Wednesday, April 26, 2017

ሃይለማርያም ደሳለኝ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሃል መጠራጠርና አለመተማመን አንደነበረ አመነ! (ክፍፍሉ አሁንም አንዳለ ግን መቀበል የፈለገ አይመስልም)



 
ምን ቢደግፉት ቢይዙት በባላ
 አንዴ ከዘመመ ቤት የለውም መላ !
በአገራችን ባለፉት ሁለት አመታት የተካሄዱት ህዝባዊ  ትግሎች በገዥው ቡድን ውስጥ መከፋፈልን ፈጥረው አንደነበረና ፣ የመግዛትም አቅሙን በመፈታተናቸው ለስልጣኑ ስሱ የሆነው ኢህአዴግ፣  በአንድ ወገን ሕዝባዊ ትግሉን ለማፈን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የትግሉ ስፋትና ጥንካሬ በመሃላቸው የፈጠረውን ሽብረክ ማለት ለመቋቋም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ  የሚታወቅ ነው ።
ለስድስት ወር ተብሎ የታወጀው አዋጅ በቅርቡ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል ቢባልም፣ ለሕዝባዊ ትግሉ መቀጣጠል ምክንያት የሆኑትን ችግሮች ከስሩ ለማስተካከል ወይንም  ለመቅረፍ አቅሙ፣ ፍላጎቱም ሆነ ቅንነቱ የሌለው ኢህአዴግ፣ አዋጁ ቢነሳ ሕዝባዊ ትግሉ አንደገና ሊያገረሽ ይችላል የሚል ፍራቻ ስላለው በርግጠኝነት አዋጁን በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ  ሊያነሳ ይችላል የሚል ግምት የለም።
ሆኖም በቅርቡ ለአገር ውስጥ ጋዜጦች መግለጫ የሰጠው ሃይለማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ ከሞላ ጎደል  ሰላም ሰፍኗል አገር አማን ነው ፣ በተጨማሪ  ደግሞ  አንደ  ሪፖርተር ዘገባ “ኢህአዴግ አንዣበውበት የነበሩ ውስጣዊ  መደናገሮችን በማጥራት ወደ ጤናማነት ” ተሸጋግሯል   ወዘተ  የሚል ፉከራ ቢያስተጋባም፣ በዚሁ መግለጫው በሁሉም አባል ድርጅቶች መሃል፣ ደረጃው የተለያየ መጠራጠር ተፈጥሮ አንደነበር ሊሽሽገው የማይችል በመሆኑ ለማመን ተገዷል። ሃይለማርያም በመሃከላቸው ግልጽ ውይይት በማካሄድ መተማመን ፈጥረናል የሚል  አስተያየት ቢሰነዝርም መሬት ላይ ያለው ውነታ ግን አስተያየቱ ተአማኒነት የሌለው ተራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ያጋልጣል ።
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሃል ያለው አለመተማመንና መወነጃጀል ጠንከር ብሎ የታየው በብአዴን፣ ኦህዴድና ህወሃት መሃል አንደነበረ፣ ለዚህም ዋናው ምክንያት በሁለቱ ክልሎች ተካሂዶ የነበረው፣ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ያልታየ መጠነ ሰፊ  ሕዝባዊ ትግል በድርጅቶቹ ላይ የፈጠረው ጫና  በመሆኑ፣ ለሕዝባዊ ትግሉ መንስኤ የሆኑት ጉዳዮች አጥጋቢ መልስ አስካላገኙ ድረስ በአስተማማኝ ደረጃ በመሃላችን ሰላም ሰፍኗል የሚለው የሀይለማርያም ገላጻ ብዙ አያስኬድም ።
አርግጥ ነው ምንጠራ በሚመስል መልኩ ብአዴን ላይ በተካሄደው ዘመቻ (ገዱ አንዳርጋቸውን ይብላ አይብላ አስካሁን በገሃድ ባይታወቅም) ለህወሃት ማስፈራሪያና አጅ ጥምዘዛ ያጎበደደ የሚመስለው የብአዴን የአመራር ክንፍ፣ “አህት ድርጅቴ ህወሃትን ያላግባብ  ጠርጥሬ ነበር ይቅር በሉኝ” የሚል እንድምታ ያለው ጽሁፍ በመጽሄቱ አውጥቷል መባሉ ቢታወቅም፣የዚህ ቡድን አቋም፣ ልቡ የሽፈተውን የበታችና መሃከል አመራሩን አንዲሁም  አብዛኛው አባላቱን ይወክላል ለማለት አዳጋች ነው። ድርጅቱ ላይ ይሄ ወከባና እጅ ጥምዘዛ ቢካሄድም በክልሉ አሁንም ሰላም እንደሌለና ፣ ትጥቅ አንስቶ እስከመፋለም የደረሰ ተቃውሞ እየጎለበተ እንደሆነ ጭምር ይታወቃል ።
በሌላ በኩል ኦህዴድ የድርጅቱን 27ኛ ዓመት በአል ምክንያት በማድረግ ባደረገው ስብሰባ ላይ፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር ለማ መገርሳ የህዝቡን ጥያቄ በቅጡ መመለስ ካልቻልን  እንደ ድርጅት፣እንደ መንግስት እያንዳንዳችን ከገባንበት ጓዳ ውስጥ አንገታችንን ይዞ አውጥቶ የፈለገውን ነገር ሊፈጽምብን እንደሚችል እንዲህ አይነት እርምጃ ሊወስድብን እንሚችል አይተናል፡፡በፊልም ሣይሆን በተጨባጭ ውስጥ ኖረን አይተናል ይሄ ቲያትር አይደለም፡፡ ጎበዝ ሌላ አማራጭ የለንም፣  በሚል ጠንከር ያለ ንግግር  አገራችን በተለይ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል  ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ በግልጽ አስቀምጦት ነበር።
በሱ አባባል ህዝብ የሰጠውን የመጨረሻ እድል ተጠቅሞ የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ውጭ አማራጭ እንደሌላቸውም የተገነዘበ መሆኑን ለማስረገጥ” በእውነት ሁሉ ነገር ድኗል ሁሉ ነገር ምላሽ አግኝቷል ሁሉ ነገር አልቆለታል ብለን የምናስብ ከሆነ ሞኝነት ነው” ብሎም ነበር።
በቅርቡ ደግሞ ኦሮሚያ ውስጥ  ስለነበረው፣ ስላለውና ወደፊትም ስለሚኖረው የባለሀብቶች ተሳትፎ አስመልክቶ “በግልባጭ ” መልአክት አንደማይቀበል፣ የ ክልሉ ውስጥዊ ጉዳዮችም  የሚካሄዱትና የሚወሰኑት በሚመለከተው ክፍል ብቻ የሚወሰን መሆኑን ሲናገር፣ የነፍስ አባትነት ሚና የነበራቸውም ከአንግዲህ ስፍራ አንድሌላቸው ሲገልጽ ፣  አንጻራዊ ነጻነትን እያንጸባረቀ እንደሆነና፣ የሃይለማርያም እንደቀድሞው በመሃላችን ሰላም ሰፍኗል፣ በአስተማማኝ ሁኔታ ፓርቲው ወደ ጥንካሬው ተመልሷል …ወዘተ ምኞት አንጂ በመሬት ያለውን ሁኔታ ገላጭ አለመሆኑን የሚያመላክት ነው ።
ከዚህ በተጨማሪ ፣ ለስሙ ለጠ/ሚሩ  ተጠሪ የሆነ፣ በአባይ ፀሃዬ(በግልባጭ ኃይለማርያምን የሚቆጣጠር የወታደራዊና ደህንነት ጁንታው የሲቪል ተጠሪ  ነው የሚሉ አሉ) የሚመራ የጥናት ማእከል ከአመት በላይ አስጠንቼ አቀረብኩት ለሚለው ሪፖርት ሰፊ የህዝብ መገናኛ ሽፋን ተሰጥቶት፣ሃይለማርያም የሚመራው የአስፈጻሚ ኃይል ” ዜጎችን በግላቸውም ሆነ በማህበር ተደራጅተው ወይም ባላቸው ኃላፊነት በሚመለከታቸው ጉዳይ ሲሳተፉና ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ  በዛቻ፣ በማስፈራሪያ፣በጥቃትና  አድሎዓዊነት የሚያይ ፣ ሁሉ ነገር ላይ የበላይ” ካልሆንኩ ብሎ የሚውተረተር ብሎ  አብጠልጠሎታል።
ማአከሉ ከላይ አንዳልኩት ተጠሪነቱ ለጠ/ሚር ነው ቢባልምና፣ ያቀረበውም ሪፖርት ሃይለማሪያም ከሚያቀርበው ትርክት ሙሉ ለሙሉ የሚላተም ቢሆንም፣ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሃይለማሪያም ሪፖርቱ እኔ ጋ አልደረሰም በሚል የመለሰው መልስ “መተማመን ፈጥረናል “ የሚለው ሃሰት መሆኑን ከበቂ በላይ  የሚያረጋግጥ ነው።
ሁኔታ ካመች  ጋብ ያለው ሕዝባዊ ትግል አገርሽቶ ከቁጥጥር ውጭ ሊሄድ ይችላል  የሚል ፍራቻና፣ በድርጅቶቹ መሃል ያለው አለመግባባትና ጥርጣሬ በቅጡ አለመርገብ ተዳምሮም ነው  ነሐሴ ላይ መካሄድ የነበረበት የኢህአዴግ ስብሰባ አንዲተላለፍ  ያስገደደው ።
ለማጠቃለል  ህዝባዊ አመጽን ፍራቻና ለስልጣን በመሳሳት፣ የሚፎከርበትን ህገ መንግስት አሽቀንጥሮ ጥሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በኮማንድ ፖስት ስም ስልጣኑን ለወታደራዊና ደህንነት ጁንታ አሳልፎ የሰጠው የሃይለማሪያም መንግስት ከእንግዲህ ውስጣዊ ሰላም የማግኘቱና እንደትላንትናው የህወሃት የበላይነት አጠያያቂ ያልሆነበት ኢህአዴግ የሚኖርበት አጋጣሚ ይመጣል ብሎ ለመናገር የማያስችል ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን።

አበጋዝ ወንድሙ

No comments:

Post a Comment