕሮጀክቶች ያላቸው ሥርጭት በአብዛኛው የተመጣጠነ እንደኾነ እምነታችን ነው። ኮሚሽኑ በአኹኑ ሰዓት በሚያካሒዳቸው 27 የሚኾኑ የልማት ፕሮጀክቶችና በ18 የስደተኞች መቀበያ ካምፕ አማካይነት በኹሉም ክልሎች በሚገኙ የፕሮጀክት ወረዳዎች ላይ እየሠራ ይገኛል።
ይኸውም በጋምቤላ ክልል፥ ጋምቤላ ዙሪያ ወረዳ፣ ፊኝዶ፣ ተርኪዲ፣ ኩሌ፣ ሆኮቡ፤ በቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል፥ በከማሽ፣ በኩርሙክ፣ በሸርቆሌ፣ በባምፓሲ፣ በቶንጎ፤ በአፋር ክልል፥ በአርጎባ ልዩ ዞን፣ ሰሙ ሮቢ፣ ዱለቻ፤ በኦሮሚያ ክልል፥ በጉርሱም፣ በጃርሶ፣ በአርሲ ሮቤ፣ በቄለም ወለጋ፤ በሶማሌ ክልል፥ በጅግጅጋ፣ በሸደር፣ በቀብሪበያህ፣ በአውበሮ፣ በኮቤ፣ በመልካ ጂዳ፣ በሔለወይኒ፣ በቆልማንዩ፤ በአማራ ክልል፥ በሊቦ ከምከም፣ በአንኮበር፣ በጊሼ ራቤል፣ በዳውንት፣ በበርኸት፤ በትግራይ ክልል፥ በክልተ አውላዕሎ፣ በእንደርታ፣ በሽመልባ፣ በአደ አርሹ፣ በእፀጽ፤ በደቡብ ክልል፥ በጉራጌ፣ በሙዑር፣ በቡታጀራ፣ በወልቂጤ፣ በሲዳማ፣ በጌዲዮ፣ በይርጋ ዓለም፣ በአለታ ወንዶ፣ በሃላባ፣ በአርባ ምንጭ በ10 ወረዳዎች የኤች.አይ.ቪና የሥነ ተዋልዶ ጤና ሥራዎች፤ ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ በኹሉም ክልሎች በ150 ወረዳዎች ላይ የኤች.አይ.ቪ እና የሥነ ተዋልዶ ጤና ሥራዎች ያከናውናል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች ሲያከናውናቸው የቆያቸው የልማት ፕሮጀክቶች እየተዘጉ እንደኾነ ይነገራል፤ ፕሮጀክቶቹ የሚዘጉበት አልያም የሚቋረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
ብፁዕነታቸው፡- ፕሮጀክቶች በተፈጥሮአቸው የጊዜ ገደብ አላቸው፡፡ ይኹንና በኮሚሽኑ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች እስከ ታች የሚዘልቁትን የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን፤ የፕሮጀክት ጽ/ቤቶችንና የማኅበረሰብ ማኅበራትን በመጠቀም ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የፕሮጀክት አፈጻጸም ሒደት በመከተል ኅብረተሰቡ የተለያዩ ሕግጋትንና ደንቦችን እንዲያወጣ በማገዝ ፕሮጀክቶቹ በዘለቄታነት የሚቀጥሉበትን ኹኔታ እያመቻቸ በራሱ በኅብረተሰቡ እየተመራ የሚከናወኑ የፕሮጀክት ዓይነቶች ናቸው።
ፕሮጀክቶች ዘላቂ በኾነ መልኩ እንዲቀጥሉ የሚከተሉት ዝርዝር ተግባራት ይከናወናሉ። ተጠቃሚው ኅብረተሰብ፥ በፕሮጀክት ጥናት፣ ዕቅድ፣ ክንውን፣ ክትትልና ግምገማ እንዲሳተፉ ይደረጋሉ። በዕቅድ ዝግጅት ወቅት የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ድርጅቶች፣ በየደረጃው የሚገኙ የአካባቢ አመራሮች… ወዘተ በፕሮጀክት ሒደት ውስጥ ያላቸው ድርሻ በግልጽ እንዲቀመጥ ይደረጋል። የፕሮጀክቱን መጀመር የሚያበሥር ዓውደ ጥናት ይዘጋጃል፡፡ ከዚህም ጋራ ተያይዞ የእያንዳንዱ የሥራ ድርሻ በግልጽ ለውይይት ይቀርባል። የፕሮጀክት ተግባራትም እንደተጠናቀቁ የሚመለከተው ባለድርሻ አካል በወቅቱ በሕጋዊ የርክክብ ሰነድ ተረክቦ እንዲያስተዳድራቸው ይደረጋል።
ሰንደቅ፡- አንዳንድ ምግባረ ሠናይ ድርጅቶች፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ሕግ አላሠራ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ፤ በዚኽ ረገድ ኮሚሽኑ የገጠመው ችግር ይኖር ይኾን?
ብፁዕነታቸው፡- ኮሚሽናችን ከ46 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየ ነው። በዕድሜው ሦስት መንግሥታት ተፈራርቀዋል። በእነዚህ ዘመናት ሕጎች ተለዋውጠዋል። ኮሚሽኑ ኹሉንም እንደ አመጣጡ አስተናግዷል። ፈቃድ ሰጪው አካል ቀድሞ በፍትሕ ሚኒስቴር ነበር፡፡ አኹን ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ተቋቁሞ የራሱን ሕግ ይዞ እየሠራ ነው።
በእኛ በኩል ቀድሞውንም እንቅስቃሴያችን፥ ተጠቃሚውን መሠረት ያደረገ በመኾኑ የገጠመን የጎላ ችግር የለም። 70 በ30 የሚለውን ሕግ ቀድመን ተግብረነዋል፤ ነገር ግን ይህ 10 በ90(10 ከመቶ በላይ ከውጭ ለጋሾች ገንዘብ መቀበል አይቻልም) የሚለው የውጭ ለጋሽ ድርጅቶች ብዙም አልተቀበሉትም። እርሱ ነው ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው። ሕጉ፥ የሀገሪቱንና የረጂዎችን ኹኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም።
ለእኛ ግን ትልቁ ተጽዕኖ ይህ አይደለም። የእኛ ትልቅ ተጽዕኖ፣ ሕዝባችን ከተረጂነት መላቀቅ አለመቻሉ ነው። የውጭ እጅ ማየት የትም አያደርስም። የጠባቂነት መንፈስ ያሳድራል። ከጠባቂነት መንፈስ ተላቅቀን ባለን ሀብት መጠቀም መጀመር አለብን።
የረጂዎችንም ኹኔታ ስንመለከት፣ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ችግሮች በዓለም ዙሪያ እየበዙ መጥተዋል። ሩቅ ሳንሔድ እዚኹ ጎረቤቶቻችን ሱዳንና ሶማልያ በየዕለቱ ሰዎች እየሞቱ፣ እየተሰደዱ ረጂዎች ለእኛ ቅድሚያ ሰጥተው እጃቸውን ሊዘረጉልን አይችሉም። በዚህ ምክንያት ከልመናና ከፈረንጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ መሥራት ይኖርብናል። ዓለም አቀፍ ርዳታ ለተወሰነ ጊዜ ከችግር ለመውጣት ሊጠቅመን ይችላል፤ ለሽግግር ጊዜ ሊረዳን ይችላል፤ በዘላቂነት ግን የሚጠቅመን አይደለም።
ሰንደቅ፡- ለልማትና ለርዳታ የሚውል ሀብት ከሀገር ውስጥ ለማሰባሰብ ዕቅድ አላችኹ?
ብፁዕነታቸው፡- በትክክል፤ ምንም ዓይነት የውጭ ተጽዕኖ የሌለበት ሕግና ደንብ አውጥተናል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከሌሎች ምሁራን ጋራ በዚኽ ጉዳይ ሕግና ደንብ አዘጋጅተናል። በቀጣይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በሥራ ላይ የሚውል ይኾናል። ይህ ጥናት ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆን ራሳችን እንድንችል የሚረዳን ይኾናል ብለን እናስባለን።
በአኹኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ 10ሺሕ ያኽል ሕፃናትን ትከባከባለች። ከሕፃናቱ መካከል አሳዳጊ አልባዎች አሉ። ቤተሰቦቻቸውጋ እንዳሉ የሚረዱ አሉ። ለእነዚኽ የምናገኘው ርዳታ በአኹኑ ሰዓት በግማሽ ቀንሷል። ምን እናድርግ ብለን አይተነዋል። በሐሳብ ደረጃ፥ አንድ ምእመን አንድ ልጅ በፈቃደኝነት ቢይዝ ብለን ብዙ ሕፃናትን መርዳትና መደገፍ እንደሚቻል አይተናል። በአኹኑ ወቅት በጉዲፈቻ ወደ ውጭ የሚሔዱ ሕፃናት ምን አሳዛኝ ኹኔታ እየደረሰባቸው እንደኾነ እናውቃለን። ይህ ችግር እንዲቆም እዚኹ በሀገራችን ልንረዳዳና ልንደጋገፍ ይገባናል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በአኹኑ ወቅት ከለጋሾች ጋራ ያለውን ግንኙነትና የወደፊት ዕቅዱን ቢጠቁሙን?
ብፁዕነታቸው፡- የልማት ኮሚሽኑ በአኹኑ ወቅት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋራ ያለው ግንኙነት በመልካምና በተሻለ ኹኔታ ላይ ይገኛል። ዋናው ጉዳይ፣ ለሚረዱን ድርጅቶች፣ ለመንግሥትና ለተጠቃሚ ማኅበረሰብ ታማኝ ኾኖ በመገኘት የታለመለትን ፕሮጀክት በጥራትና ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ በጽናት ማከናወን ነው።
የልማት ኮሚሽኑም ዋነኛ ዓላማ፣ የኅብረተሰቡ ኑሮ ተሻሽሎ ማየትና ለተሻለ ዕድገት ማብቃት በመኾኑ በዚኹ ረገድ ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል። ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት ኹኔታ የሚንቀሳቀስ በመኾኑ በየጊዜው ከለጋሽ ድርጅቶች አዎንታዊ ምላሽ ሲያገኝ ቆይቷል፤ አኹንም እያገኘ ይገኛል።
በተለይ ኮሚሽኑ፣ የሕፃናት ፖሊሲን ቀርፆና አጽድቆ በሥራ ላይ ማዋሉና የማኅበረሰብ ተጠያቂነት አጋርነት(Humanitarian Accountability Partnership) ማሕቀፍ አዘጋጅቶና አጽድቆ በመተግበሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋራ ያለውን ግንኙነት የበለጠ አጠናክሯል።
ኮሚሽኑ በቅርቡ፣ የኹሉንም የፕሮጀክት አጋሮች ተወካዮችን በመጋበዝ ባለን የጋራ አጀንዳና በቀጣይ ስለሚኖረው የሥራ ግንኙነት በተመለከተ ለመወያየት ዕቅድ በመያዝ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በአኹኑ ሰዓት የራሱ የኾነ የገቢ ምንጭ ለማጠናከር ምን እየሠራ ነው?
ብፁዕነታቸው፡- ኮሚሽኑ ከውጪ ከሚያገኘው የርዳታ ድጋፍ በተጨማሪ በገቢ ራሱን ለማጠናከር እንዲቻል ዓላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ይልቁንም በአኹኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በተከሠተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የውጭ ርዳታ በእጅጉ እየቀነሰ የመጣ ስለኾነ የተለያዩ የገቢ ምንጭ ዕቅዶችን ማዘጋጀትና መሥራት ግዴታ ኾኗል። በዚኹ መሠረት ኮሚሽኑ የገቢ ምንጭ መምሪያ አደራጅቶ ሥራ ጀምሯል።
በቃሊቲ አካባቢ ከሚገኘው የኮሚሽኑ ጋራዥና መጋዘን እንዲኹም የከርሰ ምድር መቆፈሪያ ሪግ ማሽንን ጨምሮ ለዚኹ ተግባር በማዋል የገቢ አቅሙን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው።
በተጨማሪም፣ አንድ የሻማ ማምረቻ ፋብሪካና በኹለት ቦታዎች ላይ የታሸገ የንጹሕ የመጠጥ ውኃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም መሠረታዊ ጥናቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በእንጦጦ አካባቢ የሆስፒታል ግንባታ ዕቅድ እንዳለው ይታወቃል፤ ሒደቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማወቅ ይቻላል?
ብፁዕነታቸው፡- ቤተ ክርስቲያን፣ ከ46 ዓመት በፊት የልማት ኮሚሽኑን ስታቋቁም፥ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞችን ለመርዳት፣ አባት እናት የሌላቸውንና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ምእመናን ከውጭና ከውስጥ በሚገኝ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
ቤተ ክርስቲያን፥ በገዳማት፣ በአድባራትና በገጠር አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ጥቅም ላይ ያልዋለ ብዙ መሬት ስላላት መሬቱን በማልማት ገዳማቱና ኅብረተሰቡ ከልማቱ ውጤት እንዲጠቀሙ ማድረግ፤ እንዲኹም በየአካባቢው የትምህርት ቤትና የጤና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር መሠረተ ልማት ማካሔድ አንዱ ተግባሯ ነው። ይህን የጤና አገልግሎት ለማስፋፋትና ለማዳበር በቅርቡ በእንጦጦ አካባቢ አንድ ራሱን የቻለ ከፍተኛ ሆስፒታል ተቋቁሞ በዓይነትና በጥራት አገልግሎት እንዲሰጥ ዕቅድ ወጥቷል።
ሆስፒታሉ በዓይነቱም ኾነ በባሕርይው የተለየ ከመኾኑም ባሻገር የግንባታው ወጪ ከ370ሺሕ የአሜሪካን ዶላር በላይ ሲኾን፣ በኢትዮጵያ ብር ሲተመን ደግሞ ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ተይዞለታል። ሥራው በሚጀምርበት ጊዜም ለ2ሺሕ100 ቋሚና ለ369 ጊዜአዊ በጥቅሉ ለ2ሺሕ469 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ሆስፒታሉ፣ የልዩ ልዩ በሽታዎች መታከሚያና ማገገሚያ ክፍሎችና መሣሪያዎች ይኖሩታል፡፡ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ የዲፕሎማቲክና የኤምባሲ ሠራተኞችንና ከልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሕመምተኞችን ለማከም ከ200 በላይ አልጋዎች ይኖሩታል።
ቅድመ ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ይህ በቀጥታ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በአሜሪካን ሀገር ከሚገኝ ሌዠንደር ኮርፕ ከተሰኘ ድርጅት ጋራ በአጋርነት የሚቋቋመው ሆስፒታል፣ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና በአገሪቱ ውስጥ የቱሪዝምን አገልግሎት ለማስፋፋት እንደሚረዳ ይታመናል።
የአሜሪካ መንግሥትና በአሜሪካ ውስጥ ያሉ አበዳሪ ድርጅቶች፣ ብድሩንም ኾነ ለብድሩ ዋስትና ለመስጠት ሓላፊ እንደሚኾኑ ቃል ገብተዋል። በኢትዮጵያ በኩል፣ ግንባታውንና ከውጭ የሚገኘውን መዋዕለ ነዋይ እውን ለማድረግ፣ በእንጦጦ አካባቢ ያለውና ለዚኹ ጉዳይ የተከለለው መሬት ለአገልግሎቱ እንዲውል ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ለማግኘት በሒደት ላይ እንገኛለን።¾

No comments:

Post a Comment