Tuesday, April 25, 2017

ፓትርያርኩ ተሸነፉ? “ሙስናን ተዉ፤ ማለት ከአንበሳ አፍ ሥጋ እንደ መንጠቅ ነው፤ አቅሙም ጉልበቱም የለንም” አሉ



  • ሙስናን ለማስቀረት፣ በቤተ ክርስቲያን ምንም እንዳልተደረገ መናገራቸው አጠያያቂ ነው
  • የአንድነት ዕጦት፣ የአሠራሩ መሥመር አለመያዝና ቸልታ ፕትርክናውን አክብዶባቸዋል
  • ለቤተ ክርስቲያን የሚያስብ እንደሌለ እና ኹሉም በገንዘብ መሸጡንና መለወጡን ጠቅሰዋል
  • ባለጉዳዩ ኹሉ ወደ በላይ አካል መሮጡ፣ የመዋቅሩንና አደረጃጀቱን ውድቀት አመላክቷል
  • መነኵሴ ዘመድ እንደሌለውና “በመንፈሳዊነት” ቢታወሱ ደስ እንደሚያሰኛቸው ጠቁመዋል

ሐራ ዘተዋሕዶ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ከአራት ዓመት በፊት፣ ወደ መንበረ ፕትርክናው በመጡበት በዓለ ሢመት ባሰሙት ቃለ በረከት፥ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚሠራው ሥራ እግዚአብሔር እና ምእመናን በደስታ የሚቀበሉትና የሚወዱት፤ በመንፈሳዊነት የተደገፈ፤ ሓላፊነትን፣ ተጠያቂነትን፣ ብቃትን፣ ንቃትን፣ ጥራትን፣ ታማኝነትን፣ ሐቀኝነትን፣ ፍትሐዊነትን የተጎናጸፈ ፍጹም ጤናማ የኾነና እንከን የሌለበት መኾን እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን፥ የእውነትና የሐቅ አስተማሪ እንጅ ተማሪ መኾን እንደሌለባት ከጠቆሙ በኋላ፣ “ሐቀኝነት፣ ታማኝነትና መልካም ሥነ ምግባር ከቤተ ክርስቲያን ካልተገኙ ከየት ሊገኙ ይችላሉ?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው፣ በዚያው ዓመት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በርእሰ መንበርነት በመሩት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ደግሞ፦ ከቤተ ክርስቲያን ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣመውን ሙስና ለማጥፋትና ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ ሥር ነቀል የለውጥ ርምጃ በቆራጥነትና በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲኾን አሳስበዋል፤
“ሥር ሰዶ የሚታየው አሳፋሪና አሳዛኝ ብልሹ አሠራር ሳይታረም ቢቀጥል፣ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ችግር ላይ እንደምትወድቅ በግልጽ እየታየ ነው፤” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሊወሰዱ ይገባል ያሏቸውን ሦስት መሠረታዊ ርምጃዎች ጠቁመዋል፡፡ እነርሱም፡-
  1. ብልሹ አሠራርን ለማረምና ለማስወገድ፡- የፀረ ሙስና ዐቢይ ኮሚቴ፣
  2. አስተዳደሩን በዐዲስ መልክ ለማዋቀር፡- የአስተዳደር መሻሻል ዐቢይ ኮሚቴ፣
  3. የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት፥ ዘመናዊ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለማደራጀት፡- የገንዘብ አያያዝ ሥርዓት ማሻሻያ ዐቢይ ኮሚቴ
እንዲቋቋምና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ አንድ ወጥ የኾነ ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲቻል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
እጅግ የተንዛዛ ቢሮክራሲ፤ ከቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ተልእኮ ጋራ ያልተቀናጀ የሰው ኃይል ምደባ፤ ዕውቀትና የሥራ ችሎታ ሳይኾን ሙስና፣ ወገንተኝነትና የሥነ ምግባር ብልሽት በስፋት የሚንጸባረቅበት አሠራር፣ በካህናትና በምእመናን ላይ ቅሬታንና እምነት ማጣትን እያስከተለ እንዳለ ገልጸው፣ “በፍጥነት ማስተካከል ካልቻልን፣ በቅድሚያ በእኛ ላይ የሚፈርድ የገዛ ራሳችን ኅሊና ነው፤ በይቀጥላልም እግዚአብሔርም ሌላውም ይፈርድብናል፤” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አክለውም፣ “በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ቢያዳግት እንኳ፣ የለውጡን መሠረት ግን በአስቸኳይ ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ እጅግ አስፈላጊ መኾኑ ሊሠመርበት ይገባል፤” በማለት ነበር፣ የብፁዓን አባቶችን አጋርነት የተማፀኑት፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስም፣ በዚያው ዓመት (ማለትም በ2005 ዓ.ም.) የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው፣ የቅዱስነታቸውን ማሳሰቢያ ተቀብሎና በአጀንዳ ቀርጾ ከተወያየ በኋላ ባወጣው መግለጫ ኹለት ዐበይት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ እነርሱም፡-
  • የመጀመሪያው፥ ብልሹ አስተዳደርና አሠራር፤ ዘመኑን ያልዋጀና ጥራት የጎደለው የፋይናንስ አያያዝ፣ እንደዚኹም ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን ኹሉ ወሳኝ በኾነ መልኩ ለመቅረፍና ለማድረቅ፤ ከዚኽም ጋራ ቤተ ክርስቲያን በመሪ ዕቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር ለመቀየስ፥ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን የተካተቱበት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን የማጥራትና የማጥናት ሥራ እንዲቀጥል፤
  • ኹለተኛው፡- የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ፣ እንደዚሁም በስብከተ ወንጌልና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሌሎች አህጉረ ስብከት በሞዴልነት የሚጠቀስ ሀገረ ስብከት መኾን ስለሚገባው፣ በአንድ ሀገረ ስብከት፣ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እየተመራ እንደዚኹም በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኃይል አመዳደብ የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንዲሠራ አስፈላጊው ክትትል ኹሉ በቋሚ ሲኖዶስና በመንበረ ፓትርያርኩ እንዲደረግ፤ የሚሉ ከፍተኛ ውሳኔዎች ነበሩ፡፡
በዚኽም መሠረት፣ ዐበይት ኮሚቴዎቹ ተቋቁመው፣ መዋቅራዊ አደረጃጀቱና የአሠራር ሥርዓቱ ዘመኑን በዋጀና ስትራተጅያዊ በኾነ መልኩ ለማሻሻል የሚያስችሉ ወሳኝ ጥናቶች ተዘጋጅተው ከአተገባበር ስልታቸው ጋራ ለምልአተ ጉባኤው ቀርበው ከመጽደቃቸውም በላይ፣ የማስፈጸሚያ በጀትም ተመድቦ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በተለይ አዲስ አበባን በተመለከተ ቀርቦ የነበረው፥ የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት፣ በምልአተ ጉባኤው አቅጣጫ መሠረት፣ በሀገረ ስብከቱ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ለውይይት በተዘረጋበት ወቅት፣ የብዙኃኑን ጠንካራ ድጋፍ ከማረጋገጡም ባሻገር፣ “የቤተ ክርስቲያንን ትንሣኤ ተስፋ ያየንበት ነው” በሚል በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲኾን በብርቱ ሲጠይቅ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
ይኹንና፣ ለውጡ ተግባራዊ ሲኾን የሚሰፍነው የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራር፣ ሕገ ወጥ ጥቅማቸውን የሚያስቀርባቸው አማሳኝ የአጥቢያ ሓላፊዎች እና በለውጡ፥ የሐዋርያዊ ተልእኳችን መጠናከር ያስደነገጣቸው መናፍቃንና አድርባይ ፖሊቲከኞች ግንባር ፈጥረው በነዙት ውዥንብር፣ ሒደቱ ለጊዜውም ቢኾን ተስተጓጉሏል፡፡
በእጅጉ አሳዛኝ የነበረውና ለታሪክ ትዝብት የሚቀመጠው ግን፣ የፓትርያርኩ አቋም 180 ዲግሪ መዞሩና አማሳኞቹ በሽፋን የተገለገሉበት መኾኑ ነበር፡፡ የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ፣ ቅዱስነታቸው ራሳቸው በሰጡት ቀጥተኛ መመሪያ ጭምር እንዳልተዘጋጀ ኹሉ፣ በአማሳኞች ውዥንብር የአፈጻጸም ሒደቱ ሲታጎልና ሲታገት፣ ቅዱስነታቸው ለማስተካከል ያደረጉት በይፋ የሚታወቅ ግፊትና ጥረት አልነበረም፡፡
ከዚያም በኋላ ሌሎች መለስተኛ ጥረቶች የተሞከሩ ቢኾንም፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና ልዕልና ጠብቆ ለማቆየትና የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ችግር ፈቺ ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ መዋቅራዊ አደረጃጀትና የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት አልተቻለም፤ የመልካም አስተዳደር ዕጦቱ፣ የሀብት ብክነቱና የፍትሕ መዛባቱ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
በተለይ፣ “የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት” የኾነው አዲስ አበባ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ እንደተመለከተው፣ ለሌሎች አህጉረ ስብከት በሞዴልነት በሚጠቀስበት መልኩ መደራጀቱ ይቅርና ዋና ክፍሎቹ እንኳ የሚያከናውኗቸው ተግባራት በዝርዝር አልተለየላቸውም፤ ዐቅዶ ለመሥራትና ለመገምገም የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት የለውም፡፡ እንዲያውም፣ “የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት” የሚለው ድንጋጌ ግልጽ ባለመኾኑ የበርካታ ውዝግቦች መነሻ ኾኗል፡፡ ይህን በመጠቀምና “ተጠሪነታችን ለፓትርያርኩ ነው” በሚል ከሕግና ሥርዓት ውጭ በመኾን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አመራር ያለመቀበል አዝማሚያ ይታያል፡፡
ይባስ ብሎ፣ የሚመለከተውን አካል በማግለል፣ በጎሠኝነትና በጥቅመኝነት ላይ ተመሥርቶ፣ ከሠራተኛ አስተዳደር ደንቡ ውጭ የመቅጠር፣ የማሳደግ፣ የማዛወር፣ የማገድና የማሰናበት አሠራር ተባብሶ የውስጥ ደላሎች ሽሚያና ፉክክር ይታይበት ጀምሯል፡፡ ይህም፣ ከመሠረታዊ ተልእኳችን ጋራ ሳይቀናጅ፣ የእምነት አቋሙና የሥነ ምግባር(ዲስፕሊን) ይዞታው በቅጡ ሳይፈተሽ ወደ መዋቅር የሚገባው የሰው ኃይል ቁጥር ከልክ በላይ እንዲከማች ከማድረጉም ባሻገር፣ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የፋይናንስ ሥርዓት መናጋት መንሥኤ እየኾነ ነው፡፡

በዚኽ መሰሉ አጠቃላይ ሥርዓታዊ ቀውስ ውስጥ በምንገኝበት በአኹኑ ወቅት፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ለሸገር ኤፍኤም102.1 ሬድዮ፣ የጨዋታ እንግዳ ፕሮግራም፣ የሰጡትና ባለፉት ኹለት ተከታታይ ሳምንታት የተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው፣ ፀለምተኛነትና ተስፋ መቁረጥ በግልጽ የተንጸባረቀበት እንደኾነ ብዙዎች የተገነዘቡት ኾኗል፤ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በአስቸኳይ ስለማረምና መልካም አስተዳደርን ስለማስፈን አስፈላጊነት በየመድረኩ ከሚያስተጋቡት አቋም ፍጹም የተለየ፤ የተደረጉ ጥረቶችን እንዳልተደረጉ የሚቆጥርና ድካም የተጫጫነው ድምፅ ኾኖ ተገኝቷል፡፡
መንበሩ ላይ እንደተቀመጡ፣ “ሙስና መጥፋት አለበት” በማለታቸው የተሣቀቁ እንደነበሩና ስለ ሙስና በገሃድ እንዳያነሡባቸው ይሹ እንደነበር ያወሱት ቅዱስነታቸው፣ “አኹን አኹን ለምደውታል” ብለዋል፡፡ የቃሉ መለመድ ግን የተግባር ለውጥ አላመጣም – “ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚያስብ የለም፤ ኹሉም ሰው በገንዘብ ተሽጧል፤ ተለውጧል፤ ጭልጥ ብሎ ሒዷል፤” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ሙስናን ተዉ ማለት ከአንበሳ አፍ ሥጋ የመንጠቅ ያኽል አደገኛ እንደኾነ ተናግረዋል – “ይኼን ተው ማለት፥ ከአንበሳ አፍ ሥጋ እንደ መንጠቅ ነው፡፡ ያ ኾኖ ነው ያለው፡፡ ጨርሶ አይሰማም ሰዉ፤ ጆሮ የለውም፤ ጨርሶ፡፡”
ሌላው አነጋጋሪ የፓትርያርኩ ምላሽ፣ ሙስናን ለማስቀረት በቤተ ክርስቲያን ምንም የተደረገ ነገር የለም፤ ማለታቸው ነው፡፡ ሌላውን ትተን፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔና በራሳቸው መመሪያ ጭምር፣ ሊቃውንቱና ባለሞያዎቹ በትሩፋት የደከሙባቸው፣ ለትግበራ የቀረቡ ጥናቶች አልቀረቡምን? ካህናትና ምእመናን፥ ሙስናን፣ ብክነትንና ብልሹ አሠራርን በማጋለጣቸው ለእስርና እንግልት፣ ለእግድና ስንብት አልተዳረጉምን? ጠንካራ ሰበካ ጉባኤያትና የሰንበት ት/ቤቶች እንዲዳከሙና እንዲበተኑ አልተደረገምን?
ቤተ ክርስቲያን፥ የእውነትና የሐቅ አስተማሪ እንጅ ተማሪ መኾን እንደሌለባት በመጠቆም፣ “ሐቀኝነት፣ ታማኝነትና መልካም ሥነ ምግባር ከቤተ ክርስቲያን ካልተገኙ ከየት ሊገኙ ይችላሉ?” ማለታቸውን ፈጽሞ የዘነጉ የሚመስሉት ፓትርያርኩ፣ በቃለ ምልልሱ፣ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥትን ያኽል እንኳ ጥረት እንዳላደረገች ነው የገለጹልን፡፡ ይብሱኑ፣ “እኛ ደግሞ ይኼን ለማድረግ ኃይሉ የለንም፤ ጉልበቱ የለንም፤” ብለው እጅ መስጠታቸው ሳይበቃ፣ “ጉልበትና ኃይል ያለው ተጠቃሚ የኾነው አካል ነው” በማለት አማሳኙ ኃይል ከቁጥጥር ውጭ የኾነ አቅም መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
ለፓትርያርኩ ምላሽ መነሻ የኾነው ጥያቄ፣ በዓለም ላይ እየተሸረሸሩ ከመጡ ነገሮች አኳያ ቤተ ክርስቲያን ለመጪው ትውልድ ዝግጅት አድርጋ እንደኾን የሚያነሣ ነው፡፡ ከእንግዲኽ በኋላ ተስፋ በማድረግ እንጅ እስከ አኹን ድረስ፣ ሰፊ የኾነና ጥንቃቄ የተመላበት በቂ ዝግጅት አለ ለማለት እንደማይደፍሩ የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ “ወደፊት የሚመጣውን አብረን እናያለን፤” ሲሉ ነው የመለሱት፡፡
ከዕለት ተዕለት የሥራ መርሐ ግብራቸው ጋራ በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፓትርያርኩ የሰጡት ምላሽም ቢኾን፤ ከመዋቅርና አደረጃጀት ችግር አኳያ የሕግና ሥርዓት መዛባቱን፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦቱን በሌላ በኩል የሚያሳይ መጽሔት ነው የኾነው፡፡ ከጠዋት እስከ ምሽት ባለጉዳዩን ሲያስተናግዱ እንደሚውሉ የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ ጉዳዮች ወደየሚመለከታቸው መመሪያዎች ከመሔድ ይልቅ ወደ በላይ የመሮጥ መጥፎ ባህልና ልምድ እንዳለ ቢገልጹም፣ ግን የሚሳካላት ነገር የለም ብለዋል፡፡
ሰዉ ይመጣል፤ ተገድግዶ ይውላል፤ በየዲፓርትመንቱ አይሔድም፤ ወደ በላይ ነው የሚሮጠው ሰው ኹሉ፡፡ ግን የሚሳካላት ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱ በየቦታው በየዲፓርትመንቱ ቢኾን ኖሮ ጉዳዩ ይፈጸምለት ነበር፡፡ ግን እሺ አይልም፤ ባህሉ ልምዱ ጥሩ አይደለም፤ ወደ በላይ መሮጥ ነው፡፡ እና ሰዉ ተገድግዶ፣ መሽቶብኛልና ልሒድ ማለት አይቻልም፡፡ ተራ አስገብቶ ማነጋገር አለ፤ እና በዚኹ እዘገያለኹ፤ በጣም እዘገያለኹ፡፡ ማታ፣ በጣም አምሽቼ ነው የምገባው፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለሓላፊነት ደረጃቸው በማይመጥኑ በዝርዘር ጉዳዮች ላይ ሳይቀር እንደሚሰማሩና ውሳኔ እንዲሰጡ የኾነበት በርካታ አጋጣሚዎች ታይተዋል፡፡ ይህም ለሥራ ድርርቦሽ፣ ለሓላፊነት፣ ለተጠያቂነት ክፍተት፣ በሚገባ ላልታሰበበትና ላልተመከረበት ቅጽበታዊ ውሳኔ፣ ለአሠራር ሥርዓት መፋለስ፣ ለሀብት ብክነት፣ ለአገልጋዮች ወቅታዊ ውሳኔ አለማግኘት፣ መንገላታትና መጉላላት ለመሳሰሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ሊኾን በቅቷል፡፡
በዚኽ ረገድ የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በቀዳሚነት ተወቃሽ እንደኾነ ጥናቶችና ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ልዩ ጽ/ቤቱ፣ ለቅዱስ ፓትርያርኩ የአስተዳደር አገልግሎት ድጋፍና ለጽሕፈት ነክ ሥራዎች የታሰበ መዋቅር ቢኾንም፣ ራሱን፣ ከፍተኛ የመዋቅርና ሥልጣን አካል አድርጎ የሚሠራ እንደኾነ ጥናቶችና ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም፣ ለሕግና ሥርዓት መዛባት፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለመሳሰሉ ችግሮች ቀዳዳ የከፈተ አሠራር ኾኖ ታይቷል፡፡
በአጠቃላይ የፕትርክናውን ሓላፊነት፣ አስበውትና አልመውት ሳይኾን በእግዚአብሔር ጥሪ እንደተቀበሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ሓላፊነቱ ከባድ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
በሕልሜም የለ፤ ፍላጎትም የለ፤ ኧረ እንደው እባክዎትን፤ እንደው አስቸጋሪ የኾነ ነገር የኾነው፤ ምን ይደረግ?
ሓላፊነቱን ከባድ ያደረገውም፥ የአሠራራችን መሥመር አለመያዝ፣ የእርስ በርስ አንድነት አለመኖርና የሓላፊዎች ቸልተኝነት እንደኾነ አስረድተዋል፤ በተለይም፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ የሚታየውን የሓላፊዎች ቸልተኝነት ጠቅሰዋል፡፡
ሓላፊነቱማ ከባድ ነው፤ የሚከብደው ደግሞ የራሳችን አንድ አለመኾን አለ፡፡ አንድነትና አኹን ደግሞ ከነጠቅላላ እንዲያው ቸልተኝነትም መጥቷል፡፡ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለ ነው፤ ሓላፊዎች ቸልተኛነትም እየመጣ ነው፤ በእውነቱ ቀላል አይደለም፡፡
ቃለ ምልልሱን የተከታተሉ አድማጮች በቅዱስነታቸው ምላሽ ውስጥ ያነሷቸውና መታለፍ አልነበረባቸውም ያሏቸው ሌሎችም በርካታ ነጥቦች፡፡ ሙሉ ቃለ ምልልሱን ከ… እንድትከታተሉ እያስታወስን፣ ከዚኽ ቀደም ከተሰሙት ለየት ባለ መልኩ የቀረቡትን የቃለ ምልልሱን ክፍሎች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
************************************
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሃይማኖት መሪነት በተጨማሪ የታሪክና የቅርስ፤ የባህልና የትውፊት፤ የሥነ ጽሑፍ፣ የዜማ፣ የፍልስፍና ጠባቂ ናት፡፡ ከፍተኛ ሓላፊነት ይመስለኛል፡፡ የሀገራችን መነኰሳት ትልቅ የሀገር ቅርስ የኾኑ ንብረቶችን እስከ ዛሬ ጠብቀው አቆይተውልናል፡፡ ምንም ሳይፈልጉ፤ ምንም ሳያምራቸው፡፡ እነርሱ ጥብቅ አድርገው ባይዙት ኖሮ ዛሬ ምንም አይተርፈንም ነበር፡፡ አኹን ዘመኑ እየተለወጠ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን ቅርሶች በጥሩ ኹኔታ ለመጠበቅ ተዘጋጅታለች ወይ? ይህ ሓላፊነት ከባድ ነው፣ ብዬ ነው፡፡
ቅዱስነታቸው፡- ከአኹን ቀደም ቅርሶቹ ብዙ ባክነዋል፡፡ ቅርሶቹ ያሉባቸው ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅርሱ ቁም ነገር አይመስላቸውም፡፡ ጥንቃቄ ይጎድለዋል፡፡ እንደገና ደግሞ ደንበኛ የኾነ ሙዝየም ወይም ቤት የለም፡፡ ከፊሉ አይጥ ይበላዋል፡፡ የውኃ ፍሳሽ ያበላሸዋል፡፡ እንዲያ እንዲያ እየኾነ ብዙ ባክኗል፡፡ ቁም ነገር መኾኑ ከማይገባቸው ሰዎች የሚሸጡም አሉ፡፡ በእነኚህ ምክንያቶች ኹሉ ብዙ አልቋል፤ ብዙ ጥፋት ደርሷል፡፡
አኹን፣ አኹን ግን ያ ኹሉ ብዙ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ደኅና ነው አኹን፡፡ መሸጥ፣ መለወጥና ነገሩን ኹሉ ችላ ብሎ ማበላሸት ትንሽ የተሻለ ነው፡፡ ግን እስከ አኹን ድረስ ያልተደረሰባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ በመሀል ከተማና በከፍተኛ አካባቢዎች ያሉ፣ ለምሳሌ፡- እንደ አኵስም እንደ ላሊበላ ያሉት ታላላቅ አድባራት አኹን ተጠብቀዋል፤ ነገር ግን ያልተደረሰባቸው ደግሞ በየዋሻው ያሉ ቅርሶች አሉ፡፡ መንገድም የሌላቸው፤ የድሮዎቹ አባቶቻችን ከጠላትም ለመሰወር፣ ከጥፋትም ለመዳን መሰለኝ ዋሻ ቆርቁረው እዚያ ውስጥ ነው የሚያስቀምጡት፡፡ ዋሻ ውስጥ የተቆረቆሩ ገዳማትም አሉ፤ ገና ያልተደረሰባቸው አሉ፤ በአጠቃላይ፣ ጥንቃቄ ተደርጎባቸዋል ለማለት አያስደፍርም እንጅ ከነበረው መቼም ይሻላል ብዬ ነው የምገምተው፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባላት ረዥም ታሪክ፣ ብዙ አስቸጋሪ ኹኔታዎች ውስጥ አልፋለች፡፡ ካለፉት ጋራ ሲነጻጸር ይኸኛው ቀላል ሊመስል ይችላል፡፡ ወጣቶች ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች፤ በዓለም ላይ ኹሉም ነገር እየተሸረሸረ የመጣበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ ግን ቢኾንም ቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ አላጣችም፡፡ ጥያቄው፥ ለመጪው ትውልድ ዝግጅት አለ ወይ ነው? በእርስዎ በኩልስ ምን ያስባሉ?
ቅዱስነታቸው፡- በቂ ዝግጅት አለ ለማለት አልደፍርም፡፡ ምክንያቱም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ አኹን ድረስ ብዙ ዝግጅት አላደረገችም፡፡ ሀብቷንም፣ ቅርሷንም በስፋትና በጥንቃቄ መሰብሰብ አልቻለችም፡፡ የአቅም ማነስ አለ፡፡ ኹላችንም እንደምናውቀው በድኅነት የኖረ አገር ነው፡፡ እኛም ካህናቱም ከዚያው ከድኃው ማኅበረሰብ ነው የተገኘነው፡፡ ትምህርት፣ ዕውቀት፣ ሰፊ የኾነ አስተሳሰብ የለም፡፡ ለብቻ ተኣምር መሥራት አይቻልም፡፡ ድካም አለ፡፡ ከአኹን በኋላ ተስፋ እናደርጋለን እንጅ፣ እስከ አኹን ድረስ ጥንቃቄ ነበረ ለማለት አያስደፍርም፡፡
እንደ አኹኑ አእምሮ ሰፋ ባለበት ወቅት ቢኾን ብዙ ሀገሮችን መስበክ፣ ማስተማር፣ ተከታይ ማፍራት እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ያ ኹሉ አልተደረገም፡፡ ሌላው ቀርቶ እዚኹ ሀገራችን እንኳ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡
አኹን ደግሞ፣ የማናውቀው ታሪክ መጥቷል፡፡ የማናውቀው ታሪክ ማለት ይኼ ሙስና የተባለው፥ ገንዘብ ዘረፋ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚያስብ የለም፤ ኹሉም ሰው በገንዘብ ተሽጧል፤ ተለውጧል፤ ጭልጥ ብሎ ሒዷል፤ ጭልጥ ብሎ ሒዷል፡፡ የሚያሳዝን ነው፣ ይኼ ራሱ፡፡ ሌላ አደጋ ነው ደግሞ የተደቀነባት ቤተ ክርስቲያኒቱ፡፡ መልካም አስተዳደር የሚባል ነገር የለም፡፡
ሙስና የቤተ ክርስቲያን ቋንቋ ነው፡፡ ማሰነ፥ ጠፋ ነው፡፡ ሙስና፥ ጥፋት ነው፡፡ እኔ እዚህ መንበር ላይ ስቀመጥ፣ በመጀመሪያ፣ ሙስና መጥፋት አለበት፤ እያልኩ አንዳንድ ነገር ስናገር፣ ይኼን ቃል አታንሣብን፤ ይሉኝ ነበር፡፡ ለምን ስል፣ በገሃድ መነገር የለበትም፤ ይሉኛል፡፡ ቋንቋው እኮ የቤተ ክርስቲያን ነው፤ ጥሩ ትርጉም ነው ያለው፤ ገንዘብን መስረቅ፣ ማማሰን፥ ማጥፋት ማለት ነው፡፡ ግሩም የኾነ ትርጉም ነው የተሰጠው በእውነቱ፡፡ ኧረ አታንሣብን ማለት ጀምረው ነበር፤ አኹን አኹን ለምደውታል፡፡
እንዲኽ ዓይነት አደጋ በቤተ ክርስቲያን ላይ መጥቷል፡፡ እግዚአብሔር ያድነን በእውነቱ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይኾን በጠቅላላ በሀገሪቱም ያለ ነገር ነው፤ የኾነው ኾኖ መንግሥት ይኼን ለማስቀረት ይታገላል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ግን ምንም የተደረገ ነገር የለም፡፡ እኛ ደግሞ ይኼን ለማድረግ ኃይሉ የለንም፤ ጉልበቱ የለንም፤ ጉልበትና ኃይል ያለው ተጠቃሚ የኾነው አካል ነው፡፡ ይኼን ተው ማለት፥ ከአንበሳ አፍ ሥጋ እንደ መንጠቅ ነው፡፡ ያ ኾኖ ነው ያለው፡፡ ጨርሶ አይሰማም፤ ሰዉ፤ ጆሮ የለውም፤ ጨርሶ፤ ጨርሶ፡፡ ይኼ አደገኛ የኾነ ጉዳይ ነው፡፡ ወደፊት የሚመጣውን አብረን እናያለን፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ብዙ የወጣትና የጉልምስና ዕድሜዎን በገዳም ነው ያሳለፉት፤ በኢትዮጵያ ወደፊት ይኼ የሚቀጥል ይመስሎታል?
ቅዱስነታቸው፡- ገዳማቱ እየተዳከሙ ናቸው፡፡ ለምን? ድሮ መሬት ነበራቸው፡፡ በመሬት ነው የሚተዳደሩት፡፡ በመሬት ሲተዳደሩ፥ እያሳረሱ፣ እያረሱ መሬታቸው በደርግ ተወረሰ፡፡ መሬት ለአራሹ ተባለ፤ መሬታቸው ተወረሰ፡፡ አኹን ባዶአቸውን ነው የቀሩት፡፡ እና ብዙ ገዳማት ተዳክመዋል፡፡ አንዳንድ ገዳማት ደግሞ ራሳቸውን አትክልት እየተከሉ፣ ተግባረ እድ እያደረጉ የሚኖሩ አሉ፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- እነርሱ በተዳከሙበት ጊዜ፣ የአብነት ት/ቤቶችም ችግር ይገጥማቸዋል፤…
ቅዱስነታቸው፡- ታድያስ፣ ታድያስ፤ በሀገራችን የአብነት ትምህርት መምህራንና ተማሪዎች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እነርሱን መርዳት አልቻለችም፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ፤ አቅም የላትማ፡፡ ከየት ታመጣለች? እንዴት አድርጎ? እንጅ፣ ትምህርት ቤቱ በሰፊው ነው ያለው እስከ አኹን ድረስ፡፡ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የዜማ፣ የቅኔ፣ የአቋቋም በሰፊው ነው ያለው፡፡ ግን፣ ምግብ የሚመግባቸው የለም፤ እየለመኑ ነው፡፡ ልመና ደግሞ ተሰልችቷል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ሠለጠን እያሉ፥ አንተ ተማሪ ሠርተኽ አትበላም እንዴ? ማለት ተጀምሯል፡፡ ድሮ ተማሪ ክቡር ነው፤ መንደር እየተካፈለ ነበር የሚማረው፤ ለምሳሌ፥ መአት የቅኔ ተማሪ በአንድ ጉባኤ ቤት ይቀመጣል፤ ከዚህ ወዲህ ላንተ ከዚህ ወዲያ ላንተ እየተባለ መንደሩን ይካፈላል፤ ምእመናን ደግሞ እንደ ራሳቸው ቤተሰብ አድርገው ነው ምግቡን የሚሰጡት፡፡ እንግዲህ ድሮ መምህራንም ደመወዝ የላቸውም፤ ተማሪውም ደመወዝ የለውም፤ መምህራኑ ራሳቸው ያለደመወዝ ነው የተማሩት፤ ሲያስተምሩም እየተለመነላቸው ነው፤
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ያ እንግዲህ ራስን ዝቅ ከማድረግ፣ ወደ መንፈሳዊነትምኮ የሚያስጠጋ መንገድ ነው፣ በችግር ውስጥ ማለፍ፤ እርሱም አንድ ቁም ነገር ይመስለኛል፤
ቅዱስነታቸው፡- አዎ፣ መናኒ አለ፤ ማስተማሩን የእኔ ብሎ ይዟል፤ መምህራኑ፥ ለምን ደመወዝ አላገኘንም አይሉም፤ በቃ፣ እንደ ተማሪዎቻቸው መንደር ተካፍለው ለምነው ያመጡላቸዋል፤ ይህችን ትንሽ ቁራሽ ካገኙ ይህን እየተመገቡ ነው የሚያስተምሩት፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ቅዱስነትዎ ባሉበት ሓላፊነት፣ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ሥራው ምን ይመስላል? ሰፊ ሓላፊነት ይመስለኛል፤ 35ሺሕ አብያተ ክርስቲያናት፤ 1ሺሕ500 ገዳማት፤ 50 ጳጳሳት፤ 400ሺሕ ቀሳውስት፤ 20ሺሕ ተማሪ ቤቶች አሉ፡፡ የእነኚኽ ኹሉ አባት እርስዎ ነዎት፤ ምን ይመስላል ቀኑ?
ቅዱስነታቸው፡- አይ፣ እንግዲህ፤ ችግሩ ምንድን ነው፤ መሥመር አልያዘም፤ ሥራችን አሠራራችን መሥመር አልያዘም፡፡ ለምሳሌ፡- እነዚኽን ኹሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይዘን በደንብ መሥመር ማስያዝ አልቻልንም፡፡ ገዳማቱም ደግሞ፣ ገዳማዊ ሕይወታቸውን ይዘው ይኖራሉ፡፡ አንዱ ደካማ ነው፤ ሌላው ብርቱ ነው፡፡ የተለያየ ኑሮ ነው ያላቸው፡፡ የሚተዳደሩት በመሬት ነበር፡፡ መሬቱ ሲወሰድ ደግሞ መድከም መጥቷል፡፡
እና ሓላፊነቱ ከባድ ነው፤ ሓላፊነቱማ ከባድ ነው፤ የሚከብደው ደግሞ የራሳችን አንድ አለመኾን አለ፡፡ አንድነትና አኹን ደግሞ ከነጠቅላላ እንዲያው ቸልተኝነትም መጥቷል፡፡ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለ ነው፤ ሓላፊዎች ቸልተኛነትም እየመጣ ነው፤ በእውነቱ ቀላል አይደለም፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ጠዋት ስንት ሰዓት ይነሣሉ?
ቅዱስነታቸው፡- እኔ እንግዲኽ አምሽቼ ነው የምተኛው፤ በአራት ሰዓት፣ በአራት ሰዓት ተኩል እንደዚኽ እተኛለኹ፡፡ ለሦስት ሰዓት ያህል እተኛና እነቃለኹ፡፡ ከዚያ በኋላ የራሴን ጉዳይ እሠራለኹ፤ የጸሎቱን፣ የሚነበብ እንዳለ፤ ከዚያ በኋላ በእንቅልፍ ትንሽ አሳልፋለኹ፡፡ ኤክሰራይስ አደርጋለኹ፡፡ ያው ሥራ የምንገባው ጠዋት በሦስት ሰዓት ነው፡፡ አስቸኳይ ነገር ከሌለ በቀር በዚኹ መልክ ነው እንግዲኽ የምንነሣው፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ቀኑን ሙሉ ሲሠሩ ይውላሉ…
ቅዱስነታቸው፡- አዎ
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ከሥራ ስንት ሰዓት ይወጣሉ?
ቅዱስነታቸው፡- ኡ ኡ…(ሣቅ) እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት የምቆይበት ጊዜ አለ፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- መኖርያዎም እዚኹ ነው?
ቅዱስነታቸው፡- እዚኹ ነው፤… እና ሰዉ ይመጣል፤ ተገድግዶ ይውላል፤ በየዲፓርትመንቱ አይሔድም፤ ወደ በላይ ነው የሚሮጠው ሰው ኹሉ፡፡ ግን የሚሳካላት ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱ በየቦታው በየዲፓርትመንቱ ቢኾን ኖሮ ጉዳዩ ይፈጸምለት ነበር፡፡ ግን እሺ አይልም፤ ባህሉ ልምዱ ጥሩ አይደለም፤ ወደ በላይ መሮጥ ነው፡፡ እና ሰዉ ተገድግዶ፣ መሽቶብኛልና ልሒድ ማለት አይቻልም፡፡ ተራ አስገብቶ ማነጋገር አለ፤ እና በዚኹ እዘገያለኹ፤ በጣም እዘገያለኹ፡፡ ማታ፣ በጣም አምሽቼ ነው የምገባው፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ብቸኛ ነዎት፣ እዚኽ?
ቅዱስነታቸው፡- መነኰሳት አሉ፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- እንደው ዐረፍ ብላችሁ እስር በርስ የምትጫወቱበት ጊዜ አለ?
ቅዱስነታቸው፡- አይ…
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- እርስዎ የሚወዱት ምንድን ነው? መጽሐፍ ማንበብ…
ቅዱስነታቸው፡- ምምም… መጽሐፍ ማንበብ… አኹንማ፣ ሆሆሆ..
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ጊዜ የት ተገኝቶ?
ቅዱስነታቸው፡- አኹንማ የት ተገኝቶ… ወይ ጉድ… አኹንማ ሆሆ.. ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቆይቶ መሥራቱ አግባብ ነው ብዬ ሳይኾን፣ ሰዉ ዝም ብሎ እዚህ ተገትሮ ውሎ እንዲያው ዝም ብሎ ሒድ ማለቱ ስለሚከብድ ነው እንጅ በአግባቡ መሥራቱ ነው ጠቃሚ የሚኾነው፤ እንግዲህ አልቻልኩም፡፡ ያው ሰዉን ስናስተናግድ እንውላለን፤ እንደዚያ ነው፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ምን ዓይነት መጽሐፍ ማንበብ የሚወዱት? ከሃይማኖት፣ ከጸሎት መጽሐፍ ሌላ፤ ታሪክ ያስደስትዎታል?
ቅዱስነታቸው፡- አዎ፣ እንዴታ! ታሪክ ያስደስተኛል፤ የታሪክ መጻሕፍት አሉኝ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ፤ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ አንድምታዎቹ፣ እነርሱ፣ እነርሱን አነባለኹ፡፡ ግን ጊዜው ዛሬ ምንም አልቻልኩም፤ ድሮ ነበረ፤ እዚህ ከመግባቴ በፊት ነጻነት ነበረኝ፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚወዱት የትኛውን ነው? ኹሉንም ይወዳሉ፤ የሚያስበልጡት ማለቴ ነው፤
ቅዱስነታቸው፡- መቸም ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበት፡- ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር፤ የጥበብ ኹሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ይላል፡፡ ትልቁ ጥቅሳችን፡፡ ሰው ፈሪሃ እግዚአብሔር ከሌለው ዋጋ የለውም፡፡ እንደው፣ ፈጣሪውን ካላወቀ፣ እግዚአብሔር አለ፤ ካላለ፤ ኃጢአት ብሠራ እግዚአብሔር ይፈርድብኛል፤ ካላለ ልጓም የሌለው ፈረስ ነው፤ ዋጋም የለውም፡፡ እና የጥበብ ኹሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ የሚለው ነው፤ ሌሎችም አሉ፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- እርስዎ ቅድም ብዙ ሥራ እንደሚበዛ ነግረውኛል፤ የቤተ ክርስቲያኒቷ መሪ ነዎት፤ ግን ሌላ ሊሠሩ፣ ሊያስተምሩ የሚፈልጉት ነገር አለ? ስለ ተፈጥሮ ጉዳይ ያሳስብዎታል፤ የተፈጥሮ ሀብትን በሚመለከት፤ ርግጥ የሰላም ጉዳይ አንዱ ሥራዎት ነው፤…
ቅዱስነታቸው፡- አዎ፣ በጣም… የተፈጥሮ ማለት ዕፀዋት…
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ዕፀዋት…አዎ፣ እርስዎ በገዳም ስለኖሩ…፤
ቅዱስነታቸው፡- በጣም፤ እንግዲኽ ለሰውም ኾነ ለምድር ጌጧ ደን ነው፡፡ ለምድር የደም ሥሯ ዕፀዋት ናቸው፡፡ ዕፀዋት እንዲከበሩ፣ እንዳይቆረጡ፣ እንዲተከሉ፤ ዕፀዋት ከሌሉ ምድሪቱ እንደሌለች፤ ሰው የደም ሥሩ ከተቆረጠ ሕይወት እንደሌለው፣ ይኼን ይኼን በተቻለኝ አጋጣሚ አስተምራለኹ፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ፤ በየእሑዱ፣ በየወርኃዊ በዓላቱ፣ በየዐበይት በዓላቱ፤ ከዚኽ ሌላ ደግሞ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፤ አንድነትና ሰላም ከሌለ ሀገር እንደሌለ፤ ይኼን ይኼን ነው የምናስተምረው፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- እንግዲኽ፣ በተለያየ ምክንያት የፖሊቲካውም ጉዳይ እየገባ፣ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ የእርስ በርስ መከፋፈል አለ፤ በመላው ዓለምና በሀገር ውስጥ ላሉት ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ ማለት የሚፈልጉት ነገር ካለ? የሚጠይቁት፣ የሚመክሩት ካለ?
ቅዱስነታቸው፡- መቼም፣ ቤተ ክርስቲያን ልታደርግ የምትችለው፣ ማንንም ማንንም ሳትል ሰላምን መስበክ ነው፤ የሚበጀው፣ በውስጥ ያለውንም በውጭ ያለውንም የምታስተምረው፥ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሃይማኖት ጽናት ነው ምንጊዜም ቢኾን በሰፊው ነው የምናስተምረው፡፡ አኹን ደግሞ እንደ ዘመኑ ስለ ልማት ደግሞ እናስተምራለን፤ እንግዲኽ ሚዲያው ብዙ ደጋፊ የለውም እንጅ እኛ የምንለው፣ እኛ የምናስተምረው ትምህርት በሙሉ ቢሰበክ፣ በሚዲያ ቢተላለፍ ይጠቅም ነበር፡፡ ያው ይኼን ያህል አትኩሮት የሚሰጠው የለም፡፡ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሀገር ሰላም፣ ተቻችሎና ተረዳድቶ ስለ መኖር፣ በሃይማኖት ጸንቶ ስለ መኖር ስለዚኽ ኹሉ እናስተምራለን፣ የተቻለውን ያህል፡፡ እኔ በሔድኩበት ኹሉ ሥራዬ እርሱ ነው፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ ሒብሩ፣ እንግሊዝኛ ይናገራሉ፤ ዐረብኛ ይናገራሉ፤ ሌላስ አልጨመሩም? ነው የረሳኹት አለ፣ እዚኽ ውስጥ?
ቅዱስነታቸው፡- አይ፣ የለም፤ ዕብራይስጡ እየተረሳ እየሔደ ነው፤ ዐረብኛ እንኳ ድሮም ብዙ አልነበረም፤ ዕብራይስጥ ትንሽ ትንሽ ዐውቅ ነበር፤ እየተረሳ ሔደ፤
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ቤተሰቦችዎን ያገኛሉ? እርግጥ እናት አባትዎ በሕይወት ላይኖሩ ይችላሉ፤
ቅዱስነታቸው፡- የሉም
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- እርስዎ እዚኽ ደረጃ መድረስዎን እናት አባትዎ አላዩም? ጳጳስ በኾኑ ጊዜ አይተዋል?
ቅዱስነታቸው፡- የለም፤ የት ተገናኝተን፤
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- አኹን ዘመዶችዎ ይጠይቅዎታል?
ቅዱስነታቸው፡- አይ፣ አንዳንድ ሰዎች እየመጡ አይተውኝ ይሔዳሉ፤ ርግጥ፣ በከተማም ያሉ ሰዎች አሉ፤ የቅርብ ዘመድ እንኳ ብዙ የለኝም፤ አልፎ አልፎ ከሀገር ቤት ይመጣሉ፤ አይተውኝ ይሔዳሉ፤
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- መነኵሴ ዘመድ የለውም?
ቅዱስነታቸው፡- አዎ፤ የለውም
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ኹሉ ዘመዱ ነው፤
ቅዱስነታቸው፡- አዎ፣ ልክ ነው
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- አንድ የመጨረሻ ጥያቄ፤ ወጣቱ ካህሳይ፣ አንድ ቀን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ይኾናል ብሎ አስበው፣ ተመኝተው ያውቁ ነበር? ወይስ ሕልም አይቼሎታለኹ ያለ ሰው ነበር?
ቅዱስነታቸው፡- ኧረ በጭራሽ፤ ኧረ በጭራሽ፤ እኔ ምንም ስለዚኽ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ርግጥ ገዳም ውስጥ ቅኔ ቤት ሳለሁ፣ አንድ ሕልም አይቼ ለአስተማሪዬ ነገርኋቸውና ገረማቸው፡፡ ያኔ ተራ መነኵሴ ነኝ፤ ግን የቅኔ ተማሪ ነኝ፤ የዜማም ተማሪ ነኝ፤ ሕልሙ ምንድን ነው፥ የቀድሞው የትግራይ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ጎርድ ምስል፣ ፀሐይዋ ላይ ቁጭ ብለው ፀሐይዋ ትታየኛለች፡፡ በእጃቸው፣ ና ይሉኛል፡፡ እርሱን፣ ዬኔታ ዕንቈ ባሕርይ ለሚባሉት አስተማርዬ ነገርኋቸው፡፡ ስነግራቸው ተገረሙና፣ እንዴ፣ ይኼ ምንድን ነው? ጳጳስ ትኾናለህ እንዳንል ከየት ወዴት?(ሣቅ)
.. እንደገና ደግሞ አስተማሪዬ፣ ዬኔታ አየለ ዓለሙ፣ እዚያ ጉባኤ ቤት ምን ይሉ ነበር.. እኔ መነኵሴ ነኝ፤ ጉባኤውን በየጠዋቱ በጸሎት የምከፍተው እኔ ነኝ፤ እርሳቸው በሌለኹበት ጊዜ፣ ጳጳሱ የት ሔዱ? ይሉ ነበር፡፡ ይህን እዚያ አካባቢ የነበረ ሰው ኹሉ ያውቀዋል፡፡ ከሹመት በኋላ፣ እዚያ ጉባኤ ተማሪ የነበሩ ኹሉ፥ የዬኔታ ዶ/ር አየለ ዓለሙ ትንቢት ደረሰ፤ ብለዋል፡፡ ይኼ ይኼ ነው እንጅ እኔ ሕልምም፣ ነገርም አልነበረኝ፡፡
የፓትርያርክ ምርጫው እስከተካሔደበት ወቅት ድረስ ኢየሩሳሌም ነው የነበርኩት፡፡ የመጨረሻው ስብሰባ እንደ ዛሬ ኾኖ በሳምንቱ ደግሞ ፓትርያርክ እንዲሾም ተወስኖ ተጠራኹና መጣኹ፡፡ በጭራሽ በሕልሜም ያልነበረ እኮ ነው፡፡ በሲኖዶሱ ተጠራኹና፣ ውድድሩ ውስጥ አስገብተነሃል፤ አሉኝ፡፡ ኧረ ብዙ ፈላጊ አለ፤ እባካችሁ ለምን እኔን? እኔ አልችለውም ይህን ጉዳይ፤ እኔ ጵጵስናም ስሾም አልፈለግኹም፤ ቅድም እንደተነጋገርነው፣ ወደ ግሪክ ሔጄ ትምህርት መቀጸል ነው እንጅ የማስበው የነበረው እንጅ መኾን አልፈለግኹም፤ አኹንም የፓትርያርክነት ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፡፡ አንደኛ፡- ጉዳዩ በሕልሜ የለም፤ ኹለተኛ፡- ብዙ ፈላጊዎች አሉ አይደለም ወይ፤ እነርሱን አታወዳድሩም እንዴ? ብል፣ አይ አስገብተነሃል አሉ፤ እና ደግሞ የእግዚአብሔር ጥሪ ኾኖ መሰለኝ እኔ አለፍኩ፤ ከአምስት ተወዳዳሪዎች እኔ አለፍኩኝ፤ ከ806 መራጮች 500 ድምፅ አግኝቼ እንጅ በሕልሜም የለ፤ ፍላጎትም የለ፤ ኧረ እንደው እባክዎትን፤ እንደው አስቸጋሪ የኾነ ነገር የኾነው፤ ምን ይደረግ?
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ሓላፊነቱን ተሸክመዋል አኹን እንግዲኽ፤
ቅዱስነታቸው፡- ኡ ኡ ኡ… ቀላል አይደለም፤ ቀላል አይደለም፤
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ብርታቱንም ይስጥዎት፤ ትክክለኛውን መንገድ ያሳይዎት፤
ቅዱስነታቸው፡- አሜን፤ አሜን
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- በጣም ነው የማመሰግነው፤ ቅዱስነትዎ፣ መዝሙር ያዳምጣሉ?
ቅዱስነታቸው፡- መዝሙር፣ አዎ፤ ብዙ ጊዜ ከሚያጥረኝ በቀር፤ እንዲያውም ብዙ ትርጓሜ መጻሕፍትና ዜማ የያዘ አይፓድ ነበረኝ፤ አኹን ተበላሸብኝ፤ አንዳንድ ጊዜ እርሱን አዳምጥ ነበር፤ ወሬ(ዜና) አዳምጣለኹ፤ እርሱ አያመልጠኝም፡፡ ሬድዩ ግን ከነጭራሹ የለኝም፤ የእናንተን ሬድዮ እንዴት እንደማዳምጥ አላውቅም፤(ሣቅ) እንዲያውም ጎንደር ሳለሁ ሬድዮ አዳምጥ ነበር፡፡ እዚኽ ግን ዜናውን ብቻ በቴሌቭዥን እመለከታለኹ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ሥራዬ ነው፤ በቃ፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ፖፕ ፍራንሲስን አግኝተዋቸው ያውቃሉ፤ ከሌሎችም ጋራ እንደዚኹ፤
ቅዱስነታቸው፡- አዎ፣ እርሳቸው አንዱ ናቸው፤ የግብጹ ፓትርያርክንም ጎብኝቻለኹ፤ እርሳቸውም እዚኽ መጥተው ጎብኝተዋል፤ የሕንድ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክንም ባለፈው ሔጄ ጎብኝቻለኹ፤ ሊባኖስ ያሉት የአርመን ፓትርያርክንም እዚያው ሔጄ ተገናኝተናል፤ የሶርያውን፥ ችግር ስለነበር በሀገሩ፣ አንዱ ዐርፈው ሌላው ሲሾሙ መሔድ ሲገባኝ አልሔድኩም፤ ኢየሩሳሌም ደግሞ ብዙ ፓትርያርኮች አሉ፤ የግሪክ ኦርቶዶክስ፣ የላቲን(ማለትም የካቶሊክ)፣ የአርመን ፓትርያርኮች አሉ፤ አብረን ኖረናል፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ በምን ቢታወሱ ይሻልዎታል? ስናስታውስዎት?
ቅዱስነታቸው፡- በምን ቢታወሱ!? ኧሃ.. በቃ፣ በመንፈሳዊነት፤ ሌላ ምን አለኝ፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- በዚያ ቢታወሱ ደስ ይልዎታል፤
ቅዱስነታቸው፡- አዎ፤
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፡- እግዚአብሔር ይስጥልኝ፤
ቅዱስነታቸው፡- እግዚአብሔር ይስጥልኝ፤ እናንተም ስለመጣችኹ አመሰግናለኹ፡፡

No comments:

Post a Comment